ጋቦን 2017፡ ትላንት በተደረጉ ጨዋታዎች ሳኦ ቶሜ እና ታንዛያ ድል ቀንቷቸዋል 

ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚደረጉት የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ትላንት ሲጀመሩ ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንስፔ በተጨማሪ ደቂቃ በተቆጠሩ ሁለት ግቦች ታግዛ የሰሜን አፍሪካዋን ሃገር ሊቢያ ስታንፍ ታንዛኒያ ኒጃሚና ላይ ቻድን 1-0 አሸንፋለች፡፡

በምድብ ስድሰት ሳኦ ቶሜ ላይ በተደረገ ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ከኃላ በመነሳት ሊቢያን አሸንፈዋል፡፡ ፋይሰል አልባድሪ ሊቢያን በ24ኛው ደቂቃ ቀዳሚ ቢያደርግም ሳኦቶሜዎች በጨዋታው መገባደጃ ላይ ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ታግዘው ሶስት ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል፡፡ የሊቢያው ተከላካይ ኤልትሪቢ በራሱ ግብ ላይ ሲያስቆጥር ዶስ ሳንቶስ የድሏን ግብ አክሏል፡፡ ድሉን ተከትሎ ሳኦ ቶሜ ኬፕ ቬርዴን እና ሞሮኮን ተከተላ በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ሆናለች፡፡

በምድብ 5 ኬንያ በጊኒ ቢሳው 1-0 ተረትታለች፡፡ ኢድሪሳ ካማራ የጨዋታውን ብቸኛ ግብ በ18ኛው ደቂቃ የሙሳ መሃመድን ስህተት ተጠቅሞ አስቆጥሯል፡፡ አዲስ የተሾ ሙት የኬንያው አሰልጣኝ ስታንሊ ኦኩምቢ ሁለት የግራ መስመር ተከላካዮችን በቡድናቸው ቢያካትቱም የመሃል ተከላካይ የሆነው ሙሳን በግራ መስመር ተከላካይነት ማስገባታቸው ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡

በዚሁ ምድብ በተደረገ ሌላ ጨዋታ ዛምቢያ ከኮንጎ ብራዛቪል 1-1 ተለያይታለች፡፡ የኤሲ ሊዮፓርድሱ አጥቂ ዊንስተን ካሌንጎ ቺፖሎፖሎዎቹን ቀዳሚ ሲያደርግ ጆርዳን ማሴንጎ ለኮንጎ የአቻነቷን ግብ አስቆጥሯል፡፡ ኮንጎ እና ዛምቢያ ምድቡን በአምስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ይመራሉ፡፡

አዲሱ የፊፋ ፕሬዝደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በጁባ ስታዲየም ተገኝተው በተከታተሉት የምድብ 3 ጨዋታ ቤኒን ደቡብ ሱዳንን 2-1 አሸንፋለች፡፡ ለቤኒን የድል ግቦቹን ስቴፈን ሴሴኞ እና ስቲቭ ሞኒ በስማቸው አስመዝግበዋል፡፡ ቤንኒ የምድብ ሶስትን በአምስት ነጥብ መምራት ጀምራለች፡፡

ታንዛኒያ የአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ተስፋዋን ያለመለመችበትን ውጤት ከኒጃሚና ይዛ ተመልሳች፡፡ የ2015 በአፍሪካ የሚጫወት የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን ከካፍ ያገኘው ማቡዋና አሊ ሳማታ በ30ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ታንዛኒያ ቻድን እንድትረታ አስችሏል፡፡ ታንዛኒያ ከሜዳዋ ውጪ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ስታሽንፍ ይህ ከ2011 በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ነው፡፡ ምድብ 7ን ግብፅ ስትመራ ታንዛኒያ በአራት ነጥብ ሶስተኛ ነች፡፡

የዕረቡ ውጤቶች

ደቡብ ሱዳን 1-2 ቤኒን

ጊኒ ቢሳው 1-0 ኬንያ

ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንስፔ 2-1 ሊቢያ

ዛምቢያ 1-1 ኮንጎ ብራዛቪል

ቻድ 0-1 ታንዛኒያ

የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎቹ ዛሬም ሲቀጥሉ አሰሞሃ ጂያንን በጉዳት ያጣቸው ጋና ሞዛምቢክን ታስተናግዳለች፡፡ ላይቤሪያ የምድብ 1ን መሪነት ከቶጎ ለመንጠቅ በማለም ጅቡቲን ትገጥማለች፡፡

የዛሬ ጨዋታዎች

ማዳጋስካር ከ ሴንትራል አፍሪካ ሪፑብሊክ

ኮሞሮስ ከ ቦትስዋና

ጋና ከ ሞዛምቢክ

ጅቡቲ ከ ላይቤርያ

 

*ፎቶ- ከሊቢያ እግርኳስ ፌዴሬሽን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *