የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 2-1 ባህር ዳር ከተማ

የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በሀዋሳ ከተማ አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

ስለጨዋታው

“መጀመሪያም እንዳሰብነው ኳሱን ጠብቀን እነሱ ወደ ተከላካይ አማካያቸው የመሀል ተከላካዮቹ ገፍተው የሚመጡ ሰዓት ላይ የእኛ አጥቂዎች እዛ አካባቢ ሸሽተው ይቆሙና ያንን እነሱ የሚከፍቱትን ቦታ ነው ስንፈልግ የነበረው። በዛም አጋጣሚ ነው ጎል ያገባነው። ግን በጣም ታክቲካሊ ዲስፕሊንድ ሆነን የመጫወቻ ቦታ በተለይ አደገኛውን በደንብ ስለዘጋንባቸው እነሱ በሚሳሳቱት ነበር ለመሄድ ያሰብነው። ጎሎቹም ያንን ነው የሚያሳዩት።

የተቃታኒ ቡድን ድጋፍን ስለተቋቋሙበት መንገድ

“አንደኛ ባለፈው ማሸነፋችን ነው። ሀዋሳ ባለፉት አምስት ስድስት ሳምንታት ልጆች በጉዳት ስላልነበሩ ቡድናችን በሥነልቦናው ተጎድቶ ነበር። የልጆቹ መመለስ እና የበቀደሙን ጨዋታ ማሸነፍ ዛሬ በጥሩ የራስ መተማመን እንዲገቡ አድርጓል። ያ ነው ወደ አሸናፊነት የመለሰን ፤ በልጆቹ መመለስ ቡድናችን አቅም አግኝቷል ብዬ ነው የማስበው።”

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ – ባህር ዳር ከተማ

ስለጨዋታው

“እጅግ ውጥረት የበዛበት ጨዋታ ነው የነበረው ዘጠናውን ደቂቃ። በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ተንቀሳቅሰናል ብዬ አስባለሁ። በድንገት በተፈጠር ስህተት ከተቆጠርብን በኋላ ልጆቻችን ላይ ትንሽ የመውረድ ስሜት ነበር። በመልበሻ ክፍል ውስጥ እንደገና አስተካክለን ከገባን በኋላ ሳንነሳ ጎሉ በጊዜ ገባብን። እንደገና ለመነሳት ደግሞ ጊዜ ወስዶብናል። ትንሽ ውጥረት ነበረው ብዬ አስባለሁ ጨዋታው። ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ሹት መተው ካገቧት ጎል በስተቀር ብዙ እኛ ላይ የሞከሩት ነገር የለም። ብዙ እነሱ ሜዳ ላይ ነው የዋልነው ፤ ያጠቃነው። ግን ከጭንቀት የተነሳ ፣ ከመራጋጋት ማነስ የተነሳ ጎል ማስቆጠር አልቻልንም ከአንዷ በስተቀር።

ስለማውረድ ስጋቱ

” አሁን ያለንበት ደረጃ ጥሩ የሚባል አይደለም። ስለዚህ በቀጣይ ቀሪ ሦስት ጨዋታዎች ለማሸነፍ የምንችለውን ሁሉ አድርገን ፣ ውጤቱን ቀይረን ቡድናችንን ፕሪምየር ሊጉ ውስጥ ለማቆየት አስፈላጊውን መስዕዋትነት እንከፍላለን ብዬ ነው የማስበው።”