ቅድመ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

የመዲናይቱን ትልቅ ደርቢ የተመለከተ ቅድመ ዳሰሳ በሚከተለው መልኩ አሰናድተናል።

በደረጃ ሰንጠረዡ አካፋይ እና አናት ላይ ሆነው ነገ የሚገናኙት ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጠንካራ ፉክክር የሚታይበት ፍልሚያ እንደሚያደርጉ ብዙዎች ይጠብቃሉ። ያለፉትን አራት ጨዋታዎች አንድም ድል ያላገኘው ኢትዮጵያ ቡና የራቀውን ድል በማሳካት ወደ አሸናፊነት ለመምጣት እና የደረጃ መሻሻል ለማግኘት ነገ ተግቶ እንደሚጫወት እሙን ነው። የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ ባለመሸነፍ ግስጋሴው በመቀጠል አውራነቱን ለማጠናከር እና ከበታቾቹ ያለውን የነጥብ ልዩነት እያሰፋ ለመሄድ በጠንካራ እንቅስቃሴ ጨዋታውን እንደሚቀርብ ይታሰባል።

በአሠልጣኝ ካሳዬ አራጌ የሚመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከላይ እንደገለፅነው ወቅታዊ ብቃታቸው አስተማማኝ አይደለም። ከሲዳማ ቡና ጋር አቻ በተለያዩበት ጨዋታ የወትሮ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመያዝ ቢጫወቱም በመጨረሻው የማጥቃት ሲሶ ያላቸው ተፅዕኖ ፈጣሪነት እጅግ የወረደ ነበር። ባለፉት ዘጠኝ ጨዋታዎች ከአንድ ጎል በላይ አንድ ጊዜ ብቻ ያስቆጠረው ቡድኑ ጎል ፊት ዓይናፋር እየሆነ መጥቷል። በጠቀስነው የሲዳማ ጨዋታ ጥቃታቸው በግቡ ትይዩ (ዘጠኝ ቁጥር ቦታ) ኳስ የሚቀበል እና አደገኛ ዕድሎችን የሚፈጥር ስል ሰው አለመኖሩን ተከትሎ በግራው በኩል ብቻ የግብ ምንጫቸውን እንዲያደርጉ እና ተገማች እንዲሆኑ አድርጎት ነበር።

በተቃራኒ የቀኝ መስመር በኩል ደግሞ አጥቂው (አቤል) ወደ መሐል ስለሚገባ የቀኝ ተከላካዩ (ኃይሌ) ወደፊት ሲሄድ ቦታውን መሐሪ ለመጠቀም እየጣረ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሲያዘነብል ታይቷል። የቡድኑ አዳኝ እና ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ አቡበከር ናስር ግን የተለመደ ተዐምራዊ እግሮቹን ተጠቅሞ በጨዋታው ያላቸውን ቆይታ አርዝሞ ነበር። ተጫዋቹ በነገው ጨዋታም ለጊዮርጊስ ተከላካዮች ተቀዳሚ የትኩረት ማዕከል መሆኑን ሳንጠራጠር መግለፅ እንችላለን። አቡበከር በዘጠኝ ቁጥርም ሆነ በመስመር ሚና ወደሜዳ ቢገባ ራሱ የሚፈጥራቸው አጋጣሚዎች እንዲሁም ለአጋሮቹ የሚያመቻቻቸው ቦታዎች ከፍተኛ ዋጋ አላቸው።

አንድም ጨዋታ እስካሁን ያልተረታው ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ ከኢትዮጵያ ቡና በተቃራኒ በምርጥ ብቃቱ ላይ ያለ ቡድን ነው። ለማሳያም ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ሦስት ጎል እያስቆጠረ ሦስት ነጥብ ሸምቷል። በሰበታው ጨዋታም በተሻለ የኳስ ቁጥጥር አስር ጊዜ የተጋጣሚን መረብ ለማግኘት ሞክሮ አምስቱን ዒላማቸውን አስጠብቆ እንደገለፅነው ሦስቱን ከመረብ አገናኝቷል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ እየታየ ያለው ጨዋታን ከፍ ባለ ፍጥነት እና ፍላጎት መጀመር ዋጋ እያስገኘ ያለ ጉዳይ ይመስላል። በመጨረሻው ጨዋታ በሁለቱም አጋማሾች የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ተደጋጋሚ ዕድሎችን በመፍጠር ከሦስቱ ሁለቱን ግብ አስቆጥሯል። በተወሰነ መልኩ ሰበታ ወደ ራሱ የግብ ክልል አፈግፍጎ በሚጫወትበት ጊዜ በመጠኑ የተቸገረ ቢመስልም ልኬታቸውን የጠበቁ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶችን በማዘውተር ፍሬታማ ለመሆን ሞክሯል። በተቃራኒው ኳስ ዘለግ ላለ ጊዜ የሚይዝ ቡድን ሲገጥመው ግን በቀጥተኛ እንዲሁም የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት በግለሰቦች ብቃትም ሆነ በቡድናዊ መዋቅር የተሟላ ይዟታ ያለው ይመስላል። ከዚሁ ከቡድናዊ አጨዋወት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው እስማኤል ኦሮ-አጎሮ ሳይኖር ከሦስት ተጫዋቾች ግብ ማግኘቱ የሚደነቅ ነው። በተለይ ከፊት የተሰለፈው አማኑኤል ገብረሚካኤል ማግባት እንዲሁም ጥቃቶች ላይ መሳተፍ መጀመሩ ለቡድኑ ሁነኛ አማራጭ መሆኑን በአንድ ጨዋታም ቢሆን ተመስክሯል።

