ቅድመ ዳሰሳ | የ28ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ፍልሚያዎች

የሳምንቱን ፍልሚያዎች የሚያስጀምሩት የነገ ሁለት መርሐ-ግብሮች እንደሚከተለው ዳሰናል።

ባህር ዳር ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

በ26ኛ ሳምንት በሀዋሳ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ የተረቱት ባህር ዳር እና ድሬዳዋ ካሉበት አስጊ ቀጠና ለመውጣት የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ ምንም ማቅማማት የማይሰጥበት ጉዳይ ነው። ካለፉት ዘጠኝ ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው 27 ነጥብ 6ቱን ብቻ ያሳካው ባህር ዳር ከተማ ሳይጠበቅ እያንዧበበበት ካለው የመውረድ ስጋት ለመላቀቅ መታተር ይጠበቅበታል። በመቀመጫ ከተማው እየተጫወተ የሚገኘው ቡድኑ እንደ ሌሎቹ ክለቦች የሜዳ እና የደጋፊ ጥቅሙን ማስከበር ተስኖት ይገኛል። ባሳለፍነው ሳምንት ከሀዋሳ ከተማ ጋር ተጫውቶ ከመረታቱ በፊት የሊጉን መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፈትኖ ነጥብ ያስጣለው ስብስቡ በጠቀስነው ጨዋታ ጠንካራ ብቃቱን ያስቀጥላል ተብሎ ቢታሰብም ይህ ሳይሆን ቀርቷል። በእንቅስቃሴ ደረጃ ጨዋታውን በጥሩ ሁኔታ ጀምሮ የነበረው ቡድኑ በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ እና በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ለተቆጠሩበት ጎሎች በቶሎ ምላሽ መስጠት ተስኖት ተሸንፏል። በወሳኞቹ ደቂቃዎች ግብ ማስተናገዱ ደግሞ ጭንቀት ላይ የነበሩትን ተጫዋቾች እንዳይነሳሱ ያደረገ ይመስላል። ይህ ቀድሞ ግብ የማስተናገድ እና ወደ ጨዋታ ለመመለስ የመቸገር ነገር ከዚህ በፊትም ስለተስተዋለ ነገም ቀድሞ ግብ እንዳያስተናግድ መጠንቀቅ ይገባዋል። ከዚህ ውጪ ግን ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በድምሩ 40 ሙከራዎችን ያደረገው ቡድኑ በመከላከሉ ረገድ ክፍተቶችን አዘውትሮ ለሚያሳየው ድሬዳዋ ፈተና እንደሚሰጥ ይገመታል።

እንዳለፉት ዓመታት ዘንድሮም በደረጃ ሰንጠረዡ ግልባጭ ያልጠፋው ድሬዳዋ ከተማ በአዲሱ አሠልጣኝ ሳምሶን አየለ እየተመራ ቀና ለማለት ቢሞክርም ሊጉ ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ተቋርጦ ሲመለስ የቀድሞ ደካማ ጎኖቹ ዳግም እየጎሉ ይገኛል። እርግጥ ከመቋረጡም በፊት መጠናኛ መንገራገጭ ላይ የነበረ ቢሆንም አሁን በብዙ መስፈርቶች የወረደ ብቃት ላይ ያለ ይመስላል። በተለይ በሁለቱ ወሳኝ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች ያለው ስልነት የወረደ ሆኗል። በዋናነት ደግሞ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ሦስት ነጥብ ከማስረከቡ በላይ ሦስት ሦስት ግቦችን ማስተናገዱ ምነኛ የኋላ መስመሩ ችግሩ እንዳገረሸበት ይጠቁማል። ከላይ እንደጠቀስነው በውጤት ረገድ ፍሬያማ ባይሆንም በእንቅስቃሴ ረገድ መጥፎ ደረጃ ላይ የማይገኘው ባህር ዳር ደግሞ ማጥቃቱ ጠንከር ያለ ስለሆነ ክፍተቱ ይባስ እንዳይጋለጥ ያሰጋል። የሆነው ሆኖ አማካይ መስመር ላይ ተጫዋቾችን በማብዛት የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሱ ለማድረግ የሚጥሩት ድሬዎች ነገም በዚሁ መንገድ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ሲገመት ቀጥተኝነትን በመከተል ግብ ለማስቆጠር እንደሚሞክሩ ይታሰባል። የኳስ ቁጥጥርን አሳድጎ ፍሬያማ የማድረግ ነገር ግን ነገ ከፍ ብሎ መምጣት ይገባዋል።

ባህር ዳር ከተማ የጨጓራ ህመም ላይ ከሚገኘው ተከላካዩ ፈቱዲን ጀማል ውጪ የሚያጣው ተጫዋች የሌለ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ ግን ሁሉም ተጫዋቾቹ ዝግጁ እንደሆኑለት ተገልጿል።

የእርስ በርስ ግንኙነት

– የነገ ተጋጣሚዎቹ እስካሁን አምስት የሊግ ጨዋታዎችን አድርገዋል። ባህር ዳር ከተማ ሁለቴ ድሬዳዋ ደግሞ አንዴ ድል ሲቀናቸው የመጨረሻ ሁለት ጨዋታቸው ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነበር። በግንኙነቶቹ ባህር ዳር አምስት ድሬዳዋ ደግሞ አራት ግቦች አሏቸው።

ግምታዊ አሰላለፍ


ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)

ፋሲል ገብረሚካኤል

አህመድ ረሺድ – ሰለሞን ወዴሳ – መናፍ ዐወል – ግርማ ዲሳሳ

ፍፁም ዓለሙ – ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – አለልኝ አዘነ

ተመስገን ደረሰ – ኦሴይ ማዉሊ – ዓሊ ሱሌይማን

ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)

ፍሬው ጌታሁን

እንየው ካሣሁን – አውዱ ናፊዩ – መሳይ ጳውሎስ – አብዱለጢፍ መሐመድ

ዳንኤል ደምሴ – ብሩክ ቃልቦሬ

አብዱርሀማን ሙባረክ – ሙኸዲን ሙሳ – ጋዲሳ መብራቴ

ሄኖክ አየለ

ወልቂጤ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የማይገኘው ወልቂጤ ከተማ ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ታርቆ ካለበት የስጋት ቀጠና ለመሸሽ ነገ ከሲዳማ ወሳኝ ፍልሚያ ያደርጋል። ያለ ወሳኝ አጥቂው ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች የከወነው ወልቂጤ ከተማ ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ተጋጣሚ ላይ ግብ ሳያስቆጥር ቀርቷል። በዋናነት ደግሞ በሁለቱም ጨዋታዎች ቡድኑ ባለመደው ሀሰተኛ ዘጠኝ ቁጥር መጫወቱ በላይኛው ሳጥን ክፍተቱ እንዲፈጠር እንዳደረገ ይገመታል። በጊዮርጊሱ ጨዋታም አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተው ነበር። የሆነው ሆኖ ቡድኑ ነገም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው ጌታነህ ከበደን ባያገኝም ካለበት አስጊ ቀጠና አንፃር የማጥቃት አጨዋወቱን አስተካክሎ ጨዋታውን እንደሚቀርብ ይታሰባል። ከዚህ ውጪ ከኳስ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ የሚሞክረው ስብስቡ ነገም የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ወስዶ መጫወትን ሊመርጥ ይችላል። በወራጅ ቀጠናው ከሚገኙ ክለቦች ውጪ በሊጉ ብዙ ግቦችን በማስተናገድ ቀዳሚ የሆነው ቡድኑም በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት የሚፎካከር አጥቂ የያዘ እና ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በአማካኝ ሁለት ግቦችን ካስቆጠረው ሲዳማ የሚሰነዘረውን ጥቃት መመከቻ ጥሩ መፍትሔ ማዘጋጀት ይጠበቅበታል።

ካለፉት አራት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ የተረታው ሲዳማ ቡና በበኩሉ ብልጫ ወስዶም ሆነ ተወስዶበት እጅ የማይሰጥባቸው ጨዋታዎች መኖራቸው ውጤት ተኮር እንደሆነ ይጠቁማሉ። ባሳለፍነው ሳምንትም ጅማ አባ ጅፋርን ሲረታ በኳስ ቁጥጥርም ሆነ የግብ ሙከራዎችን በማድረግ ብልጫ ተወስዶበት ጨዋታን መቆጣጠር ላይ ትኩረት አድርጎ ተሳክቶለታል። ይባስ ከ25 ደቂቃዎች በላይ በጎዶሎ ተጫዋች ተጫውቶ በእጁ የገባውን ሦስት ነጥብ አሳልፎ አለመስጠቱ የሚያስደንቀው ነው። ከምንም በላይ በተከላካይ መስመሩ ላይ ወሳኞቹን ጊት ጋትኩት እና ያኩቡ መሐመድን አጥቶ የነበረው ስብስቡ ነገ ተጫዋቾቹን ማግኘቱ ትልቅ እፎይታ ይሰጠዋል። ተጫዋቾቹ ባልነበሩበት ያለፉት ፍልሚያ በቡድናዊ እና ግለሰባዊ ስህተቶች የግብ ዘቡ መክብብ ደገፉ በተደጋጋሚ ሲጋለጥ ነበር። እንዳልነው የተጫዋቾቹ መመለስ ግን ትልቅ መረጋጋት የሚሰጥ ይሆናል። በሜዳው ሌላኛው ጫፍም ጠንካራ ተጫዋቾች ያሉት ሲዳማ ነገም ለተጋጣሚው ወልቂጤ ፈተናን እንደሚሰጥ ይጠበቃል። በተለይ የቡድኑን 74% ግብ ያስቆጠሩት ይገዙ እና ሳላዲን የሚያደርጉት የማጥቃት እንቅስቃሴ ለወልቂጤ ተከላካዮች የራስ ምታት መስጠቱ የማይቀር ይመስላል።

ወልቂጤ ከተማ የግራ ተከላካዩ አበባው ቡጣቆ እና የቀኝ ተከላካዩ ተስፋዬ ነጋሽን በጉዳት ምክንያት ነገ አይጠቀም። ሲዳማ ቡና በበኩሉ እንደገለፅነው ጊት እና ያኩቡን ከቅጣት መልስ ሲያገኝ መኳንንት ካሣ ብቻ ከፍልሚያው ውጪ ሆኖበታል።

የእርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ በተገናኙባቸው የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች ዓምና ሲዳማ ቡና በሁለቱም ዙሮች ዳዊት ተፈራ ባስቆጠራቸው የፍፁም ቅጣት ምት ግቦች በተመሳሳይ የ1-0 ውጤት አሸንፎ የነበረ ሲሆን በዘንድሮ ሦስተኛ ግንኙነታቸው ደግሞ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ሮበርት ኦዶንካራ

ዮናታን ፍሰሀ – ዮናስ በርታ – ዋሀብ አዳምስ – ረመዳን የሱፍ

በኃይሉ ተሻገር – ኢሞሞ ንጎዬ – ሀብታሙ ሸዋለም

ጫላ ተሺታ – አብዱልከሪም ወርቁ – ያሬድ ታደሰ

ሲዳማ ቡና (4-1-4-1)

መክብብ ደገፉ

አማኑኤል እንዳለ – ጊት ጋትኩት- ያኩቡ መሐመድ – ሰለሞን ሀብቴ

ሙሉዓለም መስፍን

ሀብታሙ ገዛኸኝ – ዳዊት ተፈራ – ፍሬው ሰለሞን – ይገዙ ቦጋለ

ሳላዲን ሰዒድ