​ቅድመ ዳሳሳ | ሲዳማ ቡና ከ አዲስ አበባ ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ነገ አስር ሰዓት በሲዳማ ቡና እና አዲስ አበባ ከተማ መካከል የሚደረገው ጨዋታ እንዲህ ተዳሷል።

ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠል ከአዳማ ከተማ ጋር በጣምራ በሊጉ ጥቂት ጨዋታዎችን (2) የተሸነፉት ሲዳማ ቡናዎች ባሳለፍነው ሳምንት ከወልቂጤ ከተማ ጋር አቻ ሲለያዩ ካሳዩት ደካማ ብቃት ለማገገም እና ዳግም ሦስት ነጥብ አግኝቶ በጊዜያዊነት አራተኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ነገ ታትረው እንደሚጫወቱ ይታሰባል። ጥቂት ግቦች በተስተናገዱበት የ13ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች አምስት ጎሎችን ሰበታ ላይ አዝንበው የውድድር ዓመቱ አራተኛ ድላቸውን ያስመዘገቡት አዲስ አበባዎች በበኩላቸው አሁንም ካለባቸው የወራጅነት ስጋት ተላቆ ነጥባቸውን በደረጃ ሰንጠረዡ አጋማሽ ከሚገኙ ክለቦች በላይ ለማድረግ ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይገመታል።

በአሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው ሲዳማ ቡና ያለፉትን ስድስት ጨዋታዎች ባይሸነፍም ወጥ የሆነ ብቃት ሜዳ ላይ ሲያሳይ አይስተዋልም። ከወልቂጤ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታም የቀደመ ቅርፁን አግኝቶ ለመጫወት በርከት ያሉ ደቂቃዎች ወስደውበት ነበር። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታውን ግለት መቆጣጠር ተስኗቸው በኳስ ቁጥጥር እና የግብ ሙከራዎችን በማድረግ ብልጫ ተወስዶባቸው ታይቷል። የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች ይገዙ እና ሀብታሙም በጣም ተነጥለው ከአማካይ መስመሩ ድጋፍ ሲያገኙ አልነበረም። እርግጥ ይህ የሆነው ካልተጠበቀው የወልቂጤ ፍጥነት የታከለበት አጨዋወት እንደሆነ ቢገመትም አዲስ አበባም መሐል ሜዳ ላይ ጨዋታውን ለመወሰን የሚያደርገው ፍልሚያ ቀላል ስለማይሆን ቡድኑ ተጠንቅቆ ወደ ሜዳ መግባት ይጠበቅበታል። በአንዳንድ ጨዋታዎች መሐል ለመሐል ፍሬውን ታኮ ከሚደረጉት የማጥቃት እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ ሜዳውን በሁለቱ የመስመር ተከላካዮች ለጥጦ ሌላ አማራጭ ለማግኘት የሚጥረው ቡድኑም በዚህ ረገድ ከፍተኛ መቀዛቀዝ እያመጣ ነው። ነገ አጥበው እንደሚከላከሉ የሚታሰቡትን የአዲስ አበባ ተጫዋቾች ለማዘርዘር ደግሞ የመስመር ላይ ሩጫዎች ወሳኝ ስለሆኑ ቡድኑ ይህንን ባህሪውን መልሶ ማግኘት ይጠበቅበታል።

ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት ሰበታ ከተማ ላይ ጣፋጭ ድል የተቀዳጁት አዲስ አበባዎች በጨዋታው ያሳዩት ብቃት እጅግ ከፍተኛ ነው። በሚታወቁበት 4-3-3 የተጫዋች አደራደር ቅርፅም በከፍተኛ ተነሳሽነት ኳሱን ለሰበታዎች ሰጥተው በፈጣን መልሶ ማጥቃቶች እና ተሻጋሪ ኳሶች በተጋጣሚ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ደርሰው በድምሩ 15 ሙከራዎችን አድርገዋል። ከእነዚህ ሙከራዎች ደግሞ አምስቱ ዒላማቸውን የጠበቀ ሆነው አምስቱም መረብ ላይ አርፈዋል። ከምንም በላይ ደግሞ አማካይ መስመር ላይ ቻርለስ ሪባኑ እና ሙሉቀን አዲሱ አጥቂ ቦታ ላይ ደግሞ ሪችሞንድ አዶንጎ እና ፍፁም ጥላሁን ለተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ምቾት ሲነፍጉ ነበር። ያለፉትን ጨዋታዎች የነበረባቸው የግብ ዕድሎችን በአግባቡ የመፍጠር ክፍተትም በጨዋታው ሻል ብሎ ስል ሆነው ወተዋል። ነገም ታታሪነት የተሞላበት አጨዋወት በቡድኑ በኩል ሲጠበቅ አልፎ አልፎ በተናጥል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እና የውሳኔ አሰጣጥ ችግሮች ግን አሁንም ተሻሽለው መቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት አራተኛ ግብ ሳያስቆጥሩ የወጡበትን የጨዋታ ቀን ያሳለፉት ሲዳማ ቡናዎች እስካሁን በሊጉ 14 ጎሎችን ቢያስቆጥሩም የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች የሆነው (ከኦሮ-አጎሮ ጋር እኩል) ይገዙ ላይ እጅጉን የተንጠለጠሉ ይመስላል። የቡድኑን ከግማሽ በላይ ግብ ያስቆጠረው ተጫዋቹ በዚህን ያህል ደረጃ ለቡድኑ ጠቀሜታ መስጠቱ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ቡድኑ ግን ከእርሱ ውጪ አማራጭ የግብ ማግኛ መንገዶችን መፈለግ ይጠበቅበታል። አዲስ አበባዎች ደግሞ የመጀመሪያው ዙር የመጨረሻው ጨዋታቸው ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ስለሆነ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት የሚጠብቃቸውን ከባድ ፈተና ነገ ማቅለል ይገባቸዋል። ቀድመን እንደገለፅነው ግን የይገዙን እንዲሁም የፍሬውን የመሐል ለመሐል ጥቃት መመከት ተቀዳሚ ስራቸው ይሆናል።

በሲዳማ ቡናም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ በኩል ምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና የለም። የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ ፌዴራል ዋና ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ በመሐል አልቢትርነት ሲመሩት አበራ አብርደው እና ዘሪሁን ኪዳኔ ረዳት በላይ ታደሰ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆነው ጨዋታውን እንደሚከውኑ አውቀናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት 

– የሁለቱ ቡድኖች ብቸኛ የዕርስ በርስ ግንኙነት በ2009 የተከናወነ ሲሆን ሲዳማ ቡና ሁለቱንም ጨዋታዎች (3-1 እና 1-0) ማሸነፍ ችለዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ


ሲዳማ ቡና (4-4-2 ዳይመንድ )

ተክለማርያም ሻንቆ

አማኑኤል እንዳለ – ጊት ጋትኩት – ያኩቡ መሐመድ – መሐሪ መና

ሙሉዓለም መስፍን

ቴዎድሮስ ታፈሰ – ዳዊት ተፈራ

ፍሬው ሰለሞን

ይገዙ ቦጋለ – ሀብታሙ ገዛኸኝ

አዲስ አበባ ከተማ (4-3-3)

ዳንኤል ተሾመ

አሰጋኸኝ ጴጥሮስ – ሳሙኤል አስፈሪ – ዘሪሁን አንሼቦ – ሮቤል ግርማ

ኤልያስ አህመድ – ቻርለስ ሪባኑ – ሙሉቀን አዲሱ

እንዳለ ከበደ – ሪችሞንድ አዶንጎ – ፍፁም ጥላሁን