ቅድመ ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ሌላኛውን የሳምንቱን ትኩረት ሳቢ ጨዋታ የተመለከትንበት ዳሰሳችን እንዲህ ይነበባል።

ድቻ እና ሀዋሳ በሰንጠረዡ አናት ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸው ብቻ ሳይሆን በመጨረሻ ጨዋታዎቻቸው ያሳዩት አቋም የነገው ፍልሚያ የሚያገኘውን ትኩረት ከፍ የሚያደርግ ነው። ሩጫው ካልቀዘቀዘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደነበረበት ከመመለስ ባሻገር ሀዋሳ ሁለተኝነቱን ለመያዝ ወላይታ ድቻ ደግሞ ይህንን ደረጃውን ለማስጠበቅ ይጫወታሉ። በመጨረሻ አምስት ጨዋታቸው አንድ አንድ ጊዜ ብቻ ሽንፈት ከገጠማቸው ቡድኖች ውስጥ ማን እጅ ይሰጣል የሚለውን የነገው ዘጠና ደቂቃ ያሳየናል። በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ የሚደረገው ይህ ጨዋታ ቡድኖቹ ለቻምፒዮንነት ከሚያደርጉት ጥረት ባለፈ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫው ተሳትፎ ዳግም ወደ አህጉራዊ ውድድሮች ለመመለስ ላላቸው ህልምም ወሳኝ መሆኑ ግልፅ ነው።

ከአዳማው የአቻ ውጤት መልስ ሁለተኛውን ዙር ጅማ ላይ ድል በማስመዝገብ የጀመረው ሀዋሳ ከተማ በጨዋታው በርከት ያሉ ጠንካራ ጎኖቹን አሳይቷል። በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች መረቡን ያላስደፈረው ቡድኑ የተከላካይ መስመር አደረጃጀቱ እና የአማካይ ክፍል ሽፋኑ ለተጋጣሚ በቀላሉ ክፍተት እንደማይሰጡ አሳይተዋል። የአሰልጣኝ ዘርዓይ ቡድን በወረደ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ፈጣን መልሶ ማጥቃት የመሰንዘር አቅም እንዳለውም በጅማው ጨዋታ አመላክቷል። በእርግጥ ይህንን ለማድረግ ብዙ ደቂቃዎች ይፍጁበት እንጂ በተለይም ከመሀል የሚነሱ እንዲሁም የግራው የቡድኑ ወገን የሚፈጥራቸው አጋጣሚዎች አስፈሪ ነበሩ።

ወላይታ ድቻም በፊናው ድሬዳዋ ከተማን የረታበት ጨዋታ የራሱን ስሪት በሚገባ ያንፀባረቀበት ነበር። 4-3-3 እና 3-5-2ን በሁለት አጋማሾች በተጠቀመበት ጨዋታ የተጋጣሚው የኳስ ቁጥጥር አቅም እንዲያጣ ማድረግ ችሏል። የአሰልጣኝ ፀጋዬ ቡድን በማጥቃቱ ረገድ ያለበት የፈጠራ ውስንነት እንዳለ ቢሆንም የድሬዳዋው ድል ወላይታ ድቻ ከቆሙ ኳሶች ምን ያህል አደጋ መፍጠር እንደሚችል ያሳየበት ነበር። ከዚህ ውጪ ግብ ካስቆጠረ በኋላ በጥልቀት በመከላከል የግብ አጋጣሚዎች እንዳይፈጠሩ ያደረገበት መንገድም በበጎዉ የሚነሳ ነው። በነገው ጨዋታም ድቻ በተመሳሳይ ጥንቃቄ አዘል አቀራረብ እንደሚኖረው ሲገመት ከሀዋሳ የማጥቃት ጥንካሬዎች አንፃር ትኩረት ሳቢ ፍልሚያዎች የሚጠበቁባቸው ቦታዎች ይኖራሉ።

በነገው ጨዋታ ሀዋሳ የተለየ መልክ ይዞ እንደሚቀርብ ይጠበቃል። ራሱን ለፈጣን ጥቃት አዘጋጅቶ ከዋለበት የጅማው ጨዋታ በተለየ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን በመያዝ በተሳኩ ቅብብሎች ክፍተቶችን መፈለግ የኃይቆቹ ትኩረት እንደሚሆን ይገመታል። በዚህ ሂደት ውስጥ የወላይታ ድቻ ጥንቃቄን የሚያስቀድም አቀራረብ በሜዳው ስፋት በአምስት ተጫዋቾች በቁመትም በቅርብ ርቀት በሚንቀሳቀሱ የተከላካይ እና የኋላ መስመሮች መሀል ጊዜ እና ክፍተትን ማግኘት የሀዋሳዎች ዋነኛው ፈታና ነው። በወንድምአገኝ ኃይሉ የሚመራው የሀዋሳ አማካይ ክፍል ድንቅ ጥምረት ከፈጠሩት ንጋቱ ገብረስላሴ እና ሀብታሙ ንጉሴ ጀርባ ኳስን ለማድረስ የሚሄድበት መንገድ ብርቱ ፍልሚያ እንደሚደረግበት ይጠበቃል።

ወላይታ ድቻዎች በነገውም ጨዋታ ቢሆን የቆሙ ኳሶቻቸው ትኩረት መሳባቸው አይቀርም። እንደ አንተነህ ጉግሳ ያሉ ጥሩ የግንባር ኳስ ተጠቃሚዎች የአየር ላይ ኳሶችን ለመጠቀም መጣራቸው አይቀሬ ነው። ጥሩ የቆሙ ኳሶችን በማድረሱ በኩል ያሬድ ዳዊት ተጠባቂ ሲሆን በክፍት ጨዋታም እርሱ በሚሰለፍበት የድቻ የቀኝ እና የሀዋሳ የግራ ክፍል ከፍ ባለ የማጥቃት ጉልበት ከሚጫወተው መድኃኔ ብርሀኔ ጋር የሚኖራቸው ፍልሚያ ሌላው የትኩረት ሳቢ የሜዳው ክፍል ነው።

ፊት መስመር ላይ ሀዋሳ 14 ግቦች ባሉት የብሩክ ፣መስፍን እና ኤፍሬም ጥምረት ወላይታ ድቻም 12 ግቦችን ካመረተው የስንታየሁ ፣ ቃልኪዳን እና ምንይሉ ጥምረት ግቦችን ይጠብቃሉ። እዚህ ላይ በሀዋሳ በኩል ተባረክ ሄፋሞም በመጨረሻው ጨዋታ ጥሩ አቅም እንዳለው ማሳየቱ መረሳት የለበት። ዋናው ነጥብ ግን ሁለቱም ካላቸው የመከላከል ጥንካሬ አንፃር በታክቲትክ የታጠረ ሊሆን ከሚችለው ጨዋታ ውስጥ በርካታ የግብ ዕድሎች መፍጠር ከባድ መሆኑ ነው።

ስለሆነም ሁለቱ አሰልጣኞች በሚመርጡት አደራደር ከላይ ከጠቀስናቸው ተጫዋቾች ውስጥ ይዘው የሚገቡት የአጥቂዎች ጥምረት ዕድሎችን ወደ ግብነት የመለወጥ ንፃሬው ከፍተኛ ሆኖ መገኘት ይኖርበታል። ይህ ነጥብ ይበልጥ ከተከላካይ መስመር ጀርባ እንደልብ የመሮጫ ክፍተት ላያገኙ ለሚችሉት ሀዋሳዎች ሲሰራ በጨዋታው የተሻለ የመልሶ ማጥቃት ዕድል ሊኖራቸው የሚችሉት የጦና ንቦቹም የስንታየሁ አለመኖር ተጨምሮበት የፊት መስመር ተሰላፊዎቻቸው ከሚያገኙት ዕድል አንፃር ግብ የሚያስቆጥሩበት ብዛት የሚያኩራራ አለመሆኑንን መርሳት አያስፈልግም።

ኃይለየሱስ ባዘዘው የመሀል ዳኛ ፣ ትግል ግዛው እና ለዓለም ዋሲሁን ረዳቶች ሊዲያ ታፈሰ ደግሞ አራተኛ ዳኛ በመሆን ጨዋታውን ለመምራት ተመድበዋል።

ሀዋሳ ከተማ በመጨረሻው የጨዋታ ቀን ህመም ገጥሞት የነበረው መስፍን ታፈሰን መልሶ ሲያገኝ ሌላ የጉዳትም ሆነ የቅጣት ዜና የለበትም። ስንታየሁ መንግሥቱ ለአንድ ወር ከሜዳ በሚርቅባቸው ወላይታ ድቻዎች በኩል ደጉ ደበበ ከህመም መልስ ወደ ልምምድ ቢገባም ነገ የመሰለፍ ዕድሉ ዝቅተኛ ነው።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በሊጉ 15 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ 7 በማሸነፍ ቀዳሚነቱን ሲይዝ ሀዋሳ 4 ጨዋታ አሸንፏል። በአራት አጋጣሚዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ ድቻ 17 ሀዋሳ ደግሞ 15 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዋሳ ከተማ (3-4-3)

ዳግም ተፈራ

አዲስዓለም ተስፋዬ – ላውረንስ ላርቴ – ፀጋሰው ድማሙ

ዳንኤል ደርቤ – ወንድማገኝ ኃይሉ – በቃሉ ገነነ – መድሃኔ ብርሃኔ

ኤፍሬም አሻሞ – ብሩክ በየነ – መስፍን ታፈሰ

ወላይታ ድቻ (3-5-2)

ፅዮን መርዕድ

በረከት ወልደዮሐንስ – አንተነህ ጉግሳ – መልካሙ ቦጋለ

ያሬድ ዳዊት – ሀብታሙ ንጉሴ – ንጋቱ ገብረስላሴ – እድሪስ ሰዒድ – አናጋው ባደግ

ምንይሉ ወንድሙ – ቃልኪዳን ዘላለም