ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የ1ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን በአራት ጨዋታዎች ዛሬ ቀጥሎ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ድሬዳዋ ድል ሲቀናቸው ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ተጠናቀዋል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት አራት ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ የዕለቱ ቀዳሚ የነበረው ጨዋታ የይርጋጨፌ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ነበር። የቅዱስ ጊዮርጊስ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ባየንበት እና የይርጋጨፌ ቡና ረጃጅም ኳሱን በሙሉ የጨዋታ ደቂቃ በታዘብንበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከሙከራዎች ይልቅ አብዛኞቹ እንቅስቃሴዎች ኳስን ማንሸራሸር ላይ ያተኮሩ ሆነው ታይተዋል። ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ 51ኛው ደቂቃ ምህረት ቶንጆ ቅዱስ ጊዮርጊስን መሪ ብታደርግም 76ኛው ደቂቃ ላይ የይርጋጨፌዋ ተከላካይ ናዝሬት ሰይፈ ከቀኝ የቅዱስ ጊዮርጊስ የሜዳ ክልል በቀጥታ ወደ ጎል የመታችው ኳስ ከመረብ አርፎ ጨዋታው 1ለ1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በመቀጠል የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ቦሌ ክፍለ ከተማን ከ መቻል አገናኝቶ ያለ ጎል በመጨረሻም ሊቋጭ ችሏል። የቦሌ ክፍለ ከተማ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ባየንበት በዚህ ጨዋታ በተለይ ቡድኑ ኳስን በማንሸራሸር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ በጥሩ ፍሰት መድረስ ቢችሉም የመጨረሻ ውሳኔያቸው ደካማ በመሆኑ ቡድኑ ያገኛቸውን ሁለት ዕድሎች በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ከጎል ጋር ማገናኘት ሳይችሉ ቀርተዋል። መቻሎች ለመጫወት በሚያደርጉት የረጃጅም ኳስ አጠቃቀም በአጥቂዋ ንግስት በቀለ ቀዳሚ የሆኑበትን ሙከራ አድርገዋል። 14ኛው ደቂቃ ላይ ንግስት በቀለ ግልፅ አጋጣሚን አግኝታ ሊንጎ ኡማን ከያዘችባት በኋላ ባሉ ቀሪ ደቂቃዎች የተሻሉ የነበሩት ቦሌዎች ሆነዋል።

በአጋማሹም 25ኛው ደቂቃ ላይ በአሰልጣኝ ቻለው ለሜቻ የሚመራው ቦሌ ክፍለ ከተማ በትግስት ወርቄ አማካኝነት ሁለት ፍፁም ያለቀላቸውን ዕድሎችን አግኝተው ወደ ግብነት መለወጥ ሳይችሉ የቀሩበትን ሁነት ተመልክተናል። ከዕረፍት በፊት የነበረው ሳቢነት ወርዶ በሁለተኛው አጋማሽ ዳግም የተመለሰው የቡድኖቹ ጨዋታ ከተደረጉ ሙከራዎች ይልቅ የመቻሉ አሰልጣኝ ስለሺ ገመቹ  የተጋጣሚን ተጫዋች በመዝለፉ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣበት አጋጣሚ ብቻ ትኩረት የምትስብ ሆና በመጨረሻም ጨዋታው ያለ ጎል ተቋጭቷል።

ጥሩ ፉክክርን ያሳየን የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና የአዲስ አዳጊው ሀምበሪቾ ጨዋታ ከቀትር መልስ 8፡00 ሲል ተጀምሯል። አጀማመራቸውን በሽግግር የጨዋታ መንገድ የአጥቂ ክፍላቸውን ባገናኘ መልኩ ለመንቀሳቀስ የሞከሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከጎል ጋር የተገናኙት ገና በ4ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ስራ ይርዳው ወደ ቀኝ መሬት ለመሬት የደረሳትን ኳስ ወደ ውስጥ ስታሻግር ምርቃት ፈለቀ ጎል በማድረግ ቡድኗን ወደ መሪነት አሸጋግራለች። ጎል ካስቆጠሩ በኋላ በመጠኑም ቢሆን የማጥቃት ፍላጎታቸው ቀዝቀዝ ብሎ ይታይ የነበሩት ኤሌክትሪኮች ስራ ይርዳውን በየምስራች ላቀው በፍጥነት ቅያሪን በማድረግ የማጥቃት ሀይላቸውን ከፍ ለማድረግ ሲጥሩ ተስተውሏል። የምስራች ላቀው ተቀይራ ከገባች በኋላ በድግግሞሽ ለተጨማሪ ጎሎች ሙከራን ስታደርግ የተመለከትን ሲሆን ሲሳይ ገብረዋህድም ያለቀለትን የግብ አጋጣሚ አጋማሹ ሊገባደድ ሲል አግኝታ መጠቀም ሳትችል ቀርታለች።

ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ሲመለስ ሀምበሪቾዎቾ በተሻለ መነቃቃት ወደ ሜዳ ገብተው ለኤሌክትሪክ ፈታኝ ለመሆን ቢሞክሩም የሚታይባቸው የስልነት ችግር ተጨማሪ ጎልን በተቃራኒው እንዲያስተናግዱ አድርጓቸዋል። 

75ኛው ደቂቃ ላይ ከንግስት አስረስ ያገኘችውን ኳስ የምስራች ላቀው ለቡድኗ ሁለተኛ ጎል ስታደርግ ከሦስት ደቂቃ መልስ ደግሞ የሀምበሪቾ ተከላካዮች በቅብብል ወቅት የፈጠሩትን ስህተት ተጠቅማ ፀጋነሽ ወራና ተጨማሪ ግብ ልታስገኝ ችላለች። ሀምበሪቾዎች 80ኛው ደቂቃ ላይ በዘሪቱ ብርሀኑ አማካኝነት ከባዶ መሸነፍ ያልዳኑበትን ግብ ካገኙ በኋላ ጨዋታው በኤሌክትሪክ 3ለ1 አሸናፊነት ተደምድሟል።

የሳምንቱ የማሳረጊያ ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ አሸናፊነት ፍፃሜውን አድርጓል። ድሬዳዋን ከአዳማ ከተማ ባገናኘው ጨዋታ ተመጣጣኝ የሚመስልን አቀራረብ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ብናይም የኋላ ኋላ ግን የድሬዳዋ ከተማን የተሻለ የጨዋታ ሂደት ልናስተውል ችለናል። በመጀመሪያው አጋማሽ አዳማ ከተማዎች በተለይ በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ጥሩ የሚባሉ ዕድሎችን በይታገሱ ተገኝወርቅ አማካኝነት አግኝተው መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። 11ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው ሲደርስ ቁምነገር ካሳ ከቀኝ ወደ ግብ ያቀበለቻትን ኳስ ቃልኪዳን ጥላሁን ከመረው አዋህዳ ቡድኗን ቀዳሚ አድርጋለች።

ከዕረፍት መልስ በሁለቱ መስመሮች አጥቅቶ በመጫወት ግቦችን ለማግኘት አሁንም የታተሩት ድሬዳዋዎች 53ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ጎልን ወደ ካዝናቸው ከተዋልተ። ሊዲያ ጌትነት ከቅጣት ምት ያሻማችውን ኳስ ቃልኪዳን ተስፋዬ ነካ ብቻ በማድረግ ለቡድኗ ሁለተኛ ጎልን አስገኝታለች። ወደ ጨዋታ ለመመለስ አጨዋወታቸውን ከቆሙ ኳሶች እና ከርቀት በሚደረጉ ሙከራዎች ያደረጉት አዳማ ከተማዎች በሳባ ሃይለሚካኤል አማካኝነት ከቅጣት ምት ቆንጆ ጎልን ቢያስቆጥሩም መደበኛውን የጨዋታ ደቂቃ ተጠናቆ በተሰጠው የጭማሪ ደቂቃ ድሬዎች ትዕግስት ዘውዴ ከመሐል ሜዳ የግብ ጠባቂዋን መውጣት ተመልክታ እጅግ ማራኪ ጎልን በቀድሞው ቡድኗ ላይ በማስቆጠር በመጨረሻም ጨዋታው በድሬዳዋ ከተማ 3ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።