የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 2-2 ባህር ዳር ከተማ

ጠንካራ ፉክክር አስተናግዶ በአቻ ውጤት ከተቋጨው ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች ይህንን ብለዋል።

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ – ባህር ዳር ከተማ

ስለጨዋታው

“እጅግ በጣም ውጥረት የነበረበት ጨዋታ ነው። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ እኛ ካለንበት ደረጃ ወደ ላይ ከፍ ለማለት ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ቻምፒዮንነቱን ለመጠበቅ በዛ ምክንያት ውጥረት የነበረበት ጨዋታ ነው። በመጀመሪያው አጋማሽም በሁለተኛው አጋማሽም በሁለታችንም በኩል ጥሩ ፉክክር ነበር ማለት እችላለሁ።

ከቡድናቸው የሚጠብቁትን ስለማግኘታቸው

“በመጀመሪያው አጋማሽ በትክክል የምፈልገውን ነገር አግኝቻለሁ ማለት እችላለሁ። ነገር ግን የተቆጠረብን ፍፁም ቅጣት ምት ብዙ አጨቃጫቂ በመሆኑ ምክንያት የልጆቼን ስሜት አውርዶት ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ይህንን አስተካክለን እነሱም አግብተውብን እኛም አግብተን ውጤት ተጋርተን ወጥተናል። ከትልቅ ቡድን ጋር ነው ውጤት የተጋራነው ፤ ከዕረፍት መልስ ነው አንድ ነጥብ ይዘን የወጣነው። ስለዚህ ይህ በቀጣይ ጨዋታ ትልቅ የሞራል ስንቅ ይሆነናል ብዬ ነው የማስበው።

ከባድ ተጋጣሚ ጋር ነጥብ ስለመጋራታቸው

“ቻምፒዮናውን ከሚመራው ቡድን አንድ ነጥብ ማውሰዳችን ጥንካሬያችንን ነው የሚያሳየው። ይበልጥ ደግሞ በቀጣይ ጨዋታዎች በራስ መተማመናቸውን እንዲያዳብሩ ያደርጋቸዋል። ለቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ቀሪ አራት ጨዋታዎች እንደ ዋንጫ ጨዋታ ነው የምንጫወተው ምክንያቱም ከታች ወደ ላይ ለመምጣት።”

አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ውጤቱ በዋንጫ ፉክክሩ ጫና ውስጥ የሚከታቸው ስለመሆኑ

“ይሄ ምንም የሚያሳስብ ነገር የለውም። ስለዋንጫ ሳይሆን ስለዛሬው ጨዋታ ጥሩ ጨዋታ አይተናል ብዬ አስባለሁ በሁለታችንም በኩል። ጥሩ የማጥቃት ጨዋታዎች ነበሩበት።

ዘግይተው ወደ ጨዋታው ምት ስለመግባታቸው

“እግርኳስ ሂደት ነው እና ታግሰህ ማግኘት የምትችለውን ሰዓት አግኝተህ መጠቀም አለብህ። ተጠቅመናል ሁለት ጎሎች አግብተናል። ከዚያ በኋላ እንደገና እኛ ላይ ገብቷል። ኳሱ ይሄንን ነው የሚያንፀባርቀው ስለዚህ መጥፎ አልነበረም ጥሩ ጨዋታ ነበር በሁለታችንም በኩል ብዬ አስባለሁ።

የሚፈልጉትን ክፍተት ስለማግኘታቸው

“ክፍተቱን ብዙ አላገኘነውም። የፈለግነውን ነገር በትክክለኛው መንገድ አላገኘነውም። በእርግጥ አንዳንድ ኳሶች አግኝተናል ስላልተጠቀምንበት ነው። ግን ልጆቹ ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል። ምክንያቱም የውህደት ሥራዎች ያስፈልጉ ነበር። ብሔራዊ ቡድን ሰባት ስምንት ተጫዋቾች አልነበሩም። እነዚህን አዋህደን አንድ ቀን ነው ሊያውም ቀላል ልምምድ ነው የሰራነው። ጥሩ ነገር አይቻለሁ እላለሁ ምክንያቱም የጋቶች መዳከም ከዚያ የመጣ ስለሆነ ከዚህ አንፃር ይሄንን ውጤት ይዘን መውጣታችን ምንም ችግር የለውም። ስለዋንጫውም የሚያሰጋን ነገር የለም ፤ በራሳችን እጅ ያለ ስለሆነ በየጨዋታው የራሳችንን ማድረግ የሚገባንን እናደርጋለን። ”