ቅድመ ዳሰሳ | የ26ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች ምክንያት ተቋርጦ ሲቀጥል ነገ የሚደረጉትን ሦስት ጨዋታዎች እንደሚከተለው ዳሰናቸዋል።

ሲዳማ ቡና ከ አርባምንጭ ከተማ

የጨዋታ ሳምንቱ የሚጀምረው እንዲሁም ሊጉ ወደ ዕይታ የሚመለሰው ረፋድ ላይ በሚደረገው የሲዳማ እና የአርባምንጭ ጨዋታ ይሆናል። 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሲዳማ በአሰልጣኝ ወንድምአገኝ ተሾመ ስር ሁለት ተከታታይ ድሎችን አስመዝግቦ ነበር ወደ ዕረፍቱ ያመራው። የአፍሪካ መድረክ ተሳትፎ የማግኘት ዕድሉ የቀነሰ ቢመስልም የሦስተኛነት ደረጃውን ማስጠበቅ ግን በቀሪ ጨዋታዎች ሊያሳካው የሚፈልገው እና ከነገው ጨዋታ የሚጀምረው ዓላማው ሆኗል። አርባምንጭ ከተማም በበኩሉ ሽንፈት ፀንቶበት የሰነበተበትን ጊዜ ከሦስት ጨዋታዎች አምስት ነጥቦችን ባሳካባቸው የመጨረሻ ሳምንታት ማከም ችሏል። ይህንን ማድረጉ ከወራጅ ቀጠናው በስድስት ነጥቦች እንዲርቅ ያስቻለው ሲሆን ይህን ክፍተት ከዚህ በላይ አስፍቶ እፎይ ለማለት ይረዳው ዘንድ የነገው ጨዋታ ውጤት አስፈላጊው ነው።

ሲዳማ ቡና ነገ ከሚቀጥለው ውድድር 15 ቀናትን ቀደም ብሎ ልምምዱን ጀምሯል። ሲዳማ በመጨረሻው የባህር ዳሩ ጨዋታ አሳይቶት የነበረው የመልሶ ማጥቃት ጥራት ውድድሩ ሳይቋረጥ ቢቀጥል የተሻለ ጎልብቶ ሊታይ ይችል የነበረ ሲሆን ይህንን ጠንካራ ጎን የማስቀጠል ዕቅድ እንደሚኖረው ይገመታል። የመጨረሻ ኳሶችን በመካከለኛ ርቀት ቅብብሎች ማድረስ የማይቸግራቸው አማካዮቹ በነገው ጨዋታ ጠጣሩን የአርባምንጭ ከተማ የመከላከል አደረጃጀት አልፎ ጥሩ ቅንጅት ለነበረው የይገዙ ፣ ሳልሀዲን እና ሀብታሙ ጥምረት ማድረስ የሚችሉበት ስኬት ለሲዳማ ወሳኝ ይሆናል።

ለተጫዋቾቹ የአንድ ሳምንት ዕረፍት ሰጥቶ በጊዜ ወደ ዝግጅት የተመለሰው አርባምንጭ ከተማ ወትሮም በማይታማበት የአካል ብቃቱ ተሻሽሎ እንደሚመለስ ይጠበቃል። ተጋጣሚ ከራሱ ሜዳ እንዳይወጣ በማድረግ አፍኖ ኳስ ለመንጠቅ ፍላጎት ያለው ቡድኑ ከዕረፍቱ አንፃር ይህንን አቀራረብ በበቂ ሁኔታ ለመተግበር የሚያስችል ቁመና ላይ ሆኖ ሊመለስ ይችላል። ይህ መሆኑ ከመሀል ሜዳው በፊት ከሲዳማ ቡና የመሀል ክፍል ጋር ብርቱ ፍልሚያ ሊያስመለክተን ሲችል የአዞዎቹ የአጥቂ ክፍልም የተቋረጡ ኳሶችን በአግባቡ ወደ ውጤት የመቀየር የቤት ሥራ ይጠብቀዋል።

ሲዳማ ቡና የኋላ ደጀኑ ጊትጋት ኩትን በአስር ቢጫ ካርድ ቅጣት ከማጣቱ በቀር ቀሪው የቡድኑ ስብስብ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሲሆን በአርባምንጭ በኩል ደግሞ በላይ ገዛኸኝ እና ሳምሶን አሰፋ ጉዳት ላይ ይገኛሉ።

የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ፣ ረዳቶች ዳንኤል ጥበቡ እና ትንሳኤ ፈለቀ ፣ አራተኛ ዳኛ ሀብታሙ መንግሥቴ

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ 15 ጊዜ ተገናኝተው 10 ጨዋታ በአቻ ውጤት አጠናቀዋል። አርባምንጭ 3 ሲያሸንፍ ሲዳማ ቡና 2 ማሸነፍ ችሏል። አርባምንጭ 10 ፣ ሲዳማ ቡና ደግሞ 8 ግቦችን አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሲዳማ ቡና (4-1-4-1)

መክብብ ደገፉ

አማኑኤል እንዳለ – ተስፋዬ በቀለ – ያኩቡ መሐመድ – ሰለሞን ሀብቴ

ሙሉዓለም መስፍን

ሀብታሙ ገዛኸኝ – ዳዊት ተፈራ – ፍሬው ሰለሞን – ይገዙ ቦጋለ

ሳላዲን ሰዒድ

አርባምንጭ ከተማ (4-4-2)

ይስሀቅ ተገኝ

ወርቅይታደስ አበበ – አሸናፊ ፊዳ – በርናንድ ኦቼንግ – ተካልኝ ደጀኔ

ሙና በቀለ – አቡበከር ሸሚል – እንዳልካቸው መስፍን – ሱራፌል ዳንኤል

አህመድ ሁሴን – ኤሪክ ካፓይቶ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ባህር ዳር ከተማ

የጨዋታ ሳምንቱ ተጠባቂ ፍልሚያ ከቀትር በኋላ በጊዮርጊስ እና ባህር ዳር መካከል ይደረጋል። በላይኛው የሰንጠረዡ ክፍል ባለው ፉክክር ልዩነት የፈጠረ ሽንፈት ሁለተኛ ደረጃ ላይ በሚገኘው ፋሲል ከነማ ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ በድጋሚ ነጥብ መጣልን የሚያስበው አይመስልም። በአዳማው ድል ተነቃቅቶ የነበረው ባህር ዳርም በሲዳማ ቡና የደረሰበት ሽንፈት ከወራጅ ቀጠናው በምቾት እንዳይርቅ ስላደረገው ተጨማሪ ሦስት ነጥብ ማሳካት ዋጋው በቀላሉ የሚገመት አይሆንም። በመሆኑም ቡድኖቹ ከሽንፈት ይምጡ እንጂ ማሸነፍ በየፊናቸው የሚያስገኝላቸው ትርፍ ቀላል ባለመሆኑ ጨዋታው ብርቱ ፉክክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል።

ዛሬ ረፋድ ባህር ዳር የደረሰው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ25ኛው ሳምንት ጨዋታ መልስ ለተጫዋቾቹ የአራት ቀናት ዕረፍት ብቻ በመስጠት ወደ ልምምድ ተመልሷል። ለሀገራዊ ግዴታ ከቡድኑ ጋር ያልነበሩት ዩጋንዳዊው ግብ ጠባቂው ቻርልስ ሉኩዋጎ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ቅዳሜ አመሻሽ ቡድኑን በመቀላቀል ትናንት እና ዛሬ አብረው ልምምድ በመስራት ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሆነዋል። ከሁሉም በላይ ጊዮርጊስ የወትሮው ጥንካሬዎቹን መድገም ካልቻለበት የፋሲል ከነማው ጨዋታ በኋላ የሊጉ ወደ ዕረፍት ማምራት ተጠቃሚ ያደረገው ይመስላል። ያንን ጨዋታ ረስቶ በሙሉ ኃይል በቀደመ በራስ መተማመኑ ላይ መገኘት ደግሞ በውድድሩ ማብቂያ ላይ ከሚኖሩ መሰል ፈታኝ ጨዋታዎች አንፃር አስፈላጊነቱ የጎላ ነው።

ለ15 ቀናት ያህል በዝግጅት ላይ የቆዩት ባህር ዳሮችም እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ በሥነ ልቦናው ረገድ ለመስተካከል ዕረፍቱ በጎ ነገር ይዞላቸው እንደመጣ ማሰብ ይቻላል። አዳማን ሲረቱ ቡድኑ የታየበት የዕፎይታ ስሜት በሲዳማ ቡናው ሽንፈት መበረዙ የጣና ሞገዶቹ በተከታታይ ጨዋታዎች ይበልጥ ጫና ውስጥ እንዳይገቡ የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ክፍተቱ አግዟቸዋል። በኳስ ቁጥጥር ላይ መሰረቱን ያደረገው ግን ደግሞ ከሜዳው ከመውጣት ጀምሮ ፈተና ሲገጥመው የሚታየው እና ግለሰባዊ ስህተቶች የማያጡት ቡድኑ በነገው ከባድ ጨዋታ በታክቲኩ ረገድም ያሉበትን ስህተቶች በተሻሻለ የውህደት ስራ አርሞ በብዙ ርቀት ተሻሽሎ መቅረብ ይጠበቅበታል።

የቅዱስ ጊዮርጊሱ እስማኤል ኦሮ አጎሮ ልምምድ ቢጀምርም ለጨዋታዎች ዝግጁ አይደለም። በተመሳሳይ ጉዳት ላይ የሰነበቱት ቡልቻ ሹራ እና ከነዓን ማርክነህ ጠንከር ያለ ልምምድ ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን አቤል ያለው ደግሞ ጉዳቱ እንዳያገረሽበት በጥንቃቄ ልምምድ እየሰራ ቆይቷል። በባህር ዳር ከተማ በኩል የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ፍፁም ዓለሙ ከጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ ባለማገገሙ ምክንያት የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ከመሆኑ በቀር ሌላ የጉዳት እና ቅጣት ዜና የለም።

የጨዋታ ዳኞች – ዋና ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ ፣ ረዳቶች ትግል ግዛው እና ሙሉነህ በዳዳ አራተኛ ዳኛ ዳንኤል ግርማይ

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ በድኖች እስካሁን በሊጉ ለአምስት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሁለት ሁለት ጊዜ ተሸናንፈው በአንድ ጨዋታ ያለ ግብ ተለያይተዋል። በእነዚህ ግንኙነቶች ቅዱስ ጊዮርጊስ አራት ባህር ዳር ከተማ ሁለት ግቦችን አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)

ቻርለስ ሉኩዋጎ

ሱሌይማን ሀሚድ – ምኞት ደበበ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ሄኖክ አዱኛ

ሀይደር ሸረፋ – ጋቶች ፓኖም

ተገኑ ተሾመ – የአብስራ ተስፋዬ – ቸርነት ጉግሳ

አማኑኤል ገብረሚካኤል

ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)

አቡበከር ኑራ

ሣለአምላክ ተገኘ – ፈቱዲን ጀማል – መናፍ ዐወል – አህመድ ረሺድ

አብዱልከሪም ኒኪማ – ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – አለልኝ አዘነ

ተመስገን ደረሰ – ኦሲይ ማዉሊ – ግርማ ዲሳሳ

ወልቂጤ ከተማ ከ መከላከያ

የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ በሰራተኞቹ እና በጦሩ መካከል ይከናወናል። አርባምንጭን በሰፊ ጎል ከረታ በኋላ በአራት ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦችን ብቻ ያሳካው ወልቂጤ ከተማ ከአደጋ ዞኑ በአምስት ነጥቦች ከፍ ብሎ ይቀመጥ እንጂ ከስጋት ነፃ ነው ማለት አይቻልም። በከፍተኛ መሻሻል ውስጥ የከረመው መከላከያም ጥሩ ንቃት ላይ ሆኖ ይታይ እንጂ ከነገ ተጋጣሚው በአንድ ነጥብ ብቻ ከፍ ብሎ የሚገኝ በመሆኑ ራሱን ወደ አስተማማኝ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ወደ ሜዳ ይገባል። በነጥብ እና በደረጃ የመቀራረባቸው ነገር ሲታይም ጨዋታውን በአዎንታዊ ውጤት መጨረስ መቻል አሸናፊውን ወደ መረጋጋት ሊወስደው እንደሚችል ይታሰባል።

ወልቂጤ ከተማ ትልቁ ፈተናው ሆኖ የቀጠለው የፋናንስ ችግር ወሳኙ የውድድሩ ምዕራፍ ላይ ማገርሸቱ በነገው ጨዋታ ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም። ቡድኑ የተሟላ ስብስብ ይዞ ወደ ልምምድ ከገባ ሦስት ቀናትን ብቻ እንዳስቆጠረ ሲታሰብ የጨዋታ ዝግጁነቱ ተጫዋቾች በግላቸው በዕረፍቱ ጊዜ በነበረቸው የስራ መጠን ላይ እንዲወሰን ያስገድዳል። የቡድኑ አሰልጣኞችም ስብስቡን ለጨዋታ ብቁ ለማድረግ እንዲሁም ታክቲካዊ ተግባቦቱ ከፍ ብሎ እንዲቀርብ ከማድረግ ባለፈ በሥነ ልቦናው ረገድ ሰፊ ስራ የሚጠብቃቸው ይመስላል።

ከግንቦት 24 ጀምሮ ዝግጅት ላይ የሰነበተው መከላከያ በጥሩ ግለት ላይ እያለ ሊጉ መቋረጡ ተጠቃሚ አያደርገውም። ወጥ ብቃት ሲያሳይባቸው በነበሩት ጨዋታዎች በተለይም የቡድኑ የማጥቃት ፍላጎት ጨምሮ ከኳስ ውጪ የሚያሳየው ትጋትም አድጎ ሙሉ ለሙሉ የተለየ መልክን ይዞ ተመልክተነዋል። በመጨረሻው ጨዋታ ድሬዳዋን ሲገጥም ደከም ብሎ ቢታይም ሦስት ጨዋታዎችን ያሸነፈበትን እንዲሁም ፋሲል ከነማንም የፈተነበትን ያንን የአዕምሮ ከፍታ እና ታክቲካዊ ብስለት በተጫዋቾች ምርጫ ከተረጋጋው ስብስቡ መልሶ ማግኘት ይኖርበታል።

ወልቂጤ ከተማ ጌታነህ ከበደን በቅጣት አበባው ቡታቆን በጉዳት የሚያጣ ሲሆን በመከላከያ በኩል ልምምድ ላይ ጉዳት ካስተናገደው ግሩም ሀጎስ ውጪ ሁሉም ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ። ከዚህ በተጫማሪ ለሳምንታት ከሜዳ ርቀው የነበሩት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌም ወደ ሜዳ እንደሚመለሱ ይጠበቃል።

የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ ተፈሪ አለባቸው ፣ ረዳቶች ሸዋንግዛው ተባባል እና ወጋየሁ አየለ ፣ አራተኛ ዳኛ አዳነ ወርቁ

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ዘንድሮ ለሁለቱ ተጋጣሚዎች የመጀመሪያ ግንኙነት የነበረው ጨዋታ በጦሩ 2-1 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ነበር።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልቂጤ ከተማ (4-4-2 ዳይመንድ)

ሮበርት ኦዶንካራ

ተስፋዬ ነጋሽ – ዳግም ንጉሴ – ዋሀብ አዳምስ – ረመዳን የሱፍ

በኃይሉ ተሻገር – ዮናስ በርታ – ሀብታሙ ሸዋለም – አብዱልከሪም ወርቁ

ጫላ ተሺታ- ያሬድ ከበደ

መከላከያ (4-2-3-1)

ክሌመንት ቦዬ

ገናናው ረጋሳ – አሌክስ ተሰማ – አሚን ነስሩ – ዳዊት ማሞ

ኢማኑኤል ላርዬ – ምንተስኖት አዳነ

ተሾመ በላቸው – አዲሱ አቱላ – ቢኒያም በላይ

እስራኤል እሸቱ