ቅድመ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ አርባምንጭ ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በ14ኛው ሳምንት ሦስተኛ የጨዋታ ዕለት ምሽት የሚደረገውን ጨዋታ እንዲህ ተመልክተነዋል።

ይህ ጨዋታ በዚህ ሳምንት ከሚደረጉ ጥሩ ፉክክር ልናይባቸው ከምንችላቸው ጨዋታዎች ውስጥ የሚመደብ ነው። ቡድኖቹ በደረጃ ይራራቁ እንጂ ሜዳ ላይ የጨዋታው መንገዳቸው በግልፅ የተስተዋሉባቸው የቅርብ ጨዋታዎቻቸው ነገ ምሽት ላይ ሲገናኙ የሚፈጠረውን እንድንጠብቅ ያደርገናል። ከውጤት አንፃርም ቅዱስ ጊዮርጊስ ዛሬ ድል ከቀናው ሀዋሳ ከተማ ጋር የአንድ ነጥብ ብቻ የሆነው ልዩነቱን ለማስፋት እንዲሁም አርባምንጭ ከተማ ከወራጅ ቀጠናው ያለውን የሁለት ነጥብ ብቻ ርቀት ከፍ ለማድረግ በማለም በጥሩ ተነሳሽነት ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከአምስት ተከታታይ ድሎች በኋላ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ነጥብ የተጋሩበት ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ካለማሳካት ያለፈ ትርጉም የነበረውም ነው። አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ከጨዋታው በኋላ በሰጡት አስተያየት ላይ እንዳንፀባረቁትም ቡድኑ ሰሞኑን ደጋግሞ እንዳሳየው በመስመሮች ያመዘነ ፈጣን መልሶ ማጥቃትን ለመሰንዘር በየጨዋታው ያወጣው ጉልበት ተጫዋቾችን ሳያዳክማቸው አልቀረም። በመሆኑም በተሻለ አካላዊ ቁመና ላይ የነበረው እና የጊዮርጊስን የማጥቂያ መንገዶች የመቆጣጠር የጨዋታ ዕቅድ የነበረው ሀዲያ ሆሳዕና በአምስቱ ድሎቹ 12 ግቦችን ያስቆጠረውን ቡድን ያለግብ እንዲወጣ ማድረግ ችሎ ነበር።

የነገ ምሽቱ ተጋጣሚው አርባምንጭ ከተማ በዚህ ረገድ ያለው ጥንካሬ ደግሞ የጊዮርጊስ ቀጣይ ፈተና ሊሆን ይችላል። ከሜዳው ወጥቶም ጫና በመፍጠር ሆነ ወደ ራሱ ግብ ቀርቦ በጥልቀት ለመከላከል ምቹ መዋቅር ያለው እና የመስመር ጥቃቶችን ለመቋቋም የተመቸ አደራደር የሚጠቀም አርባምንጭን በቀጥተኛ እና ፈጣን ጥቃት ጊዮርጊስ በምን አኳኋን እጅ ሊያሰጠው ይችላል የሚለው ጉዳይ የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ ትልቁ ትኩረት ነው። በአካል ብቃት ዝግጁነት የማይታማው ተጋጣሚውን ለመገዳደር አዲስ ጉልበት ያስፈልጋል ብለው ካሰቡም በሰሞኑ ቀዳሚ አሰላለፋቸው ውስጥ የተወሰኑ ለውጦች ሊያደርጉ የሚችሉበት ዕድል ይኖራል። የተጋጣሚን አጨዋወት ከመወሰን አንፃር ግን በራሱ ሜዳ ከሚቆይ ይልቅ ከሜዳው ወጥቶ ጫና ሲፈጥር ከኋላው ለመልሶ ማጥቃት የሚሆን ክፍተት የሚተው አርባምንጭን ለማግኘት የሚረዳ የጨዋታ ዕቅድ ከጊዮርጊሶች ይጠበቃል።

