ጋቦን 2017፡ ጋና ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ የተቃረበችበትን ድል አስመዝግባለች

ጋቦን በ2017 ለምታስተናግድው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚደረጉ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ትላንትም ቀጥለው ውለዋል፡፡ ጋና አክራ ላይ ሞዛምቢክን በማሸነፍ ለአፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ ስትቃረብ ኮሞሮስ ቦትስዋናን እንዲሁም ላይቤሪያ ጅቡቲን በተመሳሳይ 1-0 ረተዋል፡፡

በአክራ ስፖርትስ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ የምድብ 8 መሪዋ ጋና ሞዛምቢክን 3-1 አሸንፋለች፡፡ የድል ግቦቹን ፋራንክ አቼምፖንግ፣ የአሰሞሃ ጂያንን መጎዳት ተከትሎ አምበል የሆነው ተከላካዩ ጆን ቦይ እንዲሁም ጆርዳን አዩ ከመረብ አዋህደዋል፡፡ ሞዛምቢክን በባዶ ከመሸነፍ ያዳነች ግብ ደግሞ አፕሰን ማንጄት በስሙ አስመዝግቧል፡፡

ሶስቱንም የምድብ ጨዋታ ማሸነፍ የቻለችው ጋና ምድቡን በ9 ነጥብ ስትመራ ሩዋንዳ እና ሞሪሺየስ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡

በምደብ 1 የምትገኘው ላይቤሪያ ጅቡቲ ላይ ጅቡቲን 1-0 አሸንፋለች፡፡ አንቶኒ ላፎር የማሸነፊያ ግቧን በሁለተኛው ግማሽ አስቆጥሯል፡፡ ምድቡን ቶጎ እና ላይቤሪያ በተመሳሳይ ስድስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሲመሩት ቱኒዚያ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡

በሃይለኛ ዝናብ ምክንያት ተቋርጦ የተጀመረው የምድብ 4 የኮሞሮስ እና ቦትስዋና ግጥሚያ በኮሞሮስ አሸናፊነት ተጠናቅቋል፡፡ የኮሞሮስን የድል ግብ ቤን መሃመድ ኤል-ፋርዶ ነስሙ አስመዝግቧል፡፡ ምድቡን ዩጋንዳ በስድስት ነጥብ ስትመራ፣ ተሸናፊዋ ቦትስዋና፣ ቡርኪናፋሶ እና ኮሞሮስ በሶስት ነጥቦች ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል፡፡

አንታናናሪቮ ላይ ማዳጋስካር ከማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር አቻ ተለያይታለች፡፡ ባለሜዳዎቹ በካርሎስ አንድሪያማሂሲኖሮ የ80ኛ ደቂቃ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ቢመሩም ከአራት ደቂቃ በኃላ ሊማኔ ሙሳ እንግዶቹን አቻ አድርጓል፡፡ ምድብ 2ን ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ በአምስት ነጥብ ስትመራ አንጎላ እና ዲ.ሪ. ኮንጎ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡

የሐሙስ ውጤቶች

ጅቡቲ 0-1 ላይቤሪያ

ማዳጋስካር 1-1 ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ

ኮሞሮስ 1-0 ቦትስዋና

ጋና 3-1 ሞምቢክ

የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎቹ ዛሬም ቀጥለው ሲውሉ ካዱና ላይ ናይጄሪያ ግብፅን የምታስተናግድበት ጨዋታ ከፍተኛ ግምትን አግኝቷል፡፡ የምድቡ መሪ ግብፅ ከ2010 በኃላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለመመለስ ከናይጄሪያ ጋር ብርቱ ፉክክር ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

የ2015 የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ኮትዲቯር አቢጃን ላይ ሱዳንን ትገጥማለች፡፡ ሱዳን ምድቡን ከአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅዋ ጋቦን ቀጥሎ ስትመራ በውጤት ቀውስ ውስጥ የምትገኙት ዝሆኖቹ ማሸነፍን አላማ አድርገው ወደ ጨዋታ ይገባሉ፡፡ በምድቡ ሌላ ጨዋታ ጋቦን ሴራሊዮንን ፋራንስቪል ላይ ታስተናግዳለች፡፡

ጋቦን የ2017 አዘጋጅ በመሆኗ በአፍሪካ ዋንጫው ላይ የቀጥታ ተሳትፎ ዕድልን ብታገኝም ካፍ አዘጋጅ ሃገራት በማጣሪያ ጨዋታዎቹ ላይ እንደማሙያ እንዲሳተፉ ባወጣው ህግ መሰረት እየተሳተፈች ትገኛለች፡፡

ብሊዳ ላይ ኢትዮጵያ አልጄሪያን እንዲሁም ቱኒዚያ ቶጎን የሚገጥሙበት ጨዋታዎች ሌሎች ዛሬ የሚደረጉ መርሃ ግብሮች ናቸው፡፡

የዛሬ ጨዋታዎች

15፡00 – ስዋዚላንድ ከ ዚምባቡዌ (ሎባምባ ስታዲየም)

15፡30 – ጋቦን ከ ሴራሊዮን (ፍራንስቪል ስታዲየም)

16፡00 – ናይጄሪያ ከ ግብፅ (አማዱ ቤሎ ስታዲየም)

16፡30 – ሞሪታንያ ከ ጋምቢያ (ኦፊስ ዱ ኮምፕሌክስ ኦሎምፒክ ደ ናውኩቾ)

1፡30 – ኮትዲቯር ከ ሱዳን (ስታደ ፊሊክስ ሆፕሆት ቦይግኒ)

2፡00 – ጊኒ ከ ማላዊ (ስታደ 28 ሴፕቴምበር)

3፡00 – ቱኒዚያ ከ ቶጎ (ስታደ ሙስጠፋ ቤን ጃኔት)

4፡00 – ማሊ ከ ኢኳቶሪያል ጊኒ (ስታደ 26 ማርች)

4፡30 አልጄሪያ ከ ኢትዮጵያ (ስታደ ሙስጠፋ ቻክር)

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *