ኢትዮጵያዊቷ አጥቂ በታህሳስ ወር ወደ አሜሪካ ታመራለች

ኢትዮጵያዊ አጥቂ ሎዛ አበራ በሦስት የአሜሪካ ክለቦች ውስጥ የሙከራ ጊዜን ለማሳለፍ በታህሳስ ወር መጀመሪያ ወደ አሜሪካ ታቀናለች።

በኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ ላይ ስሟን በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት እና በምርጥ ተጫዋችነት ዝርዝር ውስጥ ራሷን በጉልህ ያስፈረችው አጥቂዋ ሎዛ አበራ ወደ አሜሪካ ልታመራ መሆኑን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። እግር ኳስን በ2004 በሀዋሳ ከተማ ከጀመረች በኋላ በመቀጠል በደደቢት ፣ አዳማ ከተማ እንዲሁም ወደ ስዊዲን አምርታ በሙከራ በመጨረሻም ደግሞ ለማልታው ክለብ ቢርኪርካራ በመፈረም የተሳካ ቆይታን አድርጋ ነበር ከሦስት ዓመታት በፊት ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ክለብ ውስጥ በአጥቂነት እና በአምበልነት ክለቡን እያገለገለች አሁንም ትገኛለች።

ከአንድ ዓመት በፊት በታንዛኒያው ሲምባ ክለብ ብትፈልግም በንግድ ባንክ ውሏ ውስጥ የውጪ ዕድል ካገኘሽ ክለቡን ትለቂያለሽ የሚል ስምምነት አለመኖሩን ተከትሎ የተገኘውን ዕድል ያልተጠቀመችው እንስቷ ከወራት በፊት ግን በክለቧ ንግድ ባንክ ውሏን ለአንድ ዓመት ስታራዝም የውጪ ዕድል ካገኘች ክለቡ እንደሚለቃት በገባችው ውል መሠረት ተጫዋቿ በታህሳስ ወር መጀመሪያ በአሜሪካ የሙከራ ዕድልን ማግኘት በመቻሏ ወደ ስፍራው እንደምታመራ ሶከር ኢትዮጵያ የደረሳት መረጃ አመላክቷል።

አሜሪካ በሚገኘው በኢትዮጵያዊው የተጫዋቾች ወኪል መዝሙረዳዊት መኩሪያ አማካኝነት ለሦስት ወራት በአሜሪካ ለሦስት የተለያዩ ክለቦች የሙከራ ጊዜን የምታሳልፈዋ የወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የንግድ ባንክ አጥቂ ሎዛ አበራ የሙከራ ጊዜዋን ካጠናቀቀች በይፋ ከሦስቱ ለአንዱ ክለብ ፊርማዋን የምታኖር ከሆነ በዛው የእግር ኳስ ህይወቷን የምትቀጥል ሲሆን ይህ ካልሆነ ግን ዳግም ወደ ሀገሯ ተመልሳ በስምምነቱ መሠረት በንግድ ባንክ የምትጫወትም ይሆናል። በተጨማሪነት የንግድ ባንኩ አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ለዝግጅት ክፍላችን እንዳሉት ከሆነ  በስድስት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ቀጣይ ጨዋታዎች ላይ ክለቧን ካገለገለች በኋላ ወደ ስፍራው እንደምታመራም ነግረውናል።