በተመሳሳይ አርባምንጭ ከተማ የታየበት ክፍተት የቅዱስ ጊዮርጊስ ጠንካራ ጎን ሆኖ እናገኘዋለን። አዞዎቹ አድካሚ በሆነው ከኳስ ውጪ ጫና ፈጥሮ ተጋጣሚ ቅብብሎችን እንዳይከውን የማድርግ አላማ ያለው አጨዋወታቸውን በጥሩ የአካል ብቃት ሲተገብሩ ይታያሉ። በተለይም የመጨረሻ ተጋጣሚያቸው ኢትዮጵያ ቡናን በዚህ አካኋን ለረጅም ደቂቃዎች ምንም ዓይነት የማጥቃት ዕድል መፍጠር እንዳይችል አድርገውት ነበር። በእርግጥ ይህ ዕቅድ ከፍ ባለ ጉልበት ጨዋታውን ጀምሮ ግቦችን በጊዜ ማስቆጠር የሚፈልገው ጊዮርጊስንም በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ ለመቋቋም የሚያስችል ሆኖ እናገኘዋለን። ነገር ግን አርባምንጮች ኳስን በሚፈልጉት ቦታ ላይ ካስጣሉ በኋላ ቀጣይ እርምጃቸው አሁንም መታረም አልቻለም።

ኳስ በመንጠቁ ሂደት ላይ በብዙው ተሳታፊ ሲሆኑ የሚታዩት የቡድኑ የወገብ በላይ ተጫዋቾች ቡድናቸው ኳስ ሲይዝ የሚወስዷቸው ወደግብ የመሞከርም ሆነ ለአጋራቸው የማድረስ ውሳኔዎች የተዛቡ ሆነው እናገኛቸዋለን። ይህ የቡድኑ ደካማ ጎን እስካሁን ሽንፈት ካላስተናገደ እና መረቡ ከተደፈረ ሰባት ጨዋታዎችን ካስቆጠረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ሲገናኝ አፈፃፀሙ ምን መምሰል እንዳለበት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን የሚያሳስብ ይመስላል። ብዙ ግምት ተሰጥቷቸው እንደተጠበቁ ካልሆኑ እንደ ኤሪክ ካፓይቶ ዓይነት ተጫዋቾችን ብቃት መልሶ ማግኘት አልያም የአሰላለፍ ለውጦችን ማድረግም የአሰልጣኙ አማራጭ ይሆናል። በጥቅሉ ግን አርባምንጮች ከኳስ ውጪ ሆነው ምላሽ በመስጠት ላይ ያተኮረ አቀራረባቸው ነገም መደገሙ የሚቀር አይሆንም።

ቅዱስ ጊዮርጊስ አማካዩ ከነዓን ማርክነህን የማሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ሲሆን በአርባምንጭ ከተማ በኩል ግን የጉዳትም ሆነ የቅጣት ዜና አልተሰማም።

ጨዋታው በተፈሪ አለባቸው መሀል ዳኝነት ሲከናወን ረዳቶቹ ክንዴ ሙሴ እና ሙስጠፋ መኪ አራተኛ ዳኛው ደግሞ ተከተል ተሾመ ሆነዋል።

የእርስ በእርስ ግንኘነት

– ተጋጣሚዎቹ እስካሁን በሊጉ 14 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ገዮርጊስ 10 በማሸነፍ ቀዳሚው ሲሆን አርባምንጭ 2 አሸንፎ በቀሪዎቹ 2 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ 26 ሲያስቆጥር አርባምንጭ 9 ማስቆጠር ችሏል። የመጨረሻ አራት ግንኙነታቸው በየጨዋታው ሦስት እና ከዛ በላይ ጎል ተቆጥሮበታል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ቻርለስ ሉክዋጎ

ሱሌይማን ሀሚድ – ምኞት ደበበ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ሔኖክ አዱኛ

ያብስራ ተስፋዬ – ጋቶች ፓኖም – በረከት ወልዴ

አቤል ያለው – እስማኤል ኦሮ-አጎሮ – አማኑኤል ገብረሚካኤል

አርባምንጭ ከተማ (4-4-2)

ሳምሶን አሰፋ

ወርቅይታደስ አበበ – በርናንድ ኦቼንግ – አሸናፊ ፊዳ – ተካልኝ ደጀኔ

ሙና በቀለ – እንዳልካቸው መስፍን – አቡበከር ሸሚል – ሀቢብ ከማል

በላይ ገዛኸኝ – ፀጋዬ አበራ