ቅዱስ ጊዮርጊስ ይፋዊ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ፈፅሟል

ፈረሰኞቹ መጪውን ሦስት ዓመታት አብሮ የሚዘልቅ የአጋርነት ስምምነት ፈፅመዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ከዊነር ኢቲ የስፖርት ውርርድ ተቋም ጋር ለሚቀጥሉት ሦስት አመታት የሚቆይ የስፖንሰርሺፕ ውል ስምምነት በዛሬው ዕለት በስካይ ላይት ሆቴል መፈፀማቸውን ታውቋል። በፊርማ ሥነ ስርዓቱ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል የክለቡ የቦርድ አባል አቶ ዳዊት ውብሸት እና ስራ አስኪያጁ አቶ ሰለሞን በቀለ በዊነር በኩል የተቋሙ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ንጋት ሙልጌታ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በውል ስምምነቱ መሠረት ዊነር በመጀመሪያው ዓመት 25 ሚልዮን ብር ገንዘብ የሚከፍል ሲሆን በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ውጤቱ እየታየ የሚያድግ ክፍያ እንደሚፈፀም ተመላክቷል። በተጨማሪም ለክለቡ ሙሉ የልምምድ እና የጨዋታ የስፖርት አልባሳት በዊነር እንደሚያቀርብ በስምምነቱ ወቅት ተገልፆል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በመጪው ሦስት ዓመታት የተቋሙን አርማ በማልያው ላይ ያኖራል ፣ በጨዋታ ወቅት የማስታወቂያ ቦርድ ያስቀምጣል ፣ ክለቡ በሚያዘጋጀው ዝግጅቶች እና መፅሔቶች አርማውን ያስቀምጣል እንዲሁም በልምምድ ወቅት የዊነር አርማ ያለበትን መለያ የሚለብስ ይሆናል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን በቀለ በስምምነቱ ወቅት እንደተናገሩት “ቅዱስ ጊዮርጊስ ህዝባዊ ክብ ነው። ለ88 ዓመት በየዘመኑ ያጋጠሙትን መሰናክሎች ሁሉ በሰከነ አመራር ፣ በትግዕስት እና በብልሀትና እየተወጣ ሁሌም ማሸነፍ ዓላማው ብቻ አድርጎ ብርቱ ጥረት የሚያደርግና የሚተጋ ክለብ ነው፡፡ ከዊነር ጋር በአውንታዊነት ፣ ተግባብቶ በመስራት የተገኘውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ክለቡን በማዘመን ወደ ተሻለ የዕድገት ደረጃ ለማድረስ ያለመታከት እንሰራለን ፡፡” ብለዋል የዊነር ኢቲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ንጋት ሙሉጌታ በበኩላቸው “ይህንን ስምምነት በመፈፀማችንና የኢትዮጵያ እግርኳስ መሠረት የሆነውን ቅዱስ ጊዮርጊስ መምረጣችን ያኮራናል።” በማለት ተናግረዋል።