የኢትዮጵያ ዋንጫ | የሁለተኛ ዙር የመጨረሻ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ዋንጫ ሁለተኛ ዙር ዛሬ በተከናወኑ ጨዋታዎች ተገባዶ 16ቱ አላፊ ቡድኖች ሙሉ ለሙሉ ተለይተዋል።

የ07:00 ጨዋታዎች

በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የሀዲያ ሆሳዕና እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታ ሲደረግ በመጀመሪያው አጋማሽ ንግድ ባንኮች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ቅድሚያ ሰጥተው ሲቀርቡ በአንጻሩ ሀዲያዎች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። ሆኖም ግን በአጋማሹ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ይህ ነው የሚባል ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳይደረግ ወደ ዕረፍት አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስም ጨዋታው በተመሳሳይ አጨዋወት ሲቀጥል ግለቱ ግን በመጠኑ ተሻሽሏል። ሁለቱም ቡድኖች የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ጨዋታውን ለማሸነፍ ጠንካራ እንቅስቃሴ ማድረግ ሲችሉ 59ኛው ደቂቃ ላይ ነብሮቹ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ብሩክ ማርቆስ በድንቅ ዕይታ ያሾለከለትን ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ ላይ ሆኖ የተቆጣጠረው ተመስገን ብርሃኑ በተረጋጋ እና ብስለት በተሞላበት አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል። ንግድ ባንኮችም ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ፍለጋ መታተራቸውን ቀጥለው በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ተደራጅተው ለመግባት በመቸገራቸው የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። ጨዋታውም በሀዲያ ሆሳዕና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በአዳማ ዩኒቨርስቲ ሜዳ በተካሄደው የሦስተኛ ቀን የኢትዮጵያ ዋንጫ የመጀመርያ ጨዋታ ነገሌ አርሲ ከስልጤ ወራቤ አገናኝቶ በነገሌ አርሲ አሸናፊነት ተጠናቋል። ገና ከጨዋታው ጅማሬ አንስተው ጫና ፈጥረው የተጫወቱት ነገሌዎች በ20ኛው ደቂቃ ግዙፉ አጥቂ ታምራት ኢያሱ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በጥሩ አጨራረስ ወደ ጎልነት በመቀየር ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል። እንደወሰዱት ብልጫ ጎል ማስቆጠር የሚገባቸው ነገሌዎች ብዙም ሳይቆይ በ30ኛው ደቂቃ ጀቤሳ ሚኤሳ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ የነጠቀው ኳስ ተጫዋች በመቀነስ ግሩም ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። እንደ ቡድን ያልተደራጀው እና የሚበላሹ ኳሶች የበዙበት ስልጤ ወራቤ በአጋማሹ እጅግ ለጎል የቀረበ ሙከራ ማቲያስ ኤልያስ አማካኝነት ከመፍጠሩ ውጭ የተሳካ እንቅስቃሴ ማድረግ አልቻሉም ነበር።

ከዕረፍት መልስ በአንፃራዊነት በተሻለ ለመንቀሳቀስ የሞከሩት ወራቤዎች ተቀይሮ በገባው ምስግናው መላኩ ያገኘውን ኳስ ወደ ጎል ቢመታውም የግቡ ቋሚ የመለሰበት ጥሩ አጋጣሞ ነበር። ውጤቱን ለማስጠበቅ በጥንቃቄ እየተከላከሉ በሚገኙ አጋጣሚዎች ወደ ፊት ይሄዱ የነበሩት ነገሌዎች በመጨረሻው ደቂቃ ሰለሞን ገመቹ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በነገሌ አርሲ 3-0 አሸናፊነት ተገባዷል።

የ09:30 ጨዋታዎች

አዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ በሁለተኛው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ እና ቤንች ማጂ ቡና ሲገናኙ ሀይቆቹ ጨዋታው በተጀመረ በ2ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥረዋል። ሙጅብ ቃሲም በድንቅ ዕይታ ከፍ አድርጎ (ቺፕ) የሰጠውን ኳስ የተቆጣጠረው ዓሊ ሱሌይማን ወደ ሳጥኑ ጠርዝ እየገፋ በመውሰድ በግሩም አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል። ቤንች ማጂዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በፈጣን ሽግግር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲቸገሩ በቀጥተኛ በተለይም ዓሊ ሱሌይማንን ትኩረት ባደረጉ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ሀዋሳዎች አጋማሹ ሊጠናቀቅ በተጨመረው አንድ የባከነ ደቂቃ ውስጥ ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። አቤኔዜር ኦቴ የሰነጠቀለትን ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያገኘው ዓሊ ሱሌይማን አስቆጥሮት ለራሱም ሆነ ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ አድርጎታል።

