ሪፖርት | ከሆሳዕና ነጥብ የተጋራው ፋሲል ከመሪው ያለው ርቀት ሰፍቷል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ቀትር ላይ ጅማሮውን ባደረገው የሁለተኛው ዙር ውድድር የዕለቱ ሁለተኛ በነበረው ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና እና ፋሲል ከነማ ነጥብ በመጋራት ዙሩን ጀምረዋል።

ፋሲል ከነማዎች ከአልጄሪያው ጄኤስ ካቢል የወራት ቆይታ መልስ ዳግም ወደ ስብስባቸው የቀላቀሉትን ሙጂብ ቃሲምን በፊት መስመራቸው ላይ ከኦኪኪ አፎላቢ በ 4-1-3-2 ቅርፅ በማጣመር ጨዋታውን ሲያስጀምሩ በአንፃሩ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደግሞ እንደ መጀመሪያው ዙር ሁሉ በ3-5-2 የተጫዋቾች አደራደር በመጠቀም ጨዋታቸውን አድርገዋል።

በጠሩ የግብ ሙከራዎች ረገድ እምብዛም የታደለ ባልነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሀዲያ ሆሳዕናዎች የተሻሉ ነበሩ ፤ በአጋማሹም በተለይ የቀኝ መስመር ተመላላሹ ብርሃኑ በቀለ ተደጋጋሚ አደጋዎችን ሲፈጥር ተመልክተናል።

በአጋማሹ ሀዲያ ሆሳዕናዎች በተጋጣሚ የሜዳ አጋማሽ በቁጥር በርከት ብለው በመገኘት ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። ኢላማውን የጠበቁ ሙከራዎችን ማድረግ ባይችሉም በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች በብርሃኑ በቀለ እና ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን አማካኝነት ከሳጥን ውጭ ያደረጓቸው ሙከራዎች ተጠቃሽ ነበሩ።

ጫና አሳድረው መጫወታቸውን የቀጠሉት ሆሳዕናዎች በ19ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማስመዝገብ ችለዋል ። ሀብታሙ ታደሰ አስቻለው ታመነ ላይ ባሳደረው ጫና ያገኘውን ኳስ ተጠቅሞ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ ሰብሮ የገባው ሀብታሙ ወደ ግብ የላከውን ኳስ ይድነቃቸው ሊያድንበት ችሏል።

መሀል ሜዳ ላይ ከተጋጣሚያቸው አንፃር የቁጥር ብልጫ የነበራቸው ሀዲያ ሆሳዕናዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታውን በመቆጣጠር ሆነ ኳስ ከራሱ ሜዳ መስርቶ መውጣት የሚፈለጉትን ፋሲል ከነማዎች ላይ ጫና አሳድረው በመጫወት ረገድ ውጤታማ ነበሩ።
በአጋማሹ ብልጫ የተወሰደባቸው ፋሲሎች በንፅፅር የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የነበራቸው ሲሆን በጨዋታው በተለይ መሀል ሜዳ ላይ በነበረው ፍላሚያ መበለጣቸውን ተከትሎ በአጋማሹ ሁለቱ የፊት አጥቂዎቻቸው ከቡድኑ ተነጥለው ያለ አገልግሎት ሲባክኑ አስተውለናል። በአጋማሹ በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች በተወሰነ መልኩ ፈጠን ባሉ የማጥቃት ሽግግሮች ወደ ሀዲያ ሆሳዕና ሳጥን መጠጋት ቢችሉም ሶሆሆ ሜንሳን የሚፈትን ሙከራ ግን በአጋማሹ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተናል።

ሁለተኛውን አጋማሽ ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ እና ሱራፌል ዳኛቸውን ተክተው በማስገባት ጨዋታውን የጀመሩት ፋሲሎች በለውጦቹ መነሻነት ወደቀደመው 4-1-4-1 አደራደር በመመልስ መሀል ሜዳ ላይ የተወሰደባቸውን የመሀል ሜዳ ብልጫ ማስመለስ የቻሉበት ሲሆን የአጋማሹ አጀማመር ግን በንፅፅር ከመጀመሪያው አንፃር እጅግ ቀዝቀዝ ያለ ነበር።

ቀስ በቀስ በጨዋታው የበላይነት መውሰድ የጀመሩት ፋሲሎች በጨዋታው ሁለተኛ በነበረው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ መሪ ሆነዋል። በ66ኛው ደቂቃ ፋሲሎች ከማዕዘን ምት ያሻሙት ኳስ በሆሳዕና ተጫዋቾች ተገጭቶ ሲመለስ ከሳጥኑ በቅርብ ርቀት የነበረው በዛብህ መለዮ ወደ ግብ የላካት ኳስ በሆሳዕና ተጫዋቾች ተጨርፋ ከመረብ ላይ በማረፍ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ፋሲሎች ይሁን እንደሻውን በግብ አስቆጣሪው በዛብህ መለዮ ተክተው በማስገባት በተወሰነ መልኩ ለተከላካያቸው ይበልጥ ሽፋን ለመስጠት ያለመ ለውጥን ቢያደርጉም መሪነታቸው ከዘጠኝ ደቂቃ በላይ መዝለቅ አልቻለም። በ75ኛው ደቂቃ ላይ ሆሳዕናዎች አቻ መሆን ችለዋል ፤ ሄኖክ አርፊጮ ከማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ የተገኘው ቃለአብ ውብሸት በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን አቻ አድርጓል።

ከግቧ በኋላ የነበረው የጨዋታ ሂደት በዋነኝነት የሆሳዕናው የግብ ዘብ የሆነው ሶሆሆ ሜንሳ ጉዳት በማስተናገዱ የተነሳ በርከት ያሉ ደቂቃዎች በህክምና እርዳታ ላይ መቆየቱን ተከትሎ የጨዋታው ሂደት ሲመለስ በተወሰነ መልኩ የተቀዛቀዘ ነበር። በቀሩት ደቂቃዎች ፋሲሎች ጫና ለመፍጠር ቢሞክሩም የሀዲያ ሆሳዕና ጠንካራ መከላከልን ማስከፈት ሳይችሉ ቀርተዋል።

ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ፋሲል ከነማዎች በ27 ነጥብ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሰባት ነጥብ ርቀው በ3ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ በአንፃሩ ሀዲያ ሆሳዕናዎች በ18 ነጥብ 11ኛ ደረጃ መቀመጥ ችለዋል።