ሲዳማ ቡና ከአሰልጣኙ ጋር ተለያየ?

ሥዩም ከበደን ያገደው እና ከአሰልጣኙም ጋር ሊለያይ ከጫፍ የደረሰው ሲዳማ ቡና በቀጣይ በጊዜያዊነት በቴክኒክ ዳይሬክተሩ ይመራል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2016 የውድድር ጉዞውን በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ መሪነት የሊጉን አምስት ሳምንታት ያደረገው እና ካደረጋቸው ጨዋታዎች ሦስቱን በሽንፈት አንዱን በአቻ እንዲሁም አንዱን በማሸነፍ በደረጃ ሰንጠረዡ 11ኛ ላይ በአራት ነጥቦች የተቀመጠው ሲዳማ ቡና ከአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ጋር ሊለያይ ከጫፍ ስለ መድረሱ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ አቡሽ አሰፋ ለዝግጅት ክፍላችን እንደ ገለፁት አሰልጣኝ ስዩም ከበደ በአምስቱ የጨዋታ ሳምንታት ያስመዘገቡትን ውጤት ተንተርሶ የዕግድ ውሳኔ እንደተላለፈባቸው ገልፀው ዛሬ ወይም በቀጣይ ቀናት የክለቡ ቦርድ በሚያደርገው ስብሰባው አዲስ ነገር ሊኖር እንደሚችል ነግረውናል።

አመርቂ ውጤትን አለማስመዝገባቸውን ተከትሎ በክለቡ ስራ አስኪያጅ የዕግድ ውሳኔ ግልባጭ የደረሳቸው አሰልጣኙ እና ረዳታቸው አሰልጣኝ አረጋዊ ወንድሙ በክለቡ የቦርድ ስብሰባ ከክለቡ የመለያየታቸው ጉዳይ ዕርግጥ እንደሚሆን ይጠበቃል። በአዳማ ከተማ ዝግጅቱን ከዕረፍት መልስ የሚቀጥለው ሲዳማ ቡና የልምምድ መርሃግብሩን በቴክኒክ ዳይሬክተሩ አለምባንተ ማሞ መሪነት ወደ ዝግጅት እንደሚገባ ስራ አስኪያጁ አያይዘው ለሶከር ኢትዮጵያ ይፋ አድርገዋል።