ሉሲዎቹ በሴካፋ ውድድር ወደ ፍፃሜ ሳያልፉ ቀርተዋል

መቶ ሀያ ደቂቃዎችን የፈጀው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ዩጋንዳን አሸናፊ በማድረግ ተጠናቋል።

ለፍፃሜ የሚያልፈውን ቡድን ለመለየት ስድስት ሰዓት ሲል የዩጋንዳ እና ኢትዮጵያ ጨዋታ ጅምሩን አድርጓል፡፡ ሉሲዎቹ በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታቸው ከደቡብ ሱዳን ጋር ተገናኝተው ድል ሲያደርጉ ከተጠቀመው ቋሚ አሰላለፍ ግብ ጠባቂዋ እምወድሽ ይርጋሸዋን በታሪኳ በርገና እንዲሁም ናርዶስ ጌትነትን በኝቦኝ የኝ በመለወጥ ለጨዋታው ቀርበዋል፡፡

ለፍፃሜ ለማለፍ ብርቱ ትግልን በጠየቀው የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ዩጋንዳዎች በተጋጣሚያቸው ላይ በተወሰነ መልኩ ብልጫን ማሳየት ቢችሉም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንደተለመደው ኳስን መሠረት ያደረገ የጨዋታ መንገድን በመከተል ዕልህ አስጨራሽ የሆነ እንቅስቃሴን አድርጓል፡፡

ሁለቱ ሀገራት ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ የማጥቃት ኃይልን ይዘው ሜዳ ላይ በሁለተኛው አጋማሽ መታየት ቢችሉም ሙሉ የጨዋታው ዘጠና ደቂቃ ያለ ጎል መጠናቀቁን ተከትሎ ወደ ሰላሳ ጭማሪ ደቂቃ አምርተዋል፡፡ ግልፅ የግብ ማግባት ሙከራዎችን ሲፈጥሩ የታዩት ዩጋንዳዎች የተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ ሊያበቃ 4 ደቂቃዎች ሲቀሩት በአጥቂዋ ፋዚላ ኢኩዋፑት አማካኝነት የማሸነፊያዋን ግብ አስቆጥረዋል።

ውጤቱን ተከትሎ የውድድሩ አስተናጋጅ ዩጋንዳ ወደ ፍፃሜ አልፋለች።

ከደቂቃዎች በፊት ኢትዮጵያ በነበረችበት ምድብ ሁለት በአንደኝነት ያጠናቀቀችሁ ታንዛኒያ ከብሩንዲ ጋር መርሐ-ግብሯን አከናውና ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት ተረታለች። ይህንን ተከትሎ የፊታችን ቅዳሜ ዩጋንዳ እና ቡሩንዲ የውድድሩን ዋንጫ ከፍ ለማድረግ የሚፋለሙ ይሆናል።