ዋልያዎቹ ፈርዖኖቹን አንበርክከዋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ሁለተኛ ጨዋታው ማላዊ ላይ ግብፅን ገጥሞ ከሙሉ የጨዋታ ብልጫ ጋር 2-0 መርታት ችሏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከቀናት በፊት በማላዊ ከተሸነፈበት ጨዋታ ሽመልስ በቀለ እና ጋቶች ፓኖምን በሱራፌል ዳኛቸው እና መስዑድ መሀመድ ምትክ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ በማካተት ወደ ሜዳ ገብቷል።

ከጨዋታው መጀመር አንስቶ ከፍ ያለ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን የያዘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጋጣሚው እምብዛም ከሜዳው እንዳይወጣ ማድረግ ችሏል። ከኳስ ውጪም በፍጥነት አፍኖ ኳሶችን በማስጣል እና በቶሎ ወደ ማጥቃት ወረዳ ለመድረስ ሲጥር ይታይ ነበር። ሆኖም የቡድኑ ቅብብሎች በሚፈለገው መጠን ወደ ሳጥን ሳይደርሱ ቢቆዩም ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ግን ይበልጥ ግብፆች ለማቆም የተቸገሯቸውን ንክኪዎች በሳጥኑ ዙሪያ መከወን ችለዋል። 16ኛው ደቂቃ ላይ ጋቶች ፓኖም ከሳጥን ውጪ ባደረገው ሙከራ ወደ ፈርኦኖቹ የግብ ክልል መድረስ የጀመሩት ዋልያዎቹ 21ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥረዋል። አቡበከር ናስር በቀኝ መስመር የደረሰውን ኳስ ይዞ ሰብሮ በመግባት መሀመድ አላን በድንቅ ሁኔታ በማለፍ ወደ ግብ የላከውን ዳዋ ሆቴሳ ከኦማር ጋባር ጋር ታግሎ ከግቡ አፋፍ ላይ አስቆጥሯል።

ከግቡ በኋላ ግብፆች በተሻለ መረጋጋት ረዘም ባሉ ኳሶች ወደ ኢትዮጵያ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ቢያዱርጉም የኢትዮጵያዊያኑ ጥቃት ግን ይበልጥ ተጠናክሮ የቀጠለ ነበር። በተለይም ዋልያዎቹ መሀል ሜዳ ላይ ከግብፅ ተጫዋቾች የሚያስጥሏቸውን ኳሶች በቀኝ መስመር አድልተው በፍጥነት ወደ አደጋ ዞን ያደርሱ የነበረበት መንገድ አስገራሚ ነበር። በሌላ በኩል ቡድኑ ከግብፅ ተከላካዮች ጀርባ የነበረውን ሰፊ ክፍተት ለመጠቀም ከተቃረበባቸው አጋጣሚዎች 24ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ናስር ከአማኑኤል የደረሰውን ኳስ ይዞ በመግባት ያደረገው ሙከራ በግቡ ቋሚ የተመለሰበት እጅግ ለግብ የቀረበው ነበር።

ፈርኦኖቹ የግብ ሙከራ ሳያደረጉ ጨዋታው እንዲጋመስ ያደረገው የዋሊያዎቹ አቀራረብ በፈጣን ጥቃት ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ቀጥሏል። 35ኛው ደቂቃ ላይ ቡድኑ በአስፈሪ ቅብብሎች ሰርጎ ገብቶ ሽመልስ በቀለ ባሳለፈው እና አቡበከር ከመረብ ባገናኘው ኳስ መሪነቱን ቢያሰፋም ከጨዋታ ውጪ በሚል ተሽሮበታል። ሆኖም 40ኛው ደቂቃ ላይ በዚሁ የቀኝ መስመር ዋልያዎቹ ፈጣን ጥቃት ሰንዝረው አማኑኤል ገብረሚካኤል ያሳለፈለትን ሽመልስ በቀለ በፍጥነት ከግብ ክልል ደርሶ በጠንካራ ምት በመሀመድ አቡ ጋባል መረብ ላይ አሳርፎታል። 

በአጋማሹ ሰባት የግብ ሙከራ ያደረጉት ኢትዮጵያዊያኑ በጭማሪ ደቂቃም በአማነኤል ገብረሚካኤል እና ጋቶች ፓኖም አማካይነት የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን አግኝተው ነበር። በአንፃሩ ግብፆች በአጋማሹ ማብቂያ እና በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ሦስት ቅያሪዎችን ለማድረግ የተገደዱበትን ደካማ 45 ደቂቃ አሳልፈዋል።

ከዕረፍት መልስ ግብፆች በተሻለ የማጥቃት ጫና ጀምረዋል። ሆኖም ዋልያዎቹ ከኳስ ውጪ ከፍ ያለ ትጋት በማሳየት ጥቃቶችን ከጅምሩ በማቋረጥ ወደ ግብ ክልላቸው አደጋን ሳይጋብዙ ተንቀሳቅሰዋል። ፈርኦኖቹ አልፎ አልፎ ከቆሙ ኳሶች መከራዎችን ለማድረግ ቢሞክሩም አደገኛዎቹ አጋጣሚዎች ግን አሁንም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኩል የሚታዩ ነበር። ቡድኑ ግብፆች በማጥቃት ፍላጎታቸው መነሻነት ከኋላ የሚተዉትን ክፍተት በፈጣን ሽግግሮች ደጋግሞ ማጥቃት ሲችል የመጨረሻ ውሳኔዎች ችግር እንጂ በተለይም በአቡበከር ናስር እና ዳዋ ሆቴሳ አማካይነት ለመጨረሻ ዕድልነት የተጠጉ የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችሏል።

ግብፆች ቀስ በቀስ በኳስ ቁጥጥሩ የተሻለ ድርሻን መያዝ ቢችሉም ዋልያዎቹ ተደጋጋሚ ቅብብሎችን በማቋረጥ የግብፅ ጫና ወደ ሙከራነት እንዳይቀየር ማድረግ ችለዋል። ይልቁኑም 71ኛው ደቂቃ ላይ ድንቅ የነበረው አማኑኤል ገብረሚካኤል ተከላካዮችን ሳጥኑ መግቢያ ላይ ሲያታልል አቡበከር ተቀብሎ አክርሮ የመታው ኳስ ወደ ላይ ተነስቷል። በቀጣዮቹ ደቂቃዎችም ዋልያዎቹ የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን አይፍጠሩ እንጂ የጨዋታውን ግለት በማቀዝቀዝ ነገሮችን አረጋግተው እና የግብፅን ጫና አቅም አሳጥተው ዘልቀዋል።

ግብፃዊያኑ 87ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ የሳጥኑ ጠርዝ ዑማር ማረሙሽ ሩቁ ቋሚ ላይ ሞክሮት ለጥቂት በወጣው እንዲሁም 89ኛው ደቂቃ ላይ አደል ዓሊ ከሳጥን ውስጥ አክርሮ መትቶ ፋሲል ገብረሚካኤል ባዳነው ኳስ በጨዋታው ለመጀመሪያ ጊዜ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን አድርገው ነበር። ሆኖም ዋልያዎቹ ጭማሪ ደቂቃዎቹንም በተረጋጋ አኳኋን በማጠናቀቅ ጨዋታውን በ2-0 ድል ደምድመዋል።

በሌላው የምድቡ ጨዋታ ኮናክሪ ላይ ማላዊን ያስተናገደችው ጊኒ 1-0 ማሸነፍ በመቻሏ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በግብ ልዩነት በልጦ ምድቡን መምራት ጀምሯል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰማ ዜና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ከብሔራዊ በድኑ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከእግርኳስ በላይ ትርጉም ያለው ድል ማስመዝገቡን በመግለፅ ከሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ጋር አስቸኳይ ስብሰባ አድርገው ፌዴሬሽኑ ለቡድኑ አባላት የ2 ሚሊየን ብር ሽልማት ለማበርከት መወሰኑን ተናግረዋል።