አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል

👉 “በሜዳችን ብንጫወት ይህ አጨዋወት ይበልጥ ውጤታማ እንደሚሆን መታወቅ አለበት”

👉 “ጥያቄዎችን በተደጋጋሚ በተጨባጭ አቅርበናል ግን ፊፋ ጨዋታው እንዲቋረጥ አይፈልግም የሚል ድርቅ ያለ መልስ ነው የተሰጠን”

👉 “ቡርኪናፋሶ ጋር የማይደበቅ የደረጃ እና የአቅም ልዩነት አለን”

👉 “ከ 23 ዓመት በታች ያሉ ተጫዋቾችን መልምሎ እንደ ‘ሻዶ ቲም’ የማዘጋጀት ሀሳብ አለኝ”

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሞሮኮ ላይ ከሴራሊዮን እና ከቡርኪናፋሶ ጋር ባደረጋቸው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ዙሪያ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል።

ስለ ዓየር ንብረቱ እና ስለ ጨዋታዎቹ…

“በዚህ ዘመን የዓየር ንብረቱ ምን እንደሚመስል ለመገመት ይቻላል። ነገር ግን የዛን ቀን ዓየሩ ሂውሚዲቲው ቶሎ ቶሎ ይቀያየር ነበር። የነበረውን ቀዝቃዛ ዓየር እናውቅ ነበር ሂውሚዲቲውም እስከ ዘጠና የሚደርስበት ጊዜ ነበር እንደገናም መልሶ ይወርዳል ፤ ጨዋታው ላይ እንደታየው ማለት ነው። ጥያቄዎችን በተደጋጋሚ በተጨባጭ አቅርበናል ግን ፊፋ ጨዋታው እንዲቋረጥ አይፈልግም የሚል ድርቅ ያለ መልስ ነው የተሰጠን። ሁለተኛው ጨዋታ ላይ ቡርኪናፋሶ ጋር የማይደበቅ የደረጃ እና የአቅም ልዩነት አለን ፤ በፊፋ ደረጃ እንኳን የ 90 ደረጃዎች ያህል ልዩነት አለን። ይህ የስነልቦና ጫና አይፈጥርም ማለት አይቻልም ይህንን ለማስወገድ ግን ብዙ ሥራዎችን ቁጭ ብለን በመወያየት እና በየ ልምምዱ ብነግራቸውም የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ማምጣት አልተቻለም።  በተለይም በመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች ግብ ካስተናገድን በኋላ የጠበቅነውን ያህል አልነበርንም። በጥሩ ዝግጅት ገብተን ነበር ግብ እስኪቆጠርብን በብቃት ተቆጣጥረነው ነበር። ከተጋጣሚያችን በተሻለም አጥቅተናል በተለይም በመልሶ ማጥቃት ብዙ ኳሶች ነጥቀን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመግባት አጨራረሱ ጥሩ ባይሆንም ግብ የምናስቆጥርበት አጋጣሚ መፍጠር ችለን ነበር። አንድ ለአንድ ላይ የማሸነፍ ብቃታችን ፣  የመስመር አጠቃቀማችን ፣ የሚገጩ ኳሶች ላይ ብዙም አይደለንም። በተጨባጭ በእኛ ቡድን ውስጥ እነዚህ ብቃቶች የሉንም። በእዚህ ምክንያትም ግብ ለማስቆጠር አስቸጋሪ ነበር።

ስለ አቀራረባቸው…

“እኛ ለመከላከል አልገባንም ፤ ያለውን ደረጃችንን እናውቀዋለን። ዝግጅታችን እነርሱ በግል ብዙ ነገር ቢኖራቸውም እኛ እንደ ቡድን ተንቀሳቅሰን አንድ ነገር መሥራት እንችላለን የሚል ነበር። አቀራረባችንም ለማሸነፍ ነበር። በዛ መንገድ ነበር የሄድነው ነገር ግን በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሦስት ግቦች ተቆጠሩብን። ይህም የሆነው በግል በተፈጠሩ ቀላል ስህተቶች ነው እንጂ እንደ ቡድን ብልጫ ወስደውብን አልነበረም። በግል የሚፈጠሩ ስህተቶችን ደግሞ ለማረም አይቸግርም እንደ ቡድን ተበልጠን ሳንደራጅ ቀርተን ብንሸነፍ ምናልባት ተስፋ ሊያስቆርጥ ይችላል። ይሄ ግን በዛ መልኩ አልነበረም።”

ከጨዋታ በፊት እና በኋላ ቃለ መጠይቆች ስላለመታየታቸው…

“ከጨዋታው በፊት አልመጡም ፤ በእነርሱ በኩል ጠይቀዋቸው ከሆነም አላውቅም። ሁለቱም ጨዋታ ላይ ከጨዋታው በኋላ አስተያየት ሰጥቻለሁ። ተደራሽ መሆን አለመሆኑ ላይ አስተዳደራዊ ጉዳይ ነው የሚሆነው እኔ ግን ሰጥቻለሁ።”

