ቅድመ ዳሰሳ | የ24ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች

ነገ የሚቋጨው የሊጉ 24ኛ ሳምንት ቀሪ ሦስት ጨዋታዎችን እንደሚከተለው ዳሰናቸዋል።

ወልቂጤ ከተማ ከ ሰበታ ከተማ

ረፋድ ላይ በሚደረገው ቀዳሚ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ የሚገፋውን ውጤት ሰበታ ከተማ ደግሞ ራሱን ለማትረፍ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ተስፋ የሚሆኑ ነጥቦችን ፍለጋ የሚገናኙበት ነው። በኢትዮጵያ ቡና ድራማዊ ሽንፈት ያስተናገደው ወልቂጤ ከተማ ከመጨረሻ አምስት ጨዋታዎቹ አንድ ድል ብቻ በማስመዝገቡ በሜዳ ላይ የሚያሳየውን መልካም እንቅስቃሴ ወደ ውጤት መቀየር ተስኖት ቢገኝም እስካሁን የከፋ የመውረድ ስጋት ውስጥ አልገባም። ሆኖም ነገ አሸንፎ ከቀጠናው ያለውን ርቀት ወደ ስምንት ማስፋት ይበልጥ ያረጋጋዋል። ሰበታ ከተማ በበኩሉ እንዳለፈው ሳምንት ነገም ድል ከቀናው የሊጉን ግርጌ ለጅማ አስረክቦ አንድ ደረጃ የማሻሻል ዕድል ሊኖረው ይችላል። ይህን ማድረግ ከቻለ ቡድኑ በቀጣይ ጨዋታዎች ይበልጥ ከፍ የማለት ተስፋውን ሊያለመልም ይችላል።

ክፍት እንቅስቃሴ እንደሚደረግበት በሚጠበቀው ጨዋታ ሁለቱም አጥቅተው በመጫወት ግቦችን የሚያስገኙላቸውን ዕቅዶች ለመተግበር እንደሚገቡ ይጠበቃል። ሰራተኞቹ በኳስ ቁጥጥር ላይ ተመስርተው በቀኝ ባደላ ጥቃት ጌታነህ ለበደ እና ጫላ ተሺታን መሰረት ያደረጉ ቅብብሎች ላይ እንደሚያተኩሩ ሲጠበቅ ነገም እንደቡና ሁሉ ኳስ መስርቶ የሚወጣ ቡድንን እንደመግጠማቸው ፊት ላይ በተናጠል ጫናዎችን ማሳደራቸው የሚቀር አይመስልም። ቡድኑ የሜዳውን ስፋት ባማከለ የመከላከል ቅርፅ ውስጥ የግብ ክልሉን የማስጠበቅ እና ለቅብብሎች ክፍተት የመስጠት በቡናው ጨዋታ የታየበት ክፍተቱ ለነገም ፈተና ሊሆንበት ይችላል። ከዚህ ባለፈ ራሱን የመከላከል ጫና ውስጥ ሳይከት የሚያገኛቸውን ዕድሎች ወደ ግብነት እየቀየረ መዝለቅ እንደሚገባው የመጨረሻው ጨዋታ ትምህርት እንደሚሆነው አያጠያይቅም።

ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ከበላያቸው ያለው ጅማ አባ ጅፋርን መርታት የቻሉት ሰበታ ከተማዎች በአዕምሮ ደረጃ ይህ ጨዋታ የሰጣቸውን የማሸነፍ ሥነ ልቦና ማስቀጠል መቻል ዋነኛ የነገ ጨዋታቸው መሰረት ነው። ድሉ ከሦስት ነጥብ ባለፈ ቡድኑ በተከታታይ ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ቆይቶ ያለውጤት የሚወጣበትን መንገድ የቀየረ መሆኑ ሲታሰብ የሚሰጠው ዋጋ ትልቅ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ከጅማ የተሻለ ተጋጣሚ በሆነው ወልቂጤ ላይ መድገም መቻል ደግሞ የሰበታ የነገው ጥያቄ ነው። ከራሱ የግብ ክልል በቅብብሎች የሚወጣው ሰበታ ከመሀል ወደ ፊት የሚጣሉ መካከለኛ ኳሶች እንዲሁም ጥሩ መነቃቃት ላይ ባሉት ሁለቱ የመስመር ተከላካዮቹ ወደ ሳጥን የሚጣሉ ኳሶች ነገም ዋነኛ የማጥቂያ መሳሪያዎቹ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። መሰል ኳሶችን ወደ አደጋ በመቀየር የዴሪክ ንሲባምቢ እና አብዱልሀፊስ ቶፊቅ ጥሩ አቋም ላይ መገኘት ለአሰልጣኝ ብርሀን ደበሌ ጥሩ ግብዓት እንደሆነ ይታመናል።

ወልቂጤ ከተማ አበባው ቡታቆን በጉዳት ሲያጣ ቀሪ የቡድኑ ስብስብ ለጨዋታው ዝግጁ ነው። ሰበታ ከተማ ደግሞ ከምንተስኖት ዓሎ በተጨማሪ ዘላለም ኢሳይያስንም በጉዳት የማያገኝ ሲሆን የቢያድግልኝ ኤልያስ መሰለፍም አጠራጣሪ ሆኗል። ከዚህ ውጪ በግል ጉዳይ ከቡድኑ ጋር ያልነበረው ፍፁም ገብረማርያምም ተመልሷል።

የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ ተስፋዬ ጉሩሙ ፣ ረዳቶች ሰለሞን ተስፋዬ እና ተከተል በቀለ ፣ አራተኛ ዳኛ ምስጋው መላኩ ፣ ተጨማሪ ዳኞች ካሳሁን ፍፁም እና ድሪባ ቀነኒሳ

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን ከተገናኙባቸው ሦስት ጨዋታዎች ሰበታ ከተማ ሁለቱን ወልቂጤ ከተማ ደግሞ አንዱን አሸንፈዋል። በጨዋታዎቹ ሰበታ ከተማ አራት ወልቂጤ ከተማ ሦስት ግቦች አሏቸው።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ሰዒድ ሀብታሙ

ተስፋዬ ነጋሽ – ዳግም ንጉሴ – ዋሀብ አዳምስ – ረመዳን የሱፍ

በኃይሉ ተሻገር – ሀብታሙ ሸዋለም – አብዱልከሪም ወርቁ

ጫላ ተሺታ- ጌታነህ ከበደ – ያሬድ ታደሰ

ሰበታ ከተማ (4-2-3-1)

ለዓለም ብርሀኑ

ጌቱ ኃይለማሪያም – በረከት ሳሙኤል – አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ

በኃይሉ ግርማ – ጋብርኤል አህመድ

ሳሙኤል ሳሊሶ – አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ – ዱሬሳ ሹቢሳ

ዴሪክ ኒስባምቢ

መከላከያ ከ ፋሲል ከነማ

አሁን ላይ ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሌላ ወጥ አቋም በማሳየት ላይ ያሉ ክለቦችን ብንፈልግ ከመከላከያ እና ፋሲል ውጪ ሌላ አናገኝም። ከሁለቱ ማን ተከታታይ የአሸናፊነት መንገዱን ያስቀጥል እንደሆን የሚነግረን ጨዋታ ደግሞ ነገ ቀጥር ላይ ይከናወናል። ከሽንፈት ከተፋታ አምስት ጨዋታዎች ያለፉት መከላከያ ሦስት ጨዋታዎችን በመደዳ አሸንፎ ለነገ ይደርሳል። ከሰንጠረዡ አጋማሽ ቢያንስ አንድ ደረጃ ወደ ላይ ከፍ የማለት ዕድልን ይዞለት የሚመጣውን የነገውን ጨዋታ የሚወጣበት መንገድ ደግሞ ተጠባቂ ሆኗል። ከመጨረሻ ስድስት ጨዋታዎቹ ሁለት ነጥቦችን ብቻ ለጣለው ፋሲል ከነማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀድሞ ጨዋታውን ማሸነፉ እርስ በእርስ ከሚያደርጉት ቀጣይ ጨዋታ በፊት የነጥብ ልዩነቱ ከስምንት እንዳይበልጥ ለማድረግ የነገዎቹን ሦስት ነጥቦች ማሳካት ለድርድር የማይቀርብ ነው።

ባለፉት አራት ጨዋታዎች 12 ግቦችን ያስቆጠረው መከላከያ ከዚያ ቀደም ለአምስት 90 ደቂቃዎች ኳስ እና መረብን ማገናኘት ተስንኖት እንደነበር ማመን ይከብዳል። አሁን ላይ የተጋጣሚው አቀራረብ ምንም ይሁን ምን በልበ ሙሉነት የሚያጠቃ አስፈላጊ ሲሆን ብቻ ወደ መከላከሉ የሚያመዝን መከላከያን እያየን እንገኛለን። በመሆኑም ለነገ ተጋጣሚው ከፍ ያለ ግምት ከመስጠት ይልቅ ከኳስ ውጪ ከፊት ጀምሮ ጫና የሚያሳድር ከተከላካዮች ጀርባ ያለውን ክፍተት በፈጣን ሽግግር ለመጠቀም አቅሙ ያለው መከላከያ በነገው ጨዋታ ይጠበቃል። በቢኒያም በላይ በሚመራው በቡድኑ ጥቃት ውስጥ ቁልፍ ሚና እየተወጡ ካሉት ተሾመ በላቸው እና አዲሱ አቱላ በተጨማሪ ከኋላ የምንተስኔት አዳነ ከፊት የእስራኤል እሸቱ ሚና ምን ያህል ወሳኝ መሆኑን የመጨረሻው ጨዋታ አሳይቶናል።

ፋሲል ከነማ ተከታታይ ጨዋታዎቹ ቀላል አልነበሩም። ሆኖም በከባድ ፍልሚያዎች ውስጥ ሦስት ነጥብ አሳክቶ የሚወጣበትን መላ ሳያጣ እዚህ ደርሷል። ዐፄዎቹ በመጀመሪያ ዙር ድክመታቸው እንዲቆጩ በሚያደርግ መልኩ ትክክለኛ የዋንጫ ተፎካካሪ ቡድን ባህሪ የሆነው በተጋጣሚ ተፈትኖ የማለፍ ገፅታቸው ለነገው ጨዋታም የሚተርፍ ነው። በአራት ተከታታይ ድሎቹ ውስጥ አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደው ፋሲል ይህንን ያሳካለትን የመከላከል መዋቅሩን እጅግ አደገኛ ፈጣን ጥቃቶችን ከሚሰነዝረው ከነገ ተጋጣሚው መጠበቅ አስፈላጊው ይሆናል። በማጥቃቱ ረገድ ግን ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ የመጨረሻ ዕድሎችን የመፍጠር አቅሙ ይበልጥ ሊፈተን ይችላል። በእርግጥ ጦሩ በመጨረሻ ጨዋታው በመስመሮች መካከል ክፍተቶችን ፈጥሮ የታየበት አጋጣሚዎች ቢታዩም የፋሲል ከነማ የማጥቃት አማካዮች መሰል ክፍተትን በቅብብሎች የመጠቀም የስኬት ደረጃ ከፍ ብሎ መገኘት ይኖርበታል። ይህንን ማድረግ ቡድኑ ተቀይሮ ገብቶ በጎ አስተዋፅዖ እያደረገ ያለው የፍቃዱ ዓለሙን የመጨረሻ ጥረት ከመሻቱ በፊት ጨዋታውን በእጁ ለማስገባት እጅግ አስፈላጊው ይሆናል።

መከላከያ ጉዳት ገጥሞት ወደ አዲስ አበባ ካመራው ኢብራሂም ሁሴን ውጪ የሚያጣው ተጫዋች አይኖርም። በፋሲል ከነማ በኩል ይሁን እንዳሻው በአምስት ቢጫ ያሬድ ባየህ ደግሞ በቀይ ካርድ ከነገው ጨዋታ ውጪ ሲሆኑ አስቻለው ታመነ እና ሙጂብ ቃሲም መመለሳቸው ተሰምቷል።

የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ ፣ ረዳቶች አሸብር ታፈሰ እና ሸዋንግዛው ይልማ ፣ አራተኛ ዳኛ ተከተል ተሾመ ፣ ተጨማሪ ዳኞች ኤፍሬም ኃይለማርያም እና ፍሬዝጊ ተስፋዬ

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ፋሲል ከነማ እና መከላካያ በአጠቃላይ 8 ጊዜ ተገናኝተዋል። ፋሲል አራት በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መከላከያ ሁለቱን አሸንፎ በቀሪዎቹ ሁለቱ አቻ ተለያይተዋል። ዐፄዎቹ 13 ፣ ጦሩ ደግሞ 6 ጎሎች አስቆጥረዋል።

መከላከያ (4-2-3-1)

ክሌመንት ቦዬ

ገናናው ረጋሳ – አሌክስ ተሰማ – ልደቱ ጌታቸው – ዳዊት ማሞ

ኢማኑኤል ላርዬ – ምንተስኖት አዳነ

ተሾመ በላቸው – አዲሱ አቱላ – ቢኒያም በላይ

እስራኤል እሸቱ

ፋሲል ከነማ (4-1-4-1)

ሚኬል ሳማኪ

ዓለምብርሃን ይግዛው – ከድር ኩሊባሊ – አስቻለው ታመነ – አምሳሉ ጥላሁን

ሀብታሙ ተከስተ

ሽመክት ጉግሳ – በዛብህ መለዮ – ሱራፌል ዳኛቸው – በረከት ደስታ

ኦኪኪ አፎላቢ

ወላይታ ድቻ ከ ሲዳማ ቡና

ከዋንጫ ፉክክሩ ብቻ ሳይሆን ከሁለተኛ ደረጃም ጭምር ፈቀቅ ብለው የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች በሳምንቱ መጨረሻ ጨዋታ ሲገናኙ በፋሲል ከነማ ውጤት ላይ ተመስርተው ለኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቦታው ያላቸውን ተስፋ የሚያሳይ ጨዋታ ያደርጋሉ። ከመጨረሻ ድሉ በኋላ ሰባት ጨዋታዎች ያለፉት ወላይታ ድቻ በተሻለ ቅርበት ላይ የሚገኝ ሲሆን ከሁለተኝነት ያለውን የሰባት ነጥብ ርቀት ማጥበብን ያልማል። ሲዳማ በበኩሉ ዛሬ ሽንፈት የገጠመው ሀዋሳ ከተማን የአራተኝነት ደረጃ ለማግኘት የሚረዳውን ጨዋታ ያከናውናል።

ከቡድናቸው ስብስብ አንፃር ያሉበት ደረጃ በአቻ ውጤቶች መታጀቡ ያላስከፋቸው አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም በተከታታይ ከተጠቀሙበት የተረጋጋ አሰላለፋቸው ውስጥ የሚያጧቸው ተጫዋቾች መኖራቸው የነገ አንዱ ፈተናቸው ነው። ያም ቢሆን መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስን ጨምሮ በሁለት ጨዋታዎች ግብ ያላስተናገዱት የጦና ንቦቹ ቅያሪዎችን ቢያደርጉም የሚፈልጉት የኋላ መስመር ጥንካሬ ላይ መገኘት እንደሚችሉ ይታሰባል። የቡድኑ ድክመት ሆኖ የቀጠለው ግን ፈጣን ሽግግሮችን በማድረግ ውስጥ በቁጥር በርካታ ዕድሎችን መፍጠር እና ወደ ግብ የመቀየር ንፃሬውን መጨመሩ ላይ ነው። ምናልባትም ነገ ከፊት አዲስ ጥምረትን ለመተግበር መገደዱ ከጨዋታው ለዚህ ችግሩ አዲስ መላ ሊያገኝ አልያም ከበፊቱም በላይ ሊቸገር የሚችልበት ዕድል አለ።

ሲዳማ ቡና ከአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ስንብት በኋላ የመጀመሪያ ጨዋታን ያደርጋል። ከጥሩ መነቃቃት በኋላ በአራት ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻለው ሲዳማ የአሰልጣኝ ለውጡ ወደ ቀደመ የማሸነፍ መንፈሱ የሚመልሰውን መነሳሳት ይፈጥርለት እንደሆን የነገው ጨዋታ ምላሽ ይሰጣል። በጨዋታው እጅግ ተበታትኖ የታየው የኋላ መስመሩ በዋነኝነት ተስተካክሎ መመለስ እንደሚገባው ይታመናል። የጊት ወደ ሜዳ መመለስ ይህንን ሊያሳካለት የሚችል ሲሆን ከአጥቂ አማካዮቹ የቀደመ ጥራት ያላቸው ቅብብሎችን ማግኘት የወላይታ ድቻን ጠንካራ መከላከል ለመጋፈጥ አስፈላጊው ይሆናል። ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት ኃላፊነት ለተረከበው ወንድምአገኝ ተሾመ የይገዙ ቦጋለ ወደ ግብ አስቆጣሪነት መመለስ ብቸኛው ከመከላከያው ሽንፈት የሚወስደው በጎ ነገር ይመስላል።

ወላይታ ድቻ ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኋላ ልምምድ ቢጀምርም ሙሉ ለሙሉ የጨዋታ ዝግጅት ላይ ያልደረሰው ስንታየሁ መንግሥቱ ሌላ ደጉ ደበበ እና ያሬድ ዳዊትን በአምስት ቢጫ ካርድ ምክንያት የማይጠቀም ሲሆን ምንይሉ ወንድሙ ደግሞ በጉዳት የመግባቱ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል። ሲዳማ ቡና ባሳለፍነው ሳምንት በጉዳት ያጣው ጊት ጋትኩት የተመለሰለት ሲሆን ቀሪው የቡድኑ ስብስብ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ነው።

የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ ለሚ ንጉሴ ፣ ረዳቶች ካሳሁን ፍፁም እና አብዱ ይጥና ፣ አራተኛ ዳኛ ዮናስ ማርቆስ ፣ ተጨማሪ ዳኞች ማንደፍሮ አበበ እና አያሌው አሰፋ

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን 15 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ ሁለት ጨዋታ ሲያሸንፍ በአምስት ጨዋታ አቻ ተለያይተው ሲዳማ ቡና ስምንት ጊዜ አሸንፏል። በሁለቱ ግንኙነት እስካሁን 24 ጎሎች ሲቆጠሩ ወላይታ ድቻ 8 ፣ ሲዳማ ቡና 16 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።

ወላይታ ድቻ (4-3-3)

ቢኒያም ገነቱ

በረከት ወልደዮሐንስ – መልካሙ ቦጋለ – አንተነህ ጉግሳ – አናጋው ባደግ

– ሀብታሙ ንጉሴ – ንጋቱ ገብረስላሴ – እንድሪስ ሰዒድ

ቢኒያም ፍቅሬ – ምንይሉ ወንድሙ – ቃልኪዳን ዘላለም

ሲዳማ ቡና (4-2-3-1)

ተክለማርያም ሻንቆ

አማኑኤል እንዳለ – ጊት ጋትኩት – ያኩቡ መሐመድ – መሐሪ መና

ዳዊት ተፈራ – ሙሉዓለም መስፍን

ይገዙ ቦጋለ – ፍሬው ሰለሞን – ሀብታሙ ገዛኸኝ

ሳላዲን ሰዒድ