የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 0-4 ቅዱስ ጊዮርጊስ

በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት ከተጠናቀቀው የዛሬው ሸገር ደርቢ በኋላ አሰልጣኞች ይህንን ብለዋል።

አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለጨዋታው ክብደት

” ከከባዶቹ አንዱ ነው ፤ ከውጤቱ አንፃር ሲታይ ለእኛ ከባድ ነበር። ሁለት ጊዜ ሽንፈት አስተናግደናል። ግን እያንዳንዱ ጨዋታ ለእኛ ለባድ ነው። ይሄ ግን ከውጤትም አንፃር ሲታይ ከደርቢነቱም አንፃር ሲታይ ከባድ ነበር ለእኛ።

ስለጊዮርጊስ ከኳስ ውጪ ጫና መፍጠር

” ጫናው በዛ መልኩ ዘጠና ደቂቃ እንደማይቀጥል እናውቃለን። የመጀመሪያዎቹ አስር አስራአምስት ደቂቃዎች ላይ ከማንኛውም ቡድን ስንጫወት ያ እንደሚኖር እንገምታለን ፤ ገና አቅሙ አለ ጉልበቱ አለ። እዛ ላይ ትንሽ አለመረጋጋት ነበር። በግራ በኩል ያጫወትነው ልጅ ከታዳጊ የመጣ ነው። ከጨዋታው ክብደት አንፃር አቅሙ እና ችሎታው አለው ግን በሥነልቦናው ዝግጁ መሆን ስለሚያስፈልግ ትንሽ ድክመት ይታይ ነበር። ያም ቢሆን የእኛ ኃላፊነት ነው። በጫና ውስጥ ለማለፍ ሥነልቦናውን የመቋቋም ጉዳይ ፤ እንደዛ ዓይነት ክፍተቶች ነበሩ።

የሚፈልጉትን ክፍተቶች ስለማግኘታቸው

“ክፍተቱ አለ። ለምሳሌ ያህል በሦስት ሰው ጫና ሲፈጥሩ አንድ የሚተዉልህ ሰው አለ። ግን ያንን ሰው አይተን በአግባቡ ያለመጠቀም ጉዳይ ነው የእኛ ድክመት። ከመሀል ተጨማሪ ሰው አምጥተው በአራት ሰው ጫና ሲፈጥሩ አንድ ከመሀል የሚተዉልን ሰው አለ። በዛ በኩል እየወጣን ነበር። የሚበላሹ ካሶች ነበሩ እየወጣንም ነበር። ክፍተቱ አለ ግን ክፍተቱን በአግባቡ የመጠቀም እና ያለመጠቀም ጉዳይ ነው። ያ ነበር ድክመታችን።

ጫና ውስጥ ስለመሆናቸው

“ቡና ውስጥ ሁሌም ጫና አለ ፤ ተጫዋችም ሆኜ ስለማውቀው። አንድ ታሳቢ መሆን ያለበት ነገር ግን ደጋፊው ውጤት ሲጠፋ ያዝናል ፣ ሥራ አመራር ቦርዱ ያዝናል ፣ ኮቺንግ ስታፉም ተጫዋቹም እንደሚያዝን ግንዛቤ መኖር አለበት ፤ ደጋፊውም ጋር ሥራ አመራር ቦርዱም ጋር። እነሱ ብቻ እንደሚያዝኑ አድርገው ማሰብ የለባቸውም ፤ ያ ሀዘን ያ ቁጭት እኛም ጋር አለ። ይሄ ግንዛቤ እንዲኖር ነው በተረፈ ግን ጫናው ሁል ጊዜ ቡና ውስጥ አለ። እያሸነፍክ ለቻምፒዮንነት እየሄድክም ሆነ እየተሸነፍክ ጫናው ሁል ጊዜ ቀጣይኑት ያለው ነው። በዛ ጫና ውስጥ ተጫዋችም ፣ አሰልጣኙም ፣ ሥራ አመራር ቦርዱም ማለፍ ግድ ነው።”

አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ያሰቡትን ስለማሳካታቸው

“100 ፐርሰንት ተሳክቷል። አጥቅተን ለመጫወት ነበር ያሰብነው። ያ ተሳክቶልኛል ፤ ልጆቼን በዚህ አጋጣሚ በጣም ነው የማመሰግናቸው።

ስለጨዋታ ዕቅዳቸው

“ብዙ ሰርተንበት ፣ ብዙ ለፍተንበት ነው። ምን ማድረግ እንዳለብን ሰርተንበት ነው የመጣነው። የሰራንበትንም ልጆቼ ግብዓቱን ስላሳዩኝ በጣም ደስ ብሎኛል። ማድረግ የሚገባንን በደንብ ደጋግመን ሰርተነው ነበር። ይሄንን ዛሬ በትክክል ሰርተው 4-0 አሰንፈናል።

ስለቸርነት ጉግሳ

“ትልቅ አቅም ያለው ተጫዋች ነው። እንደቡድን ለቅዱስ ጊዮርጊስ ይጠቅመናል ብዬ ነው መጀመሪያም ያመጣሁት። እንደቡድን የተነጋገርንበትን ሰርቶ ጎልም አግብቷል ፤ ኳሶችንም አቀብሏል። ጥሩ ጨዋታ ተጫውቷል ፤ እንደውም ከዚህ በላይ ማግባት ነበረብን። የሳትናቸውም ኳሶች ነበሩ። አቅም ያላቸው ተጫዋቾች ማድረግ የሚገባቸውን ሲያደርጉ ይህንን ግብዓት ነው የምታገኘው።

ከቡና ጋር መጫወት እንደቀለላቸው

“ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ቡና ሲጫወቱ ሁሌ ደርቢ ነው። የደርቢ ስሜት ትልቅ ስሜት አለው። ድባቡ በጣም ደስ ይላል። በዚህ ድባብ እግርኳስ ስትጫወት ምን ያህል አርኪ እንደሆነ ነው ለተጫዋቾቹም ለደጋፊውም የሚሰማው ስሜት። በዛ ላይ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ሁለቱ ዞር ላይ 8 ጎል አግብተን ለእነሱ ይህንን ሸልሜያቸውለው ብዬ አስባለሁ።

ቻምፒዮንነትን ስለማሰባቸው

“እኔ ወደፊት ያለውን ጨዋታ ነው የማየው እና ዛሬ ይሄ አልቋል ነገ ከድሬዳዋ አለ ፤ የድሬዳዋ ግብዓት ሌላ ነው። ስለዚህ ከፊት ያለውን ጨዋታ አስቤ ስለመዘጋጀት ነው የማስበው።”