ከዕረፍት መልስ አቦሎቹ 47ኛው ደቂቃ ላይ ወንድማገኝ ኬራ የተከላካይ ስህተት ተጠቅሞ በተረጋጋ አጨራረስ ባስቆጠረው ግብ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ በአራት ደቂቃዎች ልዩነት ግን በሙጅብ ቃሲም አማካኝነት ግብ ሊቆጠርባቸው ተቃርቦ ግብ ጠባቂው ናትናኤል ተፈሪ በእግሩ መልሶበታል። ቤንች ማጂዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ በፈጣን ሽግግሮች ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ማማተራቸውን ቀጥለው 60ኛው ደቂቃ ላይም በያሬድ ወንድማገኝ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ ሙከራ አድርገው በግብ ጠባቂው ተመልሶባቸዋል። በቀሪ ደቂቃዎችም በሁለቱም በኩል ተጠቃሽ የሆነ ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳይደረግ ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በአዳማ የቀጠለው የኢትዮጵያ ዋንጫ ሁለቱን የከፍተኛ ሊግ ቡድኖች ቢሸፍቱ ከተማና ሀላባ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በመለያ ምት ቢሸፍቱ ከተማ አሸንፏል። ገና በጨዋታው ጅማሬ ከሳጥን ውጭ የተገኘውን ቅጣት ምት የቢሸፍቱ የመስመር አጥቂ ዳዊት ሽፈራው በቀጥታ ወደ ጎልነት በመምታ ቡድኑን መሪ አድርጓል። ኳሱን በመቆጣጠር እና በሁሉም የሜዳ ክፍል በማጥቃት ረገድ የተሻሉ የነበሩት ሀላባዎች ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጥቃት መሰንዘር የቀጠሉት ሀላባዎች ከፊት ያሉት አጥቂዎች ንቁ ባለመሆን ዕድሎችን ሲያመክኑ ውለዋል። ጎል ካገኙ በኋላ አፈግፍገው ወደ ፊት ያልሄዱት ቢሸፍቱዎች ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት እስማኤል ጌታሁን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በሁለተኛው አጋማሽ የተጨዋቾች ቅያሪ በማድረግ የማጥቃት ክፍተታቸውን ለማረም የሞከሩት ሀላባዎች በተመሳሳይ ያገኙትን አጋጣሚዎች ለማመን በሚከብድ ኳሶችን ማምከናቸውን ቢቀጥሉም በስተመጨረሻም የጥረታቸው ውጤት በ79ኛው ደቂቃ በጥሩ ቅብብል ያገኘውን ኳስ ጌታቸው ኤርትሮ ቡድኑን አቻ አድርጓል። ጨዋታውም በአንድ አቻ መጠናቀቁን ተከትሎ ወደ መለያ ምት አምርቶ ቢሸፍቱ ከተማ 5-4 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉን አረጋግጧል።

በዚህ መልኩ የኢትዮጵያ ዋንጫ ሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ዛሬን ጨምሮ ባለፉት ሁለት ቀናት ተከናውነው 16ቱ አላፊ ቡድኖች የተለዩ ሲሆን ከታህሳስ 12-14 በሚከናወኑት የሦስተኛ ዙር ፍልሚያዎች ቀጣዮቹ ጨዋታዎች እንደሚደረጉ ይጠበቃል።

ሦስተኛው ዙር ጨዋታዎች

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሻሸመኔ ከተማ
ባህር ዳር ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ
ደብረብርሀን ከተማ ከ ፋሲል ከነማ
ኮልፌ ቀራኒዮ ከ ኢትዮጵያ ቡና
ነጌሌ አርሲ ከ ኢትዮጵያ መድን
ሀዲያ ሆሳዕና ከ ወላይታ ድቻ
ቢሾፍቱ ከተማ ከ አዳማ ከተማ
ሀዋሳ ከተማ ከ መቻል