ስላደረጉት የአጨዋወት ለውጥ…

“የአጨዋወት ለውጥ አድርገናል ፤ ሌሎች አማራጮችን መውሰድም አስፈላጊ ስላልሆነ። አያዋጣንም! ይሄንን የአጨዋወት መንገድ የምንከተለው ስለሚያዋጣን ነው። በእርግጥ ሁሉም ሊያውቀው የሚገባ ነገር ቢኖር የሜዳ ተጠቃሚ አይደለንም። በሜዳችን ብንጫወት ይህ አጨዋወት ይበልጥ ውጤታማ እንደሚሆን መታወቅ አለበት የዓየር ንብረት ፣ የደጋፊ ፣ የዳኛ በእኛ ላይ ተፅዕኖ አለመፍጠርን የመሳሰሉ ጥቅሞች ነበሩ። ከዚህ አኳያ በሁለቱ ጨዋታዎች ላይ በትንሹ አራት ነጥብ የምናገኝበት ጨዋታ ነበር። ይህ አጨዋወታችን በተጫዋቾቹ ላይ የፈጠረው ግርታ የለም።”

ስለ ግቦች አጨራረስ…

“ብዙዎቻችሁ የምታውቁት ይመስለኛል አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ብዙ 9 ቁጥሮች አሉ ለማለት እኔ ለእራሴ የማያስደፍረኝ ነው። ግን ያሉትን 9 ቁጥሮች ወደፊት ወስደን ማየት ይጠበቅብናል። ሌላ አማራጭ መውሰድ እንደሚጠበቅብኝ አስባለሁ። እዛ ቦታ ላይ ሌላ ሰው ማለማመድ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ያላቸው ቴክኒካል ካፓሲቲ ፣ የፊኒሺንግ አቅማቸው እና ታክቲካል አዌርነሳቸው በየ ክለቡ ያሉትን 9 ቁጥሮች ስናያቸው ለብሔራዊ ቡድን በጣም በጣም አስቸጋሪ ነው። እንደ ሀሳብ የያዝነው እንደ ቡድን ተንቀሳቅሰን ሌላ ዘጠኝ ቁጥር መፍጠር ካልሆነ እንደዚህ ዓይነት ኳሊቲዎች እየጠፉ ነው ወደፊት የሁላችንም ጥረት ይጠበቃል።”

ስለ ከነዓን ማርክነህ…

“አንዳንድ ጊዜ እንደ ተጫዋቹ ማሰብ አይቻልም ፤ ምን እንዳሰበ እሱ ነው የሚያውቀው። ነገር ግን ማድረግ የሚጠበቅበት ነገር ቀድሞ ይነገረዋል ፤ የአቅሙን ነው ማድረግ የሚችለው። እዛ አካባቢ የተገኙ ነገሮችን መጠቀሙ አንድ ነገር ሆኖ አልተጠቀመም ነገር ግን እሱን የማያበረታቱ ነገሮችን መጠቀም የለብንም ብዬ አስባለሁ። ይህ ልጅ ጥሩ ነገሮች ስላሉት ወደፊት ይማራል ብዬ ነው የማስበው።”

ስለ አሰልጣኝ ቡድን አባላት የቁጥር ማነስ…

“ጠበብ እንደሆነ እናውቃለን። የጊዜ ማነስ ፣ ችኮላ እና ያልተስለካከሉ ነገሮች ነበሩ። ወደፊት የአሰልጣኝ ቡድን አባላትን ሰፋ ለማድረግ እንሠራለን ጊዜ ስለሚኖረን። አንድ ለውጥ ለማምጣት የግድ ብዙ ነገሮችን ማየት አለብን በተለይ የትውልዱ አንድ ቦታ ላይ የመቆም ነገር ይታያል እና ወጣቶችን የምናመጣበት መንገድም አንድ ነገር ነው። ለፌዴሬሽናችን በፕላን ደረጃ የማቀርበው ነገር ይኖራል። ከ 23 ዓመት በታች ያሉ ተጫዋቾችን መልምሎ የተወሰነ እንደ ሻዶ ቲም የማዘጋጀት ሀሳብ አለኝ። የፕሪሚየር ሊጉ ወድድር አንድ ቦታ ላይ ስለሚደረግ እነዚህን በየ ክለቡ የሚመረጡ ልጆች በሣምንት አንዴ እያገኙ ለማብቃት ሰብስበን በተደጋጋሚ እያሠራን ብሔራዊ ቡድኑን የመተካት ሥራ ያስፈልገናል።”