በከፍተኛ የደጋፊዎች ድባብ እንደሚደረግ የሚጠበቀው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ሊኖረው እንደሚችል ይገመታል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በተቃራኒው የቡናን የኳስ ፍሰት በማጨናገፍ ቀጥተኝነት የተሞላበት አጨዋወት ማድረግን ምርጫው እንደሚያደርግ ይታሰባል። ሀይደርን ጨምሮ ለተከላካዮች ሽፋን በመስጠት የተዋጣላቸው አማካዮቹም ተፈላጊዎቹን ኳሶች በመላክ ጥሩ ስለሆኑ የቡና የቤት ሥራ መሆናቸው አይቀሬ ነው። በሰበታው ጨዋታ በግራ መስመር ተከላካይነት የተሰለፈው አዲሱ ተጫዋች ያሬድ ሀሰን ነገም በመጀመሪያ አሰላለፍ ቦታ የሚያገኝ ከሆነ ግን ገና ከቡድኑ ጋር የመዋሀጃ ጊዜ ካለማግኘቱ ጋር ተያይዞ የቡድኑ ስስ ጎን ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። ኢትዮጵያ ቡና በቀኝ መስመር በማጥቃቱ ረገድ ደከም ያለ መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ ፈረሰኞቹ ብዙም እንዳይጨነቁ ሊያደርግ ይችላል። ቡናማዎቹ በዋናነት መጠንቀቅ ያለባቸው ጉዳይ ደግሞ ለመልሶ ማጣቃት ያላቸውን መጋለጥ በማስተካከሉ ረገድ ነው። ከዚህ ትልቅ ስጋት ውጪ ግን በግል ጨዋታን የመወሰን ብቃት ያላቸው ተጫዋቾች የሚኖራቸው ተሳትፎ ለመሪው ቡድን ትኩረት እንደሚሻ አመላካች ነው።

በጨዋታው የኢትዮጵያ ቡናው ተከላካይ ቴዎድሮስ በቀለ ከጉዳት ሲመለስ አቤል እንዳለ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆኗል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ግብ ጠባቂው ተመስገን ዮሐንስ ፣ እስማኤል ኦሮ አጎሮ እና ቡልቻ ሹራ በጉዳት አሁንም አይኖሩም፡፡

ጨዋታው በኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ አማካይነት የሚመራ ሲሆን
ትግል ግዛው እና ሸዋንግዛው ተባባል በረዳትነት አሸብር ሶቦቃ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ 43 ጊዜ ተገናኝተዋል። በእነዚህ ግንኙነቶች ጊዮርጊስ 20 ጊዜ ድል ሲቀናው ቡና ደግሞ 7 ጊዜ አሸንፏል ፤ 16 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል።

– በ43ቱ የሁለቱ ቡድኖች ግንኙነት በድምሩ 84 ጎሎች መረብ ላይ አርፈዋል። 56ቱን ግብ በማስቆጠር ፈረሰኞቹ ቀዳሚ ሲሆኑ ቡናማዎቹ ደግሞ 28 ኳሶችን ከመረብ አዋህደዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

አቤል ማሞ

ኃይሌ ገብረተንሳይ – አበበ ጥላሁን – ወንድሜነህ ደረጄ – ስዩም ተስፋዬ

ሮቤል ተክለሚካኤል – አማኑኤል ዮሐንስ – ዊሊያም ሰለሞን

ሚኪያስ መኮንን – አቡበከር ናስር – አስራት ቱንጆ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ቻርለስ ሉክዋጎ

ሱሌይማን ሀሚድ – ምኞት ደበበ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ሔኖክ አዱኛ

ያብስራ ተስፋዬ – ጋቶች ፓኖም – ሀይደር ሸረፋ

አቤል ያለው – አማኑኤል ገብረሚካኤል – ቸርነት ጉግሳ