የመዲናው ክለብ ተጫዋቾች ልምምድ አቁመዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥ የታችኛው ቀጠና ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ ተጫዋቾች ልምምድ አቁመዋል።

የሀገራችን ከፍተኛ የሊግ እርከን በሆነው ውድድር ላይ የሚሳተፈው አዲስ አበባ ከተማ በወራቶች ልዩነት ሦስት አሰልጣኞችን ቀያይሮ ለከርሞ በሊጉ ለመትረፍ እየተውተረተረ እንደሚገኝ ይታወቃል። ሊጉ ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ግንቦት 15 ከተቋረጠ ከሳምንት እረፍት በኋላ እዛው ባህር ዳር መቀመጫውን ወተር ፍሮንት ሆቴል አድርጎ ሲዘጋጅ የነበረው ቡድኑ ከደሞዝ ጋር በተያያዘ በዛሬው ዕለት ተጫዋቾቹ ልምምድ እንዳቆሙ ታውቋል።

የክለቡ ተጫዋቾች ትናንት አመሻሽ በሆቴላቸው የጋራ ስብሰባ አድርገው ያስቀመጡትን አቅጣጫ ለዝግጅት ክፍላችን የላኩ ሲሆን ክለቡ ያልፈፀመላቸውን የ70 ቀን (ሁለት ወር ከአስር ቀን) ደሞዝ እስካልከፈላቸው ድረስ ልምምድ እንደማይሰሩ ተስማምተው በፊርማቸው ማፅናታቸውን ገልፀውልናል። ተጫዋቾቹ ክለቡ እስከ ነገ ድረስ ደሞዛቸውን ካልከፈለ ከነገ በስትያ እሁድ ወደየቤታቸው እንዲያሰናብታቸው መስማማታቸውን እና ለሚመለከተው አካል በደብዳቤ ማሳወቃቸውን ጨምረው አስረድተውናል። ዛሬ ረፋድ በነበረው የልምምድ መርሐ-ግብርም አለመሳተፋቸውን አውቀናል።

የተጫዋቾቹን ጥያቄ ክለቡ እንዴት ያየዋል ብለን ሥራ አስኪያጁን አቶ ነፃነት ታከለ አግኝተን ተከታዩን ምላሽ ተቀብለናል። “የተጫዋቾቹ ጥያቄ አግባብ ያለው ነው። ያለ ደሞዝ ስሩ አንልም። ስፖርተኞች መቸገር የለባቸውም። ጥያቄም አትጠይቁ አንልም። ይሄንን እኔን ጨምሮ ሁሉም የቦርድ አባል ያምናል። ነገርግን ከወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ በተፈጠሩ የሥራ መደራረቦች ክፍተቱ እንደተፈፀመ መግለፅ እፈልጋለው። ትናንት ማታ የተጫዋቾቹ ጥያቄ ደርሶኛል። እኔ ዛሬ ለቦርድ ልኬያለው። እንዳልኩት ከሥራ መደራረብ ጋር ተያይዞ ትንሽ መጣበቦች አሉ። ነገርግን ክለባችን የተጫዋቾችን ደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅም ያለመክፈል መጥፎ ታሪክ የለውም። ዘገየ እንጂ ተጫዋቾቹም እንደሚደርሳቸው ያውቁታል። ስለዚህ እነሱም ሥራቸውን እየሰሩ ጥያቄያቸውን ያቅርቡ እኛም የነሱን ጥያቄ ለመመለስ እንስራ። በአጭር ጊዜ ያላቸው ደሞዝ እና ኢንሴንቲቭ እንደሚደርሳቸው መግለፅ እወዳለው።”