የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 1-1 ወላይታ ድቻ

በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረ ግብ በአቻ ውጤት በተጠናቀቀው ጨዋታ አሰልጣኞች ይህንን ብለዋል።

አሰልጣኝ ዘርዓይ መሉ – ሀዋሳ ከተማ

ስለጨዋታው

“መጀመሪያም እንደተናገርኩት በተደጋጋሚ የሚመጡት በቆመ ኳስ ነው። አላስፈላጊ ፋዎሎች ልንሰራም ላንሰራም እንችላለን። በነዛ የቆሙ ኳሶች ነው የሚመጡት ፤ ከዛ ውጪ አማራጭ የላቸውም የገባውም እንደዛው ነው። ትንሽ ስሜታዊ የሚደርገው ኳሱን መጨረስ እንችል ነበር። በቅያሪያችንም እርግጥኛ ስለነበርን ነበር ወደ መከላከሉ ያደላነው። አጥቅተን ብንጫወት ጎሎች ማግባት እንችል ነበር። ዞሮ ዞሮ አንዳንዴ እግርኳስ ነው ይከሰታል። በሰራንበት በቆመ ኳስ ገብቶብናል። የማርኪንግ ችግር ነው። ውጤቱን በራሳችን እጅ ነው ያጣነው ማለት ይቻላል።

በሁለተኛው አጋማሽ ማጥቃትን ስላለመምረጣቸው

“አላሰብንም ምክንያቱም እነሱም ሲመጡ የነበሩት በረጃጅም ኳሶች ነው። ያንን ለመቆጣጠር ወደ ኋላ ወርደህ ነው ኳሱን መያዝ ያለብህ። ያንን ነበር ስናደርግ የነበረው። ባለቀ ሰዓት ሲመጡ የነበረው ቅያሪ ካደረግን በኋላ ነው። መቆጣጠር ይቻል ነበር ፤ በጣም ቀላል ነበር። አንድ ለአንድ ብንሆን ምንም የሚፈጠር ነገር አይኖርም ነበር። እነሱ ዕድለኞች ናቸው ማለት ይቻላል።

ስለፉክክሩ

“ጨዋታው ገና ነው ፤ 13 ጨዋታ ይቀራል። ምን እንደሚፈጠር እየታወቅም። እነሱም እኛም አሁንም ዕድሉ በእጃችን ነው። ምንም የተለየ ነገር የለም። ብንሸናነፍ ነበር የምንራራቀው። ቀጣይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ደረጃውን ለመያዝ እንሞክራለን።

ስለደጋፊዎች

“ደጋፊዎቻችን በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረው ጎል ቢያዝኑም በእንቅስቃሴው ደስተኛ እንደሚሆኑ አስባለሁ። የተፈጠረው በእግርኳስ የሚያጋጥም ነው በቀጣይ ጨዋታዎች እንደምንክስ አስባለሁ።”

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም – ወላይታ ድቻ

ስለጨዋታው

“በአጠቃላይ ቡድናችን እንደቡድን በሁሉም ነገር የተሻለ ነበር ማለት ይቻላል። ኳስ ይዘን ሜዳውን አስፍተን ለመጫወት ሞክረናል የነበረን ታታሪነት ቀላል የሚባል አልነበረም። ጥሩ በነበርንበት ስዓት ግብ ገብቶብን የመደናገጥ ነገር ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ የአደራደር ለውጥ አድርገን ነው የገባነው። ኳሱን መሬት አስይዘን ለመጫወት ሞክረናል ምክንያቱም በክሮስ ማጥቃት አልቻልንም ፤ በረኛቸው ረጅም ስለሆነም። የአጥቂ ቁጥር አብዝተን ሜዳውን በስፋት ተጠቅመን በአጠቃላይ በሁለተኛው አጋማሽ ከፍተኛ ብልጫ ነበረን ማለት እችላለሁ። ጨዋታው ተለዋዋጭ ባህሪ ነበረው። እስከመጨረሻው አንድ ተጫዋች ወጥቶብን አቻ መውጣታችን ጥሩ ነው። ተጫዋቾቼን ለዚህ ጥረታቸው ላመሰግን እፈልጋለው ከምንም በላይ እስከመጨረሻው ከጎናችን ሳይለይ ለደገፈን ደጋፊያችንንም ላመሰግን እፈልጋለሁ።

በሁለተኛ አጋማሽ እየሰጡ ስላሉት ምላሽ

“የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊጉ ሁለተኛ ዙር ከፍተኛ ልምድ ይጠይቃል። ዛሬ እንኳን ልንማርባቸው የሚገቡ ብዙ ነገሮች አሉ። በሁለተኛው አጋማሽ ትጠናናለህ። ነቅለው የሚሄዱ ቡድኖች ይኖራሉ ፣ ሦስት ነጥብ የሚፈልጉ ፣ አቻ የሚፈልጉ ብዙ የምታነባቸው ነገሮች ይኖራሉ። ከገባብን በኋላ የያዝነውን ነገር አለቀቅንም። ስትመራ እና ጎዶሎ ስትሆን ብዙ የሚዝሩከረኩብህ ነገሮች ይኖራሉ። እኛ ግን የነበረንን ታክቲካል ዲስፕሊን ሳንለቅ ጨዋታውን እያነበብነው ለመጓዝ ሞክረናል።

ተጫዋች እና የቡድን መሪ በቀይ ስለማጣታቸው

“እኔ የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ ሄኜ ነው የተቀጠርኩት። በዕለቱ ደግሞ የጨዋታው ዋና ዳኛ አሉ። በዚህ ሰዓት ይሄን ይሄን ማለት ይከብደኛል። ሦስተኛ እንዳልሆን እፈራለሁ እና በዚሁ ላጠናቅ።

ከጊዮርጊስ ጋር ስላላቸው የነጥብ ልዩነት

” ሁሉም የራሱን ቡድን እያየ ነው ያለው። ከፊታችን ብዙ ጨዋታዎች ይቀራሉ እና ራሳችንን ብቻ እያየን ብንሄድ ይሻላል። የሚወርደውም ቻምፒዮን የሚሆነውም ስላልለየ ራሳችንን ሆነን መገኘት ነው። እንደቡድን ይዘን የምንቀርበው አጨዋወት ይወስነዋል ብዬ እገምታለሁ።