ሪፖርት | ፀጋዬ አበራ አርባምንጭን ባለድል አድርጓል

ፀጋዬ አበራ በደመቀበት ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ድል በማስመዝገብ ደረጃቸውን ወደ ስምንተኛ ማሻሻል ችሏል።

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ከመከላከያ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስባቸው የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በዚህም ሀቢብ ከማል ፣ መሪሁን መስቀሉ እና አንዱዓለም አስናቀን በተካልኝ ደጀኔ ፣ አቡበከር ሻሚል እና በላይ ገዛኸኝን የተኩ ሲሆን በአንፃሩ አሰልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ ደግሞ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራው የመጀመሪያ ተመራጭ ተጫዋች ዝርዝር ላይ ተከላካዩን ልመንህ ታደሰ አስወጥተው በምትኩ አሰጋኸኝ ጴጥሮስን ብቻ ለውጠው ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።

አርባምንጮች የተሻሉ በነበረበት የመጀመሪያ አጋማሽ ቡድኑ የአንድ ለአንድ ግንኙነቶችን ሀይል ቀላቅለው በማሸነፍ ሆነ በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመድረስ እድሎችን በመፍጠር ረገድ የተሻሉ ነበሩ።

ከወትሮው በተሻለ ተደጋጋሚ ዕድሎችን መፍጠር የቻሉት አርባምንጭ ከተማዎች በ10ኛው ደቂቃ ላይ ሙና በቀለ ያሻማውን የማዕዘን ምት በአዲስ አበባ ተጫዋቾች ሲመለስ አቡበከር ሻሚል ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችበት እንዲሁም በ16ኛው ደቂቃ ሙና ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ አህመድ በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ የላካት እና በተከላካዮች የተመለሰችበት ኳስ ቡድኑ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ከፈጠሯቸው አጋጣሚዎች አደገኞቹ ነበሩ።

በአጋማሹ ከአርባምንጭ አንፃር በብዙ መመዘኛዎች ሁለተኛ የነበሩት አዲስ አበባ ከተማዎች መሀል ሜዳ ላይ በነበሩ ፍልሚያዎች ለአርባምንጭ ከተማዎች እጅ ለመስጠት መገደዳቸው ጨዋታውን በሚፈልጉት መልኩ ተቆጣጥረው እንዳይጫወቱ ተግዳሮት ሲፈጥርባቸው ተመልክተናል።

በ23ኛው ደቂቃ አርባምንጭ ከተማዎች በሜዳው የላይኛው ክፍል ያቋረጡት ኳስ ተጠቅመው የፈጠሩት ዕድል አህመድ ሁሴን ወደ ግብ ቢልክም ኳሷን ዳንኤል ተሾመ አድኗታል የተመለሰችውን ኳስ በቅርብ ርቀት የነበረው ፀጋዬ አበራ ዳግም ቢሞክርም ኳሶን ዳንኤል ተሾመ በድጋሚ ሊያድንበት ችሏል። በዚህ ሂደት የተገኘውን የማዕዘን ምት ደግሞ ሙና በቀለ ያሻማውን ኳስ ፀጋዬ አበራ በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገች ግብን አስቆጥሯል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ በነበሩት ደቂቃዎች አርባምንጭ እንደ መጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የግብ አጋጣሚዎችን ባይፈጥሩም በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የተሻለው ቡድን እንደነበር ተመልክተናል ፤ በአንፃሩ አዲስ አበባዎች በአጋማሹ ምንም አይነት ዒላማውን የጠበቀ የግብ ዕድል ሳይፈጥሩ አጋማሹን አጠናቀዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ መሐመድ አበራን እና ቢኒያም ጌታቸውን ቀይረው ያስገቡት አዲስ አበባ ከተማዎች የቅርፅ ለውጥ በማድረግ ፍፁም እና መሐመድን ከመስመር እንዲነሱ እንዲሁም ሪችሞንድ እና ቢኒያምን ደግሞ በሁለት የፊት አጥቂነት በመጠቀም የማጥቃት ጨዋታቸውን ለማሻሻል ጥረት አድርገዋል።

በቅያሬዎቹ የተነቃቃ የሚመስለው የአዲስ አበባ ማጥቃት አስፈሪ የነበረባቸውን የጨዋታ ደቂቃዎች መመልከት ችለናል። በዚህም 56ኛው ደቂቃ ላይ በላይኛው የሜዳ ክፍል የነጠቁትን ኳስ ሪችሞንድ ለቢኒያም ያቀበለውን ኳስ ተጫዋቹ ከሳጥኑ ጠርዝ በግራ እግሩ አክርሮ በመምታት ወደ ግብ የላከውን ኳስ ሳምሶን አሰፋ በግሩም ሁኔታ አድኖበታል ፤ በዚህ እንቅስቃሴ ሂደት የተገኘችውን የማዕዘን ምትን ሳሙኤል አስፈሪ ያሻማውን ኳስ ሪችሞንድ አዶንጎ በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን ወደ ጨዋታው የመለሰች ግብ አስቆጥሯል።

በግቧ የተነቃቁ የሚመስሉት አዲስ አበባዎች በደቂቃዎች ልዮነት ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ተቃርበው ነበር ፤ ፍፁም ጥላሁን በግሩም ሁኔታ ያሳለፈለትን ኳሶ ሳጥን ውስጥ የነበረው ሪችሞንድ ወደ ግብ ቢልክም ሳምሶን አዳነ በቀላሉ ይዞበታል። አዲስ አበባዎች ተጨማሪ ግብ የሚያስቆጥሩ ቢመስልም አርባምንጭ ከተማዎች ሳይጠበቁ በ65ኛው ደቂቃ ላይ ሙና በቀለ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ፀጋዬ አበራ በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን ዳግም ቀዳሚ ያደረገች ግብ አስቆጥረዋል።

በደቂቃዎች ልዮነት ሀቢብ ከማል የአርባምንጭ ከተማዎችን መሪነት ወደ ሦስት ማሳደግ የሚችል ወርቃማ አጋጣሚን በመልሶ ማጥቃት ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ሁለተኛ ግብ ከተቆጠረች በኃላ አርባምንጮች አሉታዊ ቅያሬዎችን በማድረግ ሆነ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው በመከላከል ውጤቱን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል ፤ በአንፃሩ አዲስ አበባ ከተማዎች የማጥቃት ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም በ68ኛው ደቂቃ ቢኒያም ጌታቸው በግንባር ገጭቶ የሞከራት እንዲሁም በ78ኛው ደቂቃ ሪችሞንድ አዶንጎ ከሳምሶን አሰፋ ጋር 1ለ1 ተገናኝቶ ካመከናት ኳስ ውጭ በቂ ዕድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

ጨዋታውን በድል የተወጡት አርባምንጭ ከተማዎች ነጥባቸውን ወደ 22 በማሳደግ ወደ 8ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ሲችሉ በአንፃሩ አዲስ አበባ ከተማዎች አሁንም በ15 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።