ሪፖርት | ባህር ዳር ከተማ ከድል ጋር ታርቋል

የወልቂጤውን ፎርፌ ሳይጨምር ለ11 ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻሉት የጣና ሞገዶቹ ዛሬ በተመስገን ደረሰ ጎል አዳማ ከተማን 1-0 ረተዋል።

ባህር ዳር ከተማዎች በፋሲል ከነማ ከተሸነፈው ቡድን ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ቀይ ካርድ በተመለከተው ፍፁም ዓለሙ ምትክ አለልኝ አዘነን ብቻ ተክተው ቀርበዋል።

አዳማ ከተማዎች ደግሞ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስብ ባደረጓቸው ለውጦች ዮናስ ገረመው እና አቡበከር ወንድሙን አስወጥተው በምትካቸው ታደለ መንገሻ እና አብዲሳ ጀማልን አስገብተዋል።

ፈጣን አጀማመርን ያስመለከተን ጨዋታው ገና በ2ኛው ደቂቃ ነበር አደገኛ ሙከራን የተደረገበት። በአዳማ በኩል ከራሳቸው አጋማሽ በረጅሙ የተጣለለትን ኳስ አሜ መሀመድ ከመናፍ ጋር ታግሎ በማግኘት በነፃነት ይገኝ ለነበረው ዳዋ ሆቴሳ አቀብሎት ባመከናት እጅግ አስቆጪ አጋጣሚ በኋላ ባህር ዳር ከተማዎች በ5ኛው ደቂቃ መሪ ሆነዋል። መናፍ ዐወል በረጅሙ ከራሱ አጋማሽ የላከውን ኳስ ለመከላከል ሳጥኑን ለቆ የወጣው የአዳማው የግብ ዘብ ኳሱን ማግኘት አለመቻሉን ተከትሎ ፉአድ ፈረጃ ያቀበለውን ኳስ ተመስገን ደረሰ ከሳጥን ውጪ ሲመታ በሚሊዮን ሰለሞን ተጨረፎ የአዳማ መረብ ላይ አርፏል።

አዳማዎች ከአንድ ደቂቃ በኋላ አቻ ለመሆን ቀርበው ነበር። በረጅሙ ከጀሚል ያዕቆብ የደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ ዳዋ ሆቴሳ ወደ ግብ የላከው ኳስ ግብ ጠባቂው አቡበከርን ብታልፍም ፈቱዲን ጀማል ደርሶ አድኗታል። በደጋፊያቸው ታግዘው የተሻለ የመጀመሪያ አጋማሽን ያሳለፉት ባህር ዳር ከተማዎች በአጋማሹ ጥሩ የጨዋታ ቁጥጥር የነበራቸው ሲሆን በፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች በተሻሉ የማጥቃት አጋጣሚዎችን መፍጠር ቢችሉም በደካማ ውሳኔ አሰጣጥ ውጤታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል።

በ43ኛው ደቂቃ አህመድ ረሺድ በግሩም ሁኔታ ከተከላካይ ጀርባ ያደረሰውን ኳስ ዓሊ ሱሌይማን ወደ ግብ የላካት እና ሳኩባ ካማራ ያወጣበት እንዲሁም ይህን ተከትሎ ያገኙትን የማዕዘን ምት አጋጣሚ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣበት አጋጣሚዎች የተሻሉ የቡድኑ ዕድሎች ነበሩ። በአንፃሩ አዳማ ከተማዎች ግብ ካስተናገዱ ወዲህ በፍጥነት ወደ ጨዋታው ለመመለስ በመጠኑም ቢሆን በማጥቃት ረገድ በተከላካይ ጀርባ ከሚጣሉ ኳሶች ባለፈ በቁጥር በርክተው ወደ ፊት በመጠጋት በቅብብሎች ዕድል ለመፍጠር ቢሞክሩም ብዙም ያልዘለቀው ይህ ሂደት ውጤት አላስገኘላቸውም።

ሁለተኛው አጋማሽ በእንቅስቃሴ ደረጃ ለክፉ የማይሰጥ ሆኖ ጀምሯል። አዳማ ከተማ ፈጠን ባሉ ቅብብሎች ባህር ዳር ከተማ ደግሞ በንፅፅር ኳስ መስርቶ በመውጣት ሁለቱም የማጥቃት ፍላጎታቸውን የሚገልፅ ፉክክር አድርገዋል። ሆኖም አንዳቸው የሌላኛቸውን እንቅስቃሴ ከማቋረጣቸው ባለፈ የመጨረሻ ውሳኔዎቻቸው በሚፈለገው ደረጃ ጥራታቸውን ሳይጠብቁ እየቀሩ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሊታይ አልቻለም።

ጨዋታው 65ኛው ደቂቃን ከተሻገረ በኋላ ደግሞ ባህር ዳሮች ቀስ በቀስ ከኳስ ጀርባ ወደመሆኑ አመዝነዋል። ከዚህ በኋላ አዳማዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ለመውሰድ ባይቸገሩም የባህር ዳርን የመከላከል አደረጃጀት የሚያልፉ ቅብብሎችን መከወን አልቻሉም። የጣና ሞገዶቹ በመልሶ ማጥቃት ለመውጣት የሚያደርጉት ጥረት ባይሰምርም የተጋጣሚያቸውን የኳስ ፍሰት ከግብ ክልላቸው እንዲርቅ ማድረግ ችለዋል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሰከንዶች ሲቀሩት ብቻ አዳማ ከተማዎች ከቅጣት ምት ያገኙት ዕድል በአቡበከር ኑሪ ሲመለስ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው የነበረ ቢሆንም ሳይሳካላቸው ጨዋታው በባህር ዳር ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በውጤቱ ባህር ዳር ከተማ ነጥቡ 29 በማድረስ 9ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ አዳማ ከተማ 27 ነጥብ ላይ ቀርቷል።