ሪፖርት | አዲስ አበባ ከተማ ባለቀ ሰዓት ሦስት ነጥብ አሳክቷል

አሰልቺ በነበረው ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ ተቀይሮ በገባው ብዙዓየሁ ሰይፈ የመጨረሻ ደቂቃ ጎል ከድል ጋር ተገናኝቷል።

ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው የወላይታ ድቻ እና አዲስ አበባ ከተማ ጨዋታ የመጀመሪያውን ሙከራ ለማስመልከት12 ደቂቃዎችን መጠበቅ ግድ ብሎታል። በተጠቀሰው ደቂቃም የድቻው አማካይ ሀብታሙ ንጉሴ ከስንታየሁ መንግስቱ የተቀበለውን ኳስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶት ለጥቂት ወጥቶበታል። በእንቅስቃሴ ደረጃ የዋና ከተማው ክለብ ከኳስ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ሲጥሩ የታየ ሲሆን የጦና ንቦቹ ደግሞ ቀጥተኝነት ላይ ያተኮረ አጨዋወት ሲከተሉ ነበር። ከሌላ 12 ደቂቃዎ በኋላ ደግሞ አናጋው ባደግ ራሱ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት አሻምቶ በረከት ወልደዮሐንስ በሩቁ ቋሚ ተገኝቶ በግንባሩ ለማስቆጠር ጥሯል።

መሐል ሜዳ ላይ የተገደበ የሚመስለው ጨዋታ ጥንቃቄ ቅድሚያ ተሰጥቶበታል። ቡድኖቹም የተቀናጀ የማጥቃት አጨዋወት ማድረግ ሳይችሉበት ቀርቷል። የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበረው አዲስ አበባ በበኩሉ በ33ኛው ደቂቃ ከመዓዘን ምት መነሻን ያደረገ ኳስ በሪችሞንድ አዶንጎ አማካኝነት ሞክሮ መክኖበታል። ቀሪ የአጋማሹ ደቂቃዎችም በተመሳሳይ ለዐይን የሚማርኩ ትዕይንቶች ሳይከሰቱበት ያለ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ተጠናቋል።

ተመሳሳይ ሆኖ የቀጠለው የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም ግብ ጠባቂዎችን የፈተነ ጥቃት እምብዛም አልተስተዋለበትም። በእንቅስቃሴ ደረጃ ሁለቱም ቡድኖች በተሻለ ፈጠን በማለት ወደ ተጋጣሚ ግብ ለመድረስ ቢጥሩም የተዋሀደ መናበብ ሳይኖር አጋጣሚዎቹ ሲመክኑ ነበር። የሆነው ሆኖ የጨዋታው የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ በ58ኛው ደቂቃ ተከናውኗል። በዚህም ሪችሞንድ አዶንጎ ወደ ቀኝ ካዘነበለ የሳጥኑ ጫፍ ጠበቅ ያለ ምት ወደ ግብ ልኮ ቢኒያም ገነቱ ተቆጣጥሮበታል።

የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ለውጠው በማስገባት ከጨዋታው አንዳች ነገር ለማግኘት ያሰቡት ወላይታ ድቻዎች ውጥናቸው እምብዛም ሲሰምር አልታየም። ይባስ አንፃራዊ ብልጫ ተወስዶባቸዋል። በተቃራኒው በፍላጎት ደረጃ የተሻሉት አዲስ አበባዎች በ70ኛው ደቂቃ ወደ ግብ ቀርበው ነበር። በዚህም እንዳለ ከበደ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ አዶንጎ ከተከላካዮች በላይ ዘሎ በግንባሩ ለማስቆጠር ሞክሮ ዒላማውን ሳተበት እንጂ መሪ ሊሆኑ ነበር።

በዚህ አጋማሽ ድከም ያሉት የአሠልጣኝ ፀጋዬ ተጫዋቾች በ82ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርገዋል። በዚህም ተቀይሮ የገባው እድሪስ ሰዒድ ከሳጥን ውጪ በግራ እግሩ አክርሮ መትቶ የነበረ ቢሆንም የግብ ዘቡ ዳንኤል ይዞበታል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ደጉ ደበበ ከመሀል ሜዳ ያሻማውን የቅጣት ምት አዮብ በቀታ ራሱ ላይ ሊያስቆጥረው ተቃርቦ ነበር።

ሙሉ 90 ደቂቃው ተጠናቆ በተጨመሩት ደቂቃ ላይ የቅጣት ምት ያገኙት አዲስ አበባዎች አጋጣሚውን የግብ ምንጭነት አድርገውታል። በዚህም የተገኘውን የቅጣት ምት አሰጋኸኝ መትቶት ተከላካዮች ሲመልሱት ያገኘው ብዙዓየሁ ሰይፈ በቀኝ እግሩ መረብ ላይ አሳርፎታል። ጨዋታውም በዚሁ ውጤት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ አዲስ አበባ ከተማ ነጥቡን 28 ሲያደርስ ወላይታ ድቻ ደግሞ 37 ነጥቦችን በመያዝ የነበሩበት 14 እንዲሁም 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።