ሪፖርት | የጦሩ እና አዞዎቹ ፍልሚያ በቀዝቃዛ ፉክክር ያለ ግብ ተገባዷል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ባልተስተናገደበት ጨዋታ መከላከያ እና አርባምንጭ ከተማ አቻ ተለያይተዋል።

በዝውውር መስኮቱ በንቃር የተሳተፉት መከላከያዎች ካስፈረሟቸው አምስት ተጫዋቾች ሦስቱን በአሰላለፋቸው አካተዋል። በዚህም አሚኑ ነስሩ፣ ምንተስኖት አዳነ እና እስራኤል እሸቱን በሦስቱ የሜዳ ክፍሎች አሰልፈው በ4-4-2 አደራደር ቅርፅ ወደ ሜዳ ገብተዋል። በተቃራኒው አርባምንጭ ከተማዎችም ብቸኛ ግዢያቸው አህመድ ሁሴንን በጨዋታው ተሳትፎ እንዲያገኝ በማድረግ በ3-5-2 አሰላለፍ ጨዋታውን ቀርበዋል።

አጀማመሩ ጥሩ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር አሰልቺ ሆኖ ታይቷል። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በቁጥር በርከት ብለው በተቃራኒ ሳጥን ሲደርሱ የነበሩት ቡድኖቹም በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ጥንቃቄን ምርጫቸው አድርገው መንቀሳቀን ይዘዋል። በቅድሚያ ግን በ9ኛው ደቂቃ መከላከያ የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ አድርጎ ነበር። በዚህም ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ የመሐል ተከላካዩ በርናንድ ኦቺንግ በግንባሩ ሲያፀዳው ሳጥኑ ጫፍ ያገኘው ኢማኑኤል ላርዬ አክርቶ መቶ ወጥቶበታል።

በመሐል ሜዳ የተጫዋች ቁጥር አብዝተው ሲጫወቱ የነበሩት አርባምንጮች በሩብ ሰዓት እጅግ ለግብ ቀርበው ነበር። አዲሱ ፈራሚ አህመድ ሁሴን ከሙና በቀለ የደረሰውን የተከላካይ ጀርባ ኳስ አስቆጠረው ተብሎ ቢጠበቅም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ኳስ ቶሎ ቶሎ መነጣጠቅ የበዛበት ፍልሚያ ቀጣዩን የግብ ማግባት ሙከራ ያስተናገደው በ35ኛው ደቂቃ ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃም ወርቅይታደስ አበበ ከርቀት ቡድኑን መሪ ለማድረግ ዳድቶ ሳይሳካለት ቀርቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም በሁለቱም ቡድኖች በኩል አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳይደረግበት ያለ ግብ ተገባዷል።

በቀዝቃዛነቱ የቀጠለው የሁለተኛው አጋማሽም ከሙከራዎች የራቀ ነበር። ሁለቱም ቡድኖች ግብ ለማስቆጠር ፍላጎት ያላቸው ይመስል የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች አከታትለው ቢለውጡም መፍታታት የሌለው ጨዋታ በጥብቅነቱ መጓዙን ይዟል። ከበርካታ ደቂቃዎች ጥበቃ በኋላም በ74ኛው ደቂቃ የተገኘን የቅጣት ምት ግሩም ሀጎስ ሲመታው ተቀይሮ የገባው ኤርሚያስ ኃይሉ ጨርፎ ቡድኑን መሪ ሊያደርግ ተቃርቦ ነበር።

ከተከላካይ ጀርባ ለመሮጥ እና የግብ ዕድሎችን ለማግኘት ያሰቡት አርባምንጮች በበኩላቸው በ79ኛው ደቂቃ አህመድ ሁሴንን ተክቶ በገባው ፍቃዱ አማካኝነት የክሌመንትን መረብ ለማግኘት ጥረው ተመልሰዋል። ከሙሉ ደቂቃው ለግብ የቀረበ የሚመስለው ብቸኛ ሙከራ ደግሞ በ81ኛው ደቂቃ ተስተናግዷል። በዚህም ከመዓዘን ምት ቢኒያም በላይ ያሻገረውን ኳስ ግሩም ሀጎስ በቅርቡ ቋሚ በመቆም ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ሞክሮ ለጥቂት ወጥቶበታል። ጨዋታውም በአቻ ውጤት ፍፄሜውን አግኝቷል።

ያለ ግብ የተጠናቀቀው ጨዋታን ተከትሎ መከላለያ ነጥቡን 19 አድርሶ ወደ 11ኛ ደረጃ ከፍ ሲል አርባምንጭም በተመሳሳይ በ19 ነጥብ በግብ ክፍያ በልጦ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።