ሪፖርት | ሀዲያ ሆሳዕና ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሷል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በ12ኛው ሳምንት የመጀመሪያ ቀን የምሽት ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና በሳምሶን ጥላሁን የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ሰበታ ከተማን 1-0 አሸንፏል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከጅማው ሽንፈት ባደረጋቸው ለውጦች መሳይ አያኖን በሶሆሆ ሜንሳህ ፣ ከቅጣት የተመለሰው ፍሬዘር ካሳን በኤልያስ አታሮ ፣ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀንን በአበባየሁ ዮሐንስ ፣ እንዲሁም ሚካኤል ጆርጅን በሀብታሙ ታደሰ በመተካት ጨዋታን ጀምሯል። በሰበታ በኩል በታዩ ቅያሪዎች ደግሞ ሰለሞን ደምሴ ፣ በኃይሉ ግርማ ፣ ዘላለም ኢሳይያስ እና ፍፁም ገብረማሪያም በፋሲሉ ሽንፈት ተሰልፈው የነበሩት ለዓለም ብርሀኑ ፣ ታፈሰ ሰርካ ፣ ጌቱ ኃይለማሪያም እና አብዱልሀፊዝ ቶፊቅን ተክተዋል።

በአመዛኙ ተመጣጣኝ በነበረው የጨዋታው አጀማመር በሁለቱም በኩል ያለቀላቸው ዕድሎች በብዛት አልተፈጠሩም። 4ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬዘር ካሳ ከማዕዘን ምት ጥሩ የግምባር ኳስ አግኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው ዕድል ለቡድኑ የሚያስቆጭ ነበር ። ሆሳዕና ሲጀምር የነበረውን አንፃራዊ ጫና ሳያስቀጥል ከዚህ ኳስ ሌላ አደጋ መጣል ከብዶት ታይቷል። አንዳቸው የሌላኛቸውን የማጥቃት እንቅስቃሴ በማቋረጥ የቀጠሉት ቡድኖቹ በቶሎ ወደ ጎል ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት የሚሳካ አልሆነም። የጨዋታው ቀዳሚ ከባድ አጋጣሚዎች 19ኛው ደቂቃ ላይ ሲታዩ የሳሙኤል ሳሊሶ ሁለት ተከታታይ የማዕዘን ምቶች በዘካሪያስ ፍቅሬ እና ፍፁም ገብረማሪያም ወደ ግብ ቢላኩም መሳይ አያኖ በአስገራሚ ቅልጥፍና አድኗቸዋል።


ጨዋታው ከውሀ ዕረፍት ሲመለስ ሆሳዕናዎች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር እርጋታ ተጋጣሚያቸውን ወደ ግብ ክልሉ መግፋት ችለው ነበር። ባዬ ገዛኸኝ ወደ መስመር እየወጣ ለመፍጠር ከሚሞክራቸው ዕድሎች ውጪ ግን ቡድኑ በሚያስፈልገው መጠን ሰብሮ እንዳይገባ የሰበታ ተጫዋቾች በቁጥር በርከት ብለው ክፍተቶችን ሲደፍኑ ቆይተዋል። ያለከባድ ሙከራ በቀጠለው ጨዋታ ለግብ መቅረብ የቻሉት ግን ሰበታዎች ነበሩ። 41ኛው ደቂቃ ላይ ከሳሙኤል ሳሊሶ ወደ ግራ ያደላ ቅጣት ምት በሆሳዕናዎች ሲመለስ ሰበታዎች ከግቡ አፋፍ ላይ ያለቀለት ዕድል ቢያድገኙም ዘካሪያስ በማይታመን መልኩ ወደ ላይ ልኮታል።


ከዕረፍት መልስም ጨዋታው በተመሳሳይ አኳኋን የቀጠለ ነበር። ሆኖም ሳምሶን ጥላሁን ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ዓለማየሁ ሙለታ ሳጥን ውስጥ በእጅ በመንካቱ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ሳምሶን 55ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አድርጎታል። ከግቡ በኋላም የሆሳዕና ማጥቃት የተሻለ አይን የሚገባ ነበር። በተለይም 64ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አርፌጮ ከግራ በተሻጋሪ ኳስ ብርሀኑ በቀለ ደግሞ በቀኝ ውስጥ ድረስ ሰብሮ በመግባት ጥሩ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር። ሰበታዎችም በበኩላቸው ወደ ጨዋታው ምት ተመልሰው በማጥቃት ለመጫወት ቅያሪዎችን በማድረግ ጭምር ጫና ለማሳደር ጥረዋል።


በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሰበታ ከተማዎች ከሜዳቸው በመውጣት በተሻለ ሁኔታ መንቀሳቀስ ችለዋል። ሆኖም ፍፁም ገብረማሪያም 85ኛው ደቂቃ ላይ ካደረገው መከራ ውጪ ሌላ ዕድል ሳይፈጥሩ ለአራተኛ ተከታታይ ሽንፈት ተዳርገዋል። ሀዲያ ሆሳዕና ከጨዋታው ባገኘው ሦስት ነጥብ ከ12 ወደ 7ኛ ደረጃ ሲመጣ ሰበታ ከተማ ጅማ በዚህ ሳምንት ነጥብ ካገኘ የሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የመቀመጥ ስጋት ተጋርጦበታል።