የኢትዮጵያ ሴቶች ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ከዩጋንዳ ጋር የመልስ ጨዋታውን ያደረገው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ17 ዓመት ብሔራዊ ቡድን በእየሩስ ወንድሙ የመጨረሻ ደቂቃ ጎል 1-1 በመለያየት በድምር ውጤት የመጀመሪያ ማጣሪያውን አልፏል።

የአሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ ስብስብ ከመጀመሪያው ጨዋታ አሰላለፍ ሜላት ዓሊሙዝ ፣ መስከረም መኮንን እና እየሩስ ወንድሙን በትርሲት ወንድወሰን ፣ ቃልኪዳን ወንድሙ እና ሰብለወንጌል ወዳጆ በመተካት ጨዋታውን ጀምሯል።

ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ የታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ በአመዛኙ መሀል ሜዳ ላይ ያመዘነ የጨዋታ ሂደት ታይቶበታል። ጨዋታው በጀመረባቸው ደቂቃዎች አለመረጋጋት የታየባቸው የኢትዮጵያ ከ 17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ለዩጋንዳ አቻዎቻቸው ጫና ተጋልጠው ነበር። ዩጋንዳዎች በኢትዮጵያ ሜዳ ላይ የተሻለ የኳስ ቅብብልን በመከወን ወደ ግብ ለመጠጋት ሲጥሩ ኢትዮጵያዊያኑ ደግሞ በቀኝ መስመር በየምወድሽ አሸብር በኩል አድልተው በመልሶ ማጥቃት ለመግባት ሲጥሩ ይታይ ነበር። ይሁን እንጂ የሁለቱም የማጥቃት ሂደት የሞፈልጉትን የግብ ዕድል ይዞ ሳይመጣ ቆይቷል።

ዩጋንዳዎች የፈጠሩት ጫና የጠራ ሙከራን አያስገኝላቸው እንጂ ተደጋጋሚ የቆመ ኳስ ዕድልን ይዞላቸው ሲመጣ ይታይ ነበር። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዎቾችም አልፎ አልፎ ወደ ሁለተኛው የሜዳ አጋማሽ ሲደርሱ በታመሳሳይ የቅጣት ምት አጋጣሚዎችን አግኝተው ነበር። 20ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ ያደላው የመሰረት ማሞ ቅጣት ምት ለጥቂት ወደ ውጪ ሲወጣ 25ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ እየሩስ ወንድሙ ከማዕዘን በተነሳ ኳስ ሙከራ አድርጋ ነበር። ሆኖም ዩጋንዳዎች 31ኛው ደቂቃ ላይ ከግማሽ ጨረቃው አካባቢ በካትሪና ናጋዲያ አማካይነት ግሩም የቅጣት ምት ሙከራ አድርገው ግብ ጠባቂዋ አበባ አጂቦ ያዳናችባቸው ከባዱ ሙከራ ሆኖ ታይቷል። ይኸው እንቅስቃሴ በማዕዘን ምት ሲቀጥልም ካትሪና ያሻማችውን አበባ አጂቦ የጨረፈቺውን እና ተከላካዮች ያላወጡትን ኳስ ሻኪራ ኒናጋሂርዋ በማስቆጠር ሀገሯን ቀዳሚ አድርጋለች።

በቀሪው የአጋማሹ ደቂቃዎች ይበልጥ መረጋጋት ተስኗቸው የታዩት የኢትዮጵያ ተጫዋቾች ግለሰባዊ ስህተቶች መበራከት ለዩጋንዳዎች ዕድል ሲፈጥሩ ያይቷል። ቡድኑ በጥቂት አጋጣሚዎች ብቻ ወደ ዩጋንዳ ደጃፍ መድረስ ሲችል ያለቀለት የግብ ዕድል ግን መፍጠር አልቻለም። ዩጋንዳዎችም በተመሳሳይ ያገኙትን ብልጫ ወደ ጠንካራ ሙከራ ሳይቀይሩ ጨዋታው ተጋምሷል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ የተሻለ ንቃት ታይቶበታል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአጀማመሩ በተሻለ ሁኔታ ኳስ ይዞ ወደ ዩጋንዳ ሜዳ ለመግባት ሲጥር ዩጋንዳዎችም ቀጥተኝነት ሲንፀባረቅባቸው ውጤት ከማስጠበቅ ይልቅ ገፍቶ መጫወትን ምርጫቸው አድርገዋል። የቡድኑ ቀዳሚ ሙከራ የእሙሽ ዳንኤል የ52ኛ ደቂቃ ወደ ግራ ያደላ ቅጣት ምት ሲሆን ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል። ለማጥቃት ከመጣር ያልቦዘኑት ዩጋንዳዎች በተለይም የኢትዮጵያ ተከላካዮች ስህተቶችን በመጠቅም ለግብ የቀረቡባቸው አጋጣሚዎች ቢፈጠሩም ወደ ግብ አጋጣሚዎች አልተቀየሩም።

ቀስ በቀስ ዩጋንዳዎች የኢትዮጵያዊያኑን የማጥቃት ጥረት በመግታት እና በማጥቃት መሀል ሲዋልሉ ከሰሚራ ከድር ተቀይሮ መግባት በኋላ በንፅፅር የተደራጀ የመሀል ሜዳ ብልጫ ለማግኘት ሲንቀሳቀሱ የታዩት የኢትዮጵያዊያን ያለቀላቸው ዕድሎች ከቆሙ ኳሶች መነሻነት መታየየት ጀምረዋል። 60ኛው ደቂቃ ላይ የትዕግስት አዳነን ረጅም ቅጣት ምት እሙሽ ዳንኤል በግንባሯ ሞክራ የወጣባት ቀዳሚው ነበር። ከዚህም በላይ ግን 68ኛው እና 80ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ ከቅጣት ምት ወደ ግብ የተላኩትን ኳሶች የዩጋንዳዎች ግብ ጠባቂ ሻሮን ካይዱ በአግባቡ መቆጣጠር ሳትችል ቀርታ ከግብ አፋፍ ላይ የተገኙትን ዕድሎች ኢትዮጵያዊያኑ ያመከኑበት መንገድ የሚያስቆጭ ነበር።
ሁለተኛው አስቆጪ ሙከራ ከታየ አራት ደቂቃዎች በኋላ ግን ጥሩ ስትንቀሳቀስ የዋለችው ግብ ጠባቂዋ አበባ አጄቦ በረጅሙ የለጋችው ኳስ ከዩጋንዳ የከላካዮች ጀርባ ሲደርስ እየሩስ ወንድሙ በግብ ጠባቂዋ አናት ላይ በመላክ ወሳኝ ግብ አስቆጥራለች።

ዩጋንዳዎች ሌላ ግብ ለማከል በቀሩት ደቂቃዎች ያደረጉት ጥረት ሳይሰምር በመቅረቱም የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከሜዳ ውጪ በተቆጠረ ግብ በድምር የ3-3 ውጤት ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉን አረጋግጧል።
ብሔራዊ ቡድኑ በቀጣዩ ዙር በፊፋ እገዳ የተጣለባት ኬኒያን በፎርፌ ያለፈችው ደቡብ አፍሪካ ጋር ይገናኛል።