ኢትዮጵያ ከታንዛኒያ ጋር ነጥብ ተጋርታለች

በሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ሁለተኛ የምድብ ጨዋታቸውን ያደረጉት ኢትዮጵያ እና ታንዛኒያ 2-2 በሆነ ውጤት ተለያይተዋል፡፡

ሉሲዎቹ ዛንዚባርን በጎል ተንበሽብሸው ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ቤተልሔም በቀለን በሀሳቤ ሙሶ ፣ አረጋሽ ካልሳን በአሪያት ኦዶንግ በመቀየር በ4-3-3 የጨዋታ አደራደር ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ የሚመስል የኳስ ንክኪ በርከት ብሎ ነገር ግን አልፎ አልፎ የታንዛኒያ አስፈሪ ረጃጅም ኳሶች የተንፀባረቁበት ነበር፡፡

ሉሲዎቹ ኳስን በቅብብል መስርተው ለመውጣት አልመው መንቀሳቀስ ቢችሉም ካለፈው ጨዋታ አንፃር ፍፁም መረጋጋት አይታይባቸውም ነበር፡፡ በተለይ ሁለቱ የመሀል ተከላካዮች ሀሳቤ ሙሶ እና ቅድስት ዘለቀ የታንዛኒያን ረጃጅም ኳሶች የመጀመሪያዎቹን አምስት ያህል ደቂቃዎች ላይ መቆጣጠር ተስኗቸው ታይቷል፡፡ ለዚህም ማሳያ አራተኛው ደቂቃ ላይ የታንዛኒያ ተከላካይ በረጅሙ ስታሻማ አምበሏ አሚና ቢላሊ አግኝታው ግብ ጠባቂዋ ታሪኳ በርገና ያዳነችባት በተለየ የሚጠቀሰው አጋጣሚ ነበር፡፡ የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሲመጣ አመዛኙን እንቅስቃሴ መሀል ሜዳ ላይ ያደረጉት ሉሲዎቹ በመጀመሪያ ሙከራቸው ጎል አግኝተዋል፡፡ 9ኛው ደቂቃ ላይ ከቆመ ኳስ ተሻጋሪ ኳስን ለቡድን ጓደኞቿ ለማድረስ ትጋት የሚነበብባት ኝቦኝ የኝ በረጅሙ ወደ ግብ ክልል ስታሻማ ሎዛ አበራ የታንዛኒያን ተከላካይ እና ግብ ጠባቂ ያለመናበብ ተመልክታ ጎል አስቆጥራለች።

የኢትዮጵያን የኳስ ፍሰት በማቋረጥ ቀዳዳ እየፈለጉ ወደ አቻነት ለመምጣት ተሻጋሪ ኳስ ላይ ዘንበል ያሉት ታንዛኒያዎች በአጥቂዎቹ አሚና ዓሊ እና ፈጣኗ ኦፓ ክሌመንት አማካኝነት ኳስ እና መረብን ለማገናኘት በእጅጉ ታትተረዋል፡፡ 24ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስም ተሳክቶላቸው ግብ ሊያስቆጥሩ ችለዋል፡፡ ከተከላካዮች በረጅሙ ወደ ኢትዮጵያ የግብ ክልል የተላከን ኳስ ናርዶስ ጌትነት በአግባቡ በግንባሯ መግጨት ባለመቻሏ ወደ ጎል የላከችውን ኳስ ታሪኳ በርገና እንደምንም ለማውጣት ስትሞክር አጠገቧ የነበረችው አጥቂዋ ኦፓ ክሌመንት በቀላሉ ከመረብ አገናኝታለች፡፡ በቀሩት ደቂቃዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወጥ ባይሆንም በተወሰነ መልኩ ወደ መሪነት ለመሸጋገር ሞክሯል፡፡ ረድኤት አስረሳኸኝ የተከላካይ ስህተት ተጠቅማ ያገኘችውን እና ከማዕድን ሳዕሉ በአግባቡ የተቀበለችውን ኳስ አክርራ መትታ በግቡ የላይኛው ብረት የወጣበት ለግብ የቀረበው የቡድኑ ሙከራ ነበር፡፡ ታንዛኒያዎች በአንፃሩ የሚያገኙት ዕድል ለመጠቀም ከርቀት በሚደረጉ ሙከራዎች ጎል ለማግኘት ቢታትሩም አጋማሹ 1-1 ተገባዷል፡፡

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ብርቱ ፉክክርን አስመልክቶናል፡፡ 64ኛው ደቂቃ ላይ ልክ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ መሪ መሆን የቻሉት ሉሲዎቹ ነበሩ፡፡ የመስመር አጥቂዋ መሳይ ተመስገን በግራ በኩል የደረሳትን ኳስ አክርራ በመምታት አስቆጥራው ውጤቱን ወደ 2-1 አምጥተዋለች፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጎል ካስቆጠረ በኋላ በአመዛኙ ለመከላከል በማለም አማካዩዋ ማዕድን ሳህሉን የመከላከል ባህሪ ባላት ብርቄ አማረ መለወጥ ከቻለ ሦስት ያህል ደቂቃዎች ብቻ እንደተቆጠሩ በ77ኛው ደቂቃ ብርቄ አማካዩዋ ማዋናሀሚስ ኦማሪ ላይ ከሳጥን ውጪ የሰራችባትን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የቅጣት ምት ተከላካዩዋ ኢኒኪያ ካሶንጋ ወደ ጎል አክርራ ስትመታው የግብ ጠባቂዋ ታሪኳ በርገና የቦታ አጠባበቅ ድክመት ታክሎበት ወደ ጎልነት ተለውጧል፡፡

2-2 ለመሆን መገደዳቸውንን የተመለከቱት አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የማጥቃት ኃይልን በመጨመር ጎል ለማስቆጠር ያለመ ቅያሪን አድርገዋል፡፡ አረጋሽ ካልሳን በመሳይ ተመስገን ፣ ብርቱካን ገብረክርስቶስን በአሪያት ኦዶንግ እና ቱሪስት ለማን በረድኤት አስረሳኸኝ በመለወጥ ወደ አሸናፊነት ለመምጣት ሉሲዎቹ በአንፃሩ ታንዛኒያም በመልሶ ማጥቃት የጨዋታ መንገድ ብርቱ ትግልን ማድረግ ቢችሉም ጨዋታው 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