ቅድመ ዳሰሳ | የ22ኛ ሳምንት ሦስተኛ የጨዋታ ቀን

የጨዋታ ሳምንቱ መቋጫ የሆኑትን የነገ ሁለት ጨዋታዎች እንደሚከተለው ዳሰናቸዋል።

ሲዳማ ቡና ከ ፋሲል ከነማ

በሳምንት ከነበሩ ጨዋታዎች መካከል ይህ 2ኛ እና 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ ከፍ ያለ ፉክክር እንደሚያስመለክት ይገመታል። ከነገ ተጋጣሚው ጋር በነጥብ ተስተካክሎ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የመምጣት ዕድል ያለው ሲዳማ ቡና አንድ ነጥብ ብቻ ካሳካባቸው ካለፉት ሁለት ጨዋታዎች መልስ ወደ ድል መመለስን ያልማል። ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለውን ልዩነት ዳግም አስር ለማድረግ ወደ ሜዳ የሚገባው ፋሲል ከነማ በበኩሉ የተሻለ አቋም ላይ ሲገኝ ከመጨረሻ አራት ጨዋታዎቹ አስር ነጥቦችን በማሳካት ለነገ ይደርሳል።

ሲዳማ ቡና ወደ ላይኛው ፉክክር እየመጣ በነበረበት ሰዓት ብዙ ነገር ሊቀይር ይችል የነበረውን የጊዮርጊስን ጨዋታ አለማሸነፉ ያቀዘቅዘው ይመስላል። ነገም ለሁለተኛነት ደረጃም ቢሆን ተመሳሳይ ይዘት ያለው ጨዋታ የሚጠብቀው በመሆኑ በሙሉ የሥነ ልቦና ደረጃ ላይ መገኘት ይኖርበታል። በተለይም በመጀመሪያው ዙር በፋሲል የደረሰበትን የ4-0 ሽንፈት ትዝታ ረስቶ ወደ ሜዳ መግባት ያስፈልገዋል። ቡድኑ በመከላከሉ ረገድ አሁንም የጎላ ድክመት ባይስተዋልበትም ከፍሬው እና ዳዊት ጥምረት የሚያገኛቸውን ጥራት ያላቸው ኳሶች መልሶ ማግኘት እንዲሁም በሳላዲን ሰዒድ የተጠናከረውን እና ከመስመር በሚነሳው አዲሱ ሚናው ጥሩ እየተንቀሳቀስ ባለው ይገዙ ቦጋለ የሚደገፈውን የማጥቃት መስመሩ ነገ ጥሩ ንቃት ላይ እንዲገኝ ይጠብቃል።

የወላይታ ድቻው የፋሲል ከነማ ድል ከሦስት ነጥቦች ባለፈ ለቡድኑ አሰልጣኞች ትምህርት ሰጥቶ ያለፈ ነበር ማለት ይቻላል። እያንዳንዱ ጨዋታ ከፍ ባለ ፉክክር በሚደረግበት በአሁኑ ወቅት ቡድኑ ከዚህ ቀደመም እምብዛም ወዳልዘለቀበት በሦስት ተከላካዮች ወደሚጀምር አደራደር መመለሱ ብዙ ነገሮችን አዘባርቆበት ነበር። ሆኖም ወደለመደው ቅርፅ ከተመለሰ በኋላ ግን ጨዋታውን በሰፊ ግብ አሸንፏል። በመሆኑም ነገም ተጠባቂ ላለመሆን በሚደረጉ አዳዲስ ለውጦች ይልቅ የእስካሁኑ የቡድን የአሰላለፍ እና የማጥቃት መንገድ ምርጫ ሳያዋጣው አይቀርም። ከኳስ ቁጥጥር ባለፈ በፈጣን ሽግግር በመጨረሻው ጨዋታ የታየበት ብቃትም ለነገው ጨዋታ ግብዓት መሆን የሚችል ነበር።

ሲዳማ ቡና በመጨረሻው ጨዋታ ጉዳት አስተናግደው የነበሩት ጊት ጋትኩት እና ሳላዲን ሰዒድ ተመልሰውለታል። አሁንም ጉዳት ላይ የሚገኘው ሙጂብ ቃሲምን የማያገኘው ፋሲል ከነማ ደግሞ አምሳሉ ጥላሁንን እና ሽመክት ጉግሳ ከቅጣት መልስ መጠቀም የሚችል ሲሆን በአንፃሩ ከድር ኩሊባሊን በአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ያጣል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ ዘጠኝ ጊዜ የመገናኘት ታሪክ ያላቸው ሲሆን ሁሉም ጨዋታዎች በመሸናነፍ ተጠናቀዋል። ፋሲል ከነማ 5-4 በሆነ ቁጥር የማሸነፍ የበላይነት ሲኖረው እስካሁን ሲዳማ ቡና 11 ፋሲል ከነማ ደግሞ 14 ግቦችን አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሲዳማ ቡና (4-2-3-1)

ተክለማርያም ሻንቆ

አማኑኤል እንዳለ – ጊት ጋትኩት – ያኩቡ መሐመድ – መሐሪ መና

ዳዊት ተፈራ – ሙሉዓለም መስፍን

ይገዙ ቦጋለ – ፍሬው ሰለሞን – ሀብታሙ ገዛኸኝ

ሳላዲን ሰዒድ

ፋሲል ከነማ (4-1-4-1)

ሚኬል ሳማኪ

ዓለምብርሃን ይግዛው – አስቻለው ታመነ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን

ይሁን እንዳሻው

ሽመክት ጉጋሳ – በዛብህ መለዮ – ሱራፌል ዳኛቸው – በረከት ደስታ

ኦኪኪ አፎላቢ

ወልቂጤ ከተማ ከ አዲስ አበባ ከተማ

የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ በሰንጠረዡ አጋማሽ እና ታች የሚገኙ ቡድኖችን ያገናኛል። አርባምንጭን በመርታት ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል የተመለሱት ወልቂጤ ከተማዎች የነጥብ ስብስባቸውን ከሰላሳ ለማሳለፍ እና ወደ ላይኛው ፉክክር ለመጠጋት የነገው ውጤት ያስፈልጋቸዋል። የወራጅ ቀጠና ፍልሚያ ውስጥ ለሚገኘው አዲስ አበባ ከተማ ግን ቦታውን ለድሬዳዋ አስረክቦ ቀና ለማለት የነገው ጨዋታ ከወልቂጤም በላይ በእጅጉ ያስፈልገዋል።

ወልቂጤ ከተማ ሊያስቸግረው ይችላል ተብሎ የተገመተው የአርባምንጭ ከተማን የመከላከል ብርታት መቋቋም ያስቻለውን የማጥቃት ሂደት ማስቀጠል የነገ ዋነኛው ጉዳዩ ይመስላል። ከተጋጣሚውም ባህሪ አንፃር ክፍት እንደሚሆን በሚጠበቀው ጨዋታ በኳስ ቁጥጥር ላይ መመስረትን የሚያዘወትሩት ሰራተኞቹ የቅብብሎቻቸውን ፍጥነት መጨመር እና የሜዳውን ስፋት መጠቀም ሊያግዛቸው ይችላል። እዚህ ላይ ከፍ ዝቅ የሚለው የተጫዋቾች አቋም ልዩነት መፍጠሩ የሚቀር አይመስልም። የቡድኑ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ጌታነህ ከበደ መልካም አቋም ላይ መገኘት በዚህ ረገድ ለወልቂጤ መልካም አጋጣሚ ነው። ቡድኑ ከቀድሞው አሰልጣኙ ጋር በሚገናኝበት ጨዋታ የተጫዋቾችን ጠንካራ እና ደካማ ጎን አንፃር ከማወቅ አኳያ የሚመጣ የተገማችነት ፈተና እንደሚጠብቀው ግን ይታመናል።

አዲስ አበባ ከተማ በሜዳ ላይ ያለው እንቅስቃሴ እና ያለበት ደረጃ የተገላቢጦሽ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸውን ወደ ኃላፉነት ያመጣው አዲስ አበባ በአዲስ አሰልጣኝ ስር ቡድኖች የሚያሳዩት መነቃቃት ተጠቃሚ መሆን ከቻለ ነገ የአጨዋወት ባህሪው የሚጎለውን አንድ ድክመት ሊያሻሽል ይችላል። ይህም ከኋላ መስመሩ ላይ የሚታይበት የትኩረት ችግር ነው። በሆሳዕናው ጨዋታ ያስተናገዳቸው ግቦች ከዚህ ችግሩ የመነጩ እንደነበሩም አይዘነጋም። በመሆኑም ቡድኑ ግብ አስቆጥሮ ሲመራ በጥሩ መዋቅር ለተከላካይ ክፍሉ ሽፋን በመስጠት የማጥቂያ መንገዶች ሲገኙ ደግሞ በተጠናና እስካሁን በሚታይበት የቸልተኝነት ደረጃ ሳይሆን በተሻለ አፈፃፀም ግቦች ጨምሮ ጨዋታን ተቆጣጥሮ መውጣትን መላመድ የግድ ይለዋል።

ወልቂጤ ከተማ ጉዳት ላይ የነበሩት ሀብታሙ ሸዋለም እና ጫላ ተሺታን በነገው ጨዋታ ያገኛል። በአዲሱ የአሰልጣኞች ቡድን ስር ሁለት ልምምዶችን የሰራው አዲስ አበባ ከተማ ስብስብም በሙሉ ስብስቡ ለነገው ጨዋታ ይደርሳል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ዘንድሮ በመጀመሪያው ዙር የተገናኙበት እና ወልቂጤ ከተማ 1-0 ያሸነፈበት ጨዋታ ብቸኛው የሊግ ግንኙነታቸው ነበር።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ሮበርት ኦዶንካራ

ተስፋዬ ነጋሽ – ዳግም ንጉሴ – ዋሀብ አዳምስ – ረመዳን የሱፍ

በኃይሉ ተሻገር – ሀብታሙ ሸዋለም – አብዱልከሪም ወርቁ

ያሬድ ታደሠ – ጌታነህ ከበደ – ጫላ ተሺታ

አዲስ አበባ ከተማ (4-3-3)

ዳንኤል ተሾመ

አሰጋኸኝ ጴጥሮስ – ቴዎድሮስ ሀሙ – አዩብ በቀታ – ሮቤል ግርማ

ሙሉቀን አዲሱ – ቻርለስ ሩባኑ – ኤሊያስ አህመድ

እንዳለ ከበደ – ሪችሞንድ ኦዶንጎ – አቤል ነጋሽ