ጋቦን 2017፡ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ዛሬ ይጀምራሉ

  • ጋቦን ለምታስተናግደው የ2017 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ዛሬ በተለያዩ ከተሞች በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጀመራሉ፡፡ በ2015 ዲኤስቲቪ ሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ካፕ ላይ እስከሩብ ፍፃሜ የተጓዘችው ደቡብ ሱዳን ጁባ ላይ ቤኒንን ታስተናግዳለች፡፡ ደቡብ ሱዳን በምድብ 3 በሶስት ነጥብ ከምድብ መሪዋ ማሊ በአንድ ነትብ አንሳ ሁለተኛ ስትሆን በመጀመሪያው የማጣሪያ ጨዋታ የ2015 የአፍሪካ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ የነበረችውን ኤኳቶሪያል ጊኒን በአታክ ሉአል ግብ 1-0 አሸንፋለች፡፡ የብራይት ስታርስ አሰልጣኝ ቢላል ፊሊክስ ኮሞያንጊ በአውሮፓ፣ አውስትራሊያ፣ ሰሜን አሜሪካ እና ጎረቤት ሱዳን የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ለብሄራዊ ቡድኑ ጠርተዋል፡፡ ተጋጣሚዋ ቤኒን በ2 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡

    በቀኑ ትልቅ ጨዋታ የ2012 የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ዛምቢያ ኮንጎ ብራዛቪልን በሜዳዋ ትገጥማለች፡፡ የቺፖሎፖሎዎቹ አሰልጣኝ ጆርጅ ላዋንዳሚና በኮንጎ ብራዛቪል ሊግ ከኤሲ ሊዮፖርድስ ጋር የተሳካ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኘውን ዊንስተን ካሌንጎ እና ግብ ጠባቂው ኬኔዲ ኢምዌኔ ለጨዋታው ጠርተዋል፡፡ በማጣሪያው 4 ግቦችን ያስቆጠረው አጥቂው ፌሬቦሬ ዶሬ በረጅም ግዜ ጉዳት ከቡድኑ ውጪ የሆነባት ኮንጎ ባራዛቪል በበኩሏ አሁንም በኮከብ አጥቂዋ ቲዪቪ ቢፎማ ላይ ጥገኛ የምትሆን ይሆናል፡፡ ምድብ አምስትን ኮንጎ ብራዛቪል በአራት ነጥብ ስትመራ ዛምቢያ በተመሳሳይ ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጣ ሁለተኛ ናት፡፡ በምድቡ ሌላ ጨዋታ ጊኒ ቢሳው ኬኒያን የምታስተናግድ ይሆናል፡፡

    ቻድ ኒጃሚና ላይ ታንዛኒያን ትገጥማለች፡፡ ሁለቱም ሃገራት ከምድቡ የማለፍ ተስፋቸው ከአሁኑ ላለማጨለም 3 ነጥብ ማግኘት ላይ ተመስርተው ይጋጠማሉ፡፡ ሁለቱ ሃገራት የሚገኙበትን ምድብ ሰባት ግብፅ በስድስት ነጥብ ስትመራ ናይጄሪያ በአራት ትከተላለች፡፡

    በምድብ ስድስት ሳኦ ቶሜ እና ፒሪንስፔ ሊቢያን የምታስተናግበት ጨዋታ ሳኦ ቶሜ ላይ ይደረጋል፡፡ ሁለቱም ሃገራት በመጀመሪያ ሁለት የምድብ ጨዋታ ሽንፈትን የቀመሱ ሲሆን ከአሁን ከማጣሪያው ውጪ ላለመሆን የግድ ማሸነፍን አላማ አድርገው ወደ ጨዋታ ያመራሉ፡፡ ምድቡን በፊፋ ኮካ ኮላ የዓለም የሃገራት ደረጃ የአፍሪካ ቁጥር አንድ የሆነችው ኬፕ ቬርዴ እና ሞሮኮ በእኩል ስድስት ነጥብ በግብ ክፋያ ተበላልጠው ይመራሉ፡፡

     

    የዛሬ ጨዋታዎች

    (15፡30 GMT) ቻድ ከ ታንዛኒያ (ስታደ ኢድሪስ ማህማት ኦያ)

    (15፡30 GMT) ሳኦ ቶሜ እና ፒሪንስፔ ከ ሊቢያ (12 ዲ በጁሎ)

    (16፡00 GMT) ጊኒ ቢሳው ከ ኬኒያ (ስታዲዮ 24 ዲ ስትምብሮ)

    (16፡30 GMT) ደቡብ ሱዳን ከ ቤኒን (ጁባ)

    (18፡00 GMT) ዛምቢያ ከ ኮንጎ ብራዛቪል (ሌቪ ማዋንዋሳ ስታዲየም)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *