​ሪፖርት | ሲዳማ ቡና በደረጃ ሰንጠረዡ ሽቅብ የወጣበትን ድል አግኝቷል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የ12ኛ ሳምንት የማሳረጊያ መርሐ-ግብር የሆነው የሲዳማ ቡና እና ጅማ አባጅፋር ጨዋታ በሲዳማ ቡና አሸናፊነት ተገባዷል።

በአሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚመሩት ጅማ አባጅፋሮች ሁለተኛ ተከታታይ ድላቸውን ካገኙበት የሀዲያ ሆሳዕናው ጨዋታ አንድም ተጫዋች ሳይቀይሩ የዛሬውን ጨዋታ ቀርበዋል። ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ እየመሩ አቻ ከተለያዩበት የአርባምንጩ ጨዋታ ሁለት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ጊት ጋትኩት እና ብሩክ ሙሉጌታን በቴዎድሮስ በቀለ እና ዳዊት ተፈራ ለውጠው ጨዋታውን ጀምረዋል።

ፈጣን እንቅስቃሴ ማስመልከት የጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ቶሎ ቶሎ ግብ ጋር አጋጣሚ ሲፈጠርበት ነበር። በአንፃራዊነት ከኳስ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ የሞከሩት ሲዳማዎችም በ8ኛው ደቂቃ ሳይታሰብ መሪ ሊሆኑ ነበር። በዚህም መሀሪ መና ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ የግብ ዘቡ ዮሐንስ በዛብህ በእግር አፀዳለው ብሎ ስህተት ፈፅሞ ግብ ሊቆጠር ነበር። ፈጣን የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ለመከተል የጣሩት ጅማ አባጅፋሮች ደግሞ በ14ኛው ደቂቃ በላይ አባይነህ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመታው ኳስ ቀዳሚ ለመሆን ሞክረዋል።

የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው ለማድረግ የሞከሩት ሲዳማዎች በ18ኛው ደቂቃ በይገዙ ቦጋለ አማካኝነት ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም የግቡ ባለቤት ይገዙ የጅማን ተጫዋቾች የኳስ ቅብብል ስህተት ተጠቅሞ ያገኘውን ኳስ ለዳዊት ተፈራ አቀብሎ ቦታ ከያዘ በኋላ የዳዊትን እጅግ ድንቅ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ በመቀበል የዩሐንስ በዛብህን መረብ አግኝቷል። አካላዊ ጉሽሚያዎች የበዙበት ጨዋታው ቶሎ ቶሎ በዳኛው ፊሽካ ሲቆራረጥ ነበር። በ24ኛው ደቂቃም መሐመድኑር ሙሉዓለም ላይ በሰራው ጥፋት ተጫዋቹ ጉዳት አስተናግዶ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ኳሱን የግላቸው ያደረጉት ጅማዎች በፍጥነት የሲዳማን ግብ ለመጎብኘት ሲታትሩ ነበር። ነገርግን እምብዛም ፍሬያማ ሲሆኑ አልነበረም። በቀጣይ ደቂቃዎች እንደ አጀማመሩ ያልሆነው ፍልሚያውም የጠራ የግብ ማግባት አጋጣሚ ሳይፈጠርበት ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛውን አጋማሽ በጥሩ ተነሳሽነት የቀረቡት ጅማ አባጅፋሮች አቻ ለመሆን በሚጥሩበት ሰዓት ሲዳማዎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት የግብ ክልላቸው ሄደው የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። በዚህም ኢያሱ የግቡ ባለቤት ይገዙ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ዳዊት ተፈራ በግራ እግሩ መረብ ላይ አሳርፎታል።

የጅማዎች ግብ ለማግባት ነቅሎ መውጣት የጠቀማቸው ሲዳማዎች በ54ኛው ደቂቃ በይገዙ አማካኝነት መሪነታቸውን ወደ ሦስት ሊያሳድጉ ነበር። ከሁከት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ፈጣኑ አጥቂ መሐመድኑር ከቀኝ መስመር ወደ ግብ የላከው ኳስ ጅማን ወደ ጨዋታው ሊመልስ የተቃረበ ነበር። 

ጨዋታው ሰባኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ሦስት ነጥብ ለማግኘት ከደቂቃ በፊት ሦስት ተጫዋቾችን የቀየሩት ጅማዎች ሦስተኛ ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። በዚህም ሀብታሙ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ለመጠቀም ጥሮ ተከላካዩ ወንድማገኝን አልፎ ወደ ግብ ቢመታውም ግብ ጠባቂው ዮሐንስ አድኖበታል። ያላቸውን ሀይል አሟጠው ለመጠቀም የጣሩት ጅማዎች በ84ኛው ደቂቃ ባገኙት የቅጣት ምት ቀይረው ባስገቡት አድናን ረሻድ አማካኝነት የማስተዛዘኛ ጎል ለማግኘት ሞክረው መክኖባቸዋል። ሲዳማዎች ደግሞ ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው የማሳረጊያውን ጎል በፈጣን ሽግግር ሊያገኙ ተቃርበው ወጥቶባቸዋል። በጭማሪው ደቂቃ ደግሞ ቴዎድሮስ እጅግ ጥሩ ኳስ ሳጥን ውስጥ ተገኝቶ ሞክሮ ነበር። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት ሁለት ለምንም በሆነ ውጤት ተጠናቋል።                               

ሲዳማ ቡና ድሉን ተከትሎ ነጥቡን 18 በማድረስ ከነበረበት 10ኛ ደረጃ  ወደ 5ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ሦስት ነጥብ ያስረከበው ጅማ አባጅፋር ደግሞ በ7 ነጥቦች የሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቀምጦ ቀጥሏል።