ቅድመ ዳሰሳ | መከላከያ ከ አርባምንጭ ከተማ

የሦስተኛ ቀን የሊጉ የመጀመሪያ መርሐ-ግብር እንዲህ ተቃኝቷል።

ዘንድሮ ሊጉን የተቀላቀሉት እና በእኩል 18 ነጥቦች በግብ ክፍያ ብቻ ተበላልጠው 12ኛ እና 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መከላከያ እና አርባምንጭ ከተማ ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ዳግም ድል አግኝተው ሁለተኛውን ዙር በጥሩ ሁኔታ ለመጀመር ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። በዋናነት ደግሞ አካላዊ እና ቀጥተኛ አጨዋወት ላይ ትኩረት በማድረግ ሲጫወቱ የሚታየው ቡድኖቹ ከወራጅ ቀጠናው እምብዛም ስላራቁ የደረጃ እና የነጥብ መሻሻል ለማግኘት ድልን እያሰላሰሉ ጨዋታውን እንደሚቀርቡ ይታመናል።

በአሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመራው መከላከያ ሊጉን ተቀላቅሎ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ድል ሲያገኝ ብዙዎች የተሻለ ግምት እንዲሰጡት አድርጎ ነበር። ከሁለቱ ጨዋታዎች በኋላ ግን በወጥነት ወጥ ያልሆነ ጉዞ በማድረግ ሦስት ጨዋታዎችን ብቻ አሸንፎ በ7ቱ እጅ ሰጥቷል። ከግብ ዘብ እና ከመሐል ተከላካይ ጥምረት ውጪ በአብዛኛው የተለያዩ ተጫዋቾችን የተጠቀመው ቡድኑ እስካሁን ዋነኛ ተመራጮቹን ያገኘ አይመስልም። ለማሳያም በመጀመሪያው ዙር ውድድር በስብስቡ ውስጥ ከነበሩት እና በአጠቃላይ በተጠባባቂ ወንበር ላይም አስቀምጧቸው ከነበሩ አጠቃላይ 23 ተጫዋቾች 19ኙን ቢያንስ ከ60 ደቂቃ በላይ ሜዳ ላይ አጫውቷል። ከምንም በላይ ግን በመከላከያ ቤት ክፍተት የሆነው ጉዳይ አስተማማኝ ግብ አስቆጣሪ መጥፋቱ ነው። ከሁለት በላይ ግብ በስሙ ያለው ተጫዋች ያጣው ክለቡም በዝውውሩ ከኦኩቱ ኢማኑኤል ጋር ተለያይቶ እስራኤል እሸቱ እና ጊኒያዊውን ባዳራ ናቢ ሲላን አስፈርሟል። የእነኚህ የአጥቂ ግዢዎች ምን ያህል ለችግሩ መፍትሄ ይሰጣሉ የሚለው ቢጠበቅም በአማካይ እና ተከላካይ ቦታ ምንተስኖት አዳነ እና አሚኑ ነስሩን እንዲሁም የማጥቃት ባህሪ ያለው አሚን መሐመድን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል። የአራቱ ተጫዋቾች ጥራት፣ ልምድ እና ብቃት ደግሞ ለቡድኑ ጥንካሬ እንደሚሰጥ ይታመናል። ምናልባት ግን ተጫዋቾቹ ካላቸው የአጨዋወት ባህሪ መነሻነት የአቀራረብ ለውጥ ሊከተል እንዳሰበም መናገር ይቻላል።

በመጀመሪያው ዙር የሊጉ ውድድር አንድም ጨዋታ በተከታታይ ያላሸነፈው አርባምንጭ ከተማ በበኩሉ እንደ አዲስ አዳጊ ቡድን ለክፉ የሚዳርገው ውጤት ላይ ባይገኝም በሁለተኛው ዙር እጅግ መሻሻል ያለበት ቦታዎች አሉ። ቡድኑ ከመከላከያ ጋር በዓመቱ መጀመሪያ ከደረሰበት ሽንፈት በመቀጠል በዋንጫ ፉክክር ውስጥ በሚገኙት ወላይታ ድቻ እና ሀዋሳ ከተማ ጋር ብቻ ሲጫወት ብቻ በጠባብ ውጤት ሦስት ነጥብ ከማስረከቡ ውጪ ተረቶ አያውቅም። የአጨዋወት መሠረቱም በጠንካራ መከላከል የተዋቀረ በመሆኑ በአንድም ጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ተቆጥሮበት አያውቅም። በተቃራኒው ከአንድ ግብ በላይ አስቆጥሮ ያሸነፈባቸው ጨዋታዎች ሁለት ብቻ ነው። ይህንን ተከትሎ እንደ ጦሩ በዋናነት መሻሻል ያለበት ክፍሉ ጎል ፊት ያለው መዋቅር ነው። በ15ቱ ጨዋታዎች አጠቃላይ 133 የግብ ሙከራዎችን ቢያደርግም እንደ ቡድን እነዛን ሙከራዎች ወደ ጎልነት የመቀየር ንፃሬው 8.3 በመቶ ብቻ ነው። ይህን ለማስተካከል በሚመስል መልኩ ዘንድሮ በ559 ደቂቃዎች 2 ጎሎችን ለወልቂጤ ያስቆጠረውን አህመድ ሁሴን አስፈርመዋል። የቡድኑ አሠልጣኝ መሳይ ከሚከተሉት ቀጥተኝነት የተሞላበት አጨዋወት መነሻነት አህመድ ያለው አካላዊ ቁመት እና ቅልጥፍና ደግሞ የሁለቱ አካላት ጋብቻ የተቀደሰ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል።

ከዚህ ቀደም ቡድኖቹ ሲከተሉት ከነበረው አጨዋወት መነሻነት የነገው ፍልሚያ ክፍት አጨዋወት ላይኖርበት ይችላል። ቡድኖቹ በድምሩ ተጋጣሚ ላይ ያስቆጠሩት ጎልም (21) የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻውን ካስቆጠረው ግብ በ6 ያንሳል። ከላይ እንደገለፅነውም ጎል ፊት ካለባቸው የስልነት ችግር እና ጠንካራ የመከላከል መዋቅር መነሻነት በጎሎች የታጀበ ፍልሚያ ላያከናውኑ እንደሚችሉ ቀድሞ መናገር ይቻላል።

መከላከያ በነገው ጨዋታ የአዲሱ አቱላን ግልጋሎት በጉዳት ምክንያት የማያገኝ ሲሆን ዛሬ ከፈረመው ጊኒያዊ አጥቂ ባዳራ ናቢ ሲላን ውጪ ያሉት አራቱ አዲስ ተጫዋቾች ግን ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው ተብሏል። አርባምንጭ ከተማ በበኩሉ በጉዳትም ሆነ በቅጣት ምክንያት የሚያጣው ተጫዋች የለም። ብቸኛው አዲስ ፈራሚ አህመድ ሁሴንም በአዲሱ መለያ የመጀመሪያ ጨዋታውን ማድረግ እንደሚችል ተጠቁሟል።

ይህንን ጨዋታ ዮናስ ካሣሁን በመሐል አልቢትርነት ሲመሩት ሶሬሳ ድጉማ እና ሲራጅ ኑርበገን በመስመር ለሚ ንጉሴ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት እርዳታ እንደሚሰጡ ታውቋል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ቡድኖቹ 15 ጊዜ ተገናኝተው 5 ጊዜ መከላከያ ሲያሸንፍ አርባምንጭ ከተማ 4 አሸንፈዋል። በ6 ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።

– ሊጉ ከረጅም ዕረፍት እንደመመለሱ ለዛሬ ግምታዊ አሰላለፍ እንደማይኖረን ለመግለፅ እንወዳለን።