ሪፖርት | የጣና ሞገዶቹ ወሳኝ ሦስት ነጥቦች አሳክተዋል

የመናፍ ዐወል ብቸኛ ግብ በፍሬው ጌታሁን ድንቅ ብቃት እስከፍፃሜው በጨዋታው ውስጥ የቆየው ድሬዳዋ ከተማን አሳዛኝ ተሸናፊ አድርጋለች።

ባህር ዳር ከተማዎች ከሀዋሳው ሽንፈት ባደጓቸው ለውጦች አቡበከር ኑራ በፋሲል ገብረሚካኤል ፣ ሰለሞን ወዴሳ ህመም በገጠመው ፈቱዲን ጀማል ፣ ሳለአምላክ ተገኘ በግርማ ዲሳሳ ፣ ፉዓድ ፈረጃ በአብዱልከሪም ኒኪማ ፣ ፍፁም ዓለሙ በአለልኝ አዘነ እና አደም አባስ በተመስገን ደረሰ ቦታ ተተክተው ገብተዋል።

በአርባምንጭ ከተማ ከተሸነፉበት ጨዋታ ሁለት ለውጦች ያደረጉት ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ ያሲን ጀማል እና አቤል አሰበን በእንየው ካሳሁን እና ዳንኤል ደምሴ ምትክ አስጀምረዋል።

በጥሩ ፉክክር በጀመረው ጨዋታ ውጤቱን አጥብቀው የሚፈልጉት ተጋጣሚዎቹ ጠንቀቅ ያለ አቀራረብን ይዘው ታይተዋል። የተሻለ የኳስ ቁጥጥር እና የማጥቃት ጉልበት የታየባቸው ባህር ዳሮች በዋነኝነት በአደም አባስ እና ፍፁም ዓለሙ እንቅስቃሴ ላይ ተመስርተው በቅብብሎች ወደ አደጋ ዞን ሲቀርቡ ተመልክተናል። ሆኖም ኦሴይ ማዉሊ እና ፉዓድ ፈረጃ ካደረጓቸው ግማሽ የሚባሉ ሙከራዎች ሌላ ቡድኑ ያለቀለት ዕድል አልፈጠረም።

በተመሳሳይ በአቤል አሰበ አንድ ጠንካራ የማይባል ሙከራ ያደረጉት ድሬዳዋ ከተማዎች ከወትሮው በተለየ ንቃት በጥሩ የመከላከል አደረጃጀት የተጋጣሚያቸውን የኳስ ፍሰት መቋቋም