​ሪፖርት | በሁለቱ አጋማሾች መረብ ላይ ያረፉት ሁለት ኳሶች ሰበታ እና ባህር ዳርን አቻ አለያይተዋል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የ14ኛ ሳምንት የመክፈቻ መርሐ-ግብር የሆነው የሰበታ ከተማ እና ባህር ዳር ከተማ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተገባዷል።

ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ አምስት ለአንድ የተረቱት ሰበታ ከተማዎች ሦስት ነጥብ ካስረከቡበት ጨዋታ ግብ ጠባቂው ለዓለም ብርሃኑን በሰለሞን ደምሴ፣ ወልደአማኑኤል ጌቱን በኃይለሚካኤል አደፍርስ፣ ታፈሠ ሰርካን በአንተነህ ናደው እንዲሁም መሐመድ አበራን በዱሬሳ ሹቢሳ ለውጠዋል። በተቃራኒው ባህር ዳር ከተማዎች ደግሞ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ ከተለያዩበት ፍልሚያ ቅጣት የተላለፈበት ግርማ ዲሳሳ እና በረከት ጥጋቡን በፈቱዲን ጀማል እና አለልኝ አዘነ ተክተው ጨዋታውን ቀርበዋል።

በጨዋታው ጅማሮ ወደግብ በመድረሱ ረገድ ተሽለው የቀረቡት ሰበታ ከተማዎች በጊዜ መሪ ለመሆን ሲታትሩ ባህር ዳሮች ደግሞ ኳስን በመቆጣጠር የተጋጣሚን የጨዋታ መንገድ ለማርገብ ሲጥሩ ነበር። በ14ኛው ደቂቃም ከወትሮው በተለየ እንደ ቡድን ሲያጠቃ እና ሲከላከል የነበረው ሰበታ በባህር ዳር ተጫዋቾች ስህተት ቀዳሚ ሆኗል። በተጠቀሰው ደቂቃም በረጅሙ የተላከውን ኳስ መናፍ ለግብ ጠባቂው ፋሲል ሲያቀብለው የግብ ዘቡ እጅግ ያጠረ ኳስ ለሌላኛው ተከላካይ ሰለሞን አደርሳው ሲል ሁለተኛ ጨዋታውን ለቡድኑ እያደረገ የሚገኘው ዴሪክ ኒስባምቢ ደርሶበት ለዱሬሳ ሲያመቻችለት ዱሬሳ ኳስ እና መረብን አገናኛቷል። 

የኳስ ቁጥጥራቸውን በሦስተኛው የሜዳ ሲሶ ማድረግ ያልቻሉት ተመሪዎቹ ባህር ዳሮች የጠራ የግብ ሙከራ ለማድረግ እስከ 22ኛው ደቂቃ ድረስ መጠበቅ የግድ ብሏቸዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ አካፋይ ሰዓትም ዓሊ ራሱ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት ፍፁም ሲያሻማው አግኝቶ በቀጥታ ወደግብ መትቶት ለጥቂት ወጥቶበታል። መሐል ለመሐል ብቻ በማጥቃት አቻ ለመሆን ያሰቡ የሚመስሉት ባህር ዳሮች ከኳስ ጀርባ የሆኑትን ሰበታዎች ማስከፈት ከብዷቸው ጨዋታው ቀጥሏል። ይባስ በ33ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ጎል ለማስተናገድ ተቃርበው ነበር። በዚህም ከመሐል ሜዳው ጨረቃ በረከት ሳሙኤል እጅግ አክርሮ የመታውን የቅጣት ምት ኳስ ፋሲል እንደምንም በእግሩ አምክኖታል። የጣናው ሞገዶቹ የኋላውን መስመር ሰብረው መግባት ባይችሉም በ39ኛው ደቂቃ አምበላቸው ፍቅረሚካኤል ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመታው እና የግቡን አግዳሚ ገጭቶ በተመለሰው ኳስ አቻ ሊሆኑ ነበር። አጋማሹ ሊገባደድ ስልሳ ሰከንዶች ሲቀሩትም ፉዐድ ሌላ ኳስ ከሳጥን ውጪ ሞክሮ ነበር። 

እጅግ የተዋሀደ አጨዋወት ማድረግ የቀጠሉት ሰበታዎች ቦታዎችን ለተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች እየነፈጉ ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ በመከተል ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ታትረዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ በግራ መስመር ላይ ብቻ (100%) የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ሲዘውሩ የነበሩት የአሠልጣኝ ብርሃን ደበሌ ተጫዋቾች በ51ኛው ደቂቃ ለመጀመሪያ ጊዜ በተቃራኒ መስመር ሄደው ወደ ሳጥን ጥሩ ኳስ በሳሙኤል ሳሊሶ አማካኝነት ቢልኩም ግብ አስቆጣሪው ዱሬሳ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በመጀመሪያው አጋማሽ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ያልቻሉት ባህር ዳሮች በ57ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ኳስ በግብ ብረቶቹ መሐል ልከው አቻ ሆነዋል። በተገለፀው ደቂቃም በረጅሙ የተላከን ኳስ ተከላካዮች ሲያወጡት የደረሰው ፍፁም በጥሩ ሁኔታ ለዓሊ ሰጥቶት ፈጣኑ አጥቂ በግራ እግሩ ግብ አስቆጥሯል። ተጫዋቹም የመጨረሻ የኳስ ንክኪውን መረብ ላይ አሳርፎ ከሜዳ ተቀይሮ ወጥቷል። ከአርባ ደቂቃዎች በላይ መሪ የነበሩት ሰበታዎች የአቻነት ግብ ካስተናገዱ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ በጥሩ የኳስ ቅብብል በበኃይሉ ግርማ አማካኝነት ጥቃት ሰንዝረው ዳግም መሪ ለመሆን ጥረዋል።

ከግቡ በኋላ እድገት እያሳዩ የመጡት ባህር ዳሮች የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን አስገብተው ጫና ለመፍጠር ሞክረዋል። ሰበታዎችም የአማካይ እና የአጥቂ ተጫዋቾችን ለውጥ ቢያደርጉም በመጀመሪያው አጋማሽ የነበራቸው ተነሳሽነት ቀነስ በማለቱ ወደራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው የባህር ዳርን ጥቃት መመከት ላይ ተጠምደው ሲውሉ ተስተውሏል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊገባደድ አራት ደቂቃዎች ሲቀሩት ግን ሰበታ እጅግ ለግብ ቀርቦ ነበር። በ79ኛው ደቂቃ ዱሬሳ ሹቢሳን ቀይሮ የገባው ፍፁም ከተከላካይ ጀርባ የደረሰውን ተንጠልጣይ ኳስ መረብ ላይ አሳረፈ ሲባል መናፍ በሚገርም ቅልጥፍና ደርሶ አምክኖበታል። ጨዋታውም በቀሪ ደቂቃዎች ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት ፍፃሜውን አግኝቷል።

አንድ አንድ ነጥብ ከጨዋታው የወሰዱት ሰበታ እና ባህር ዳር በቅደም ትከተል 8 እና 19 ነጥቦችን በመያዝ 16ኛ እንዲሁም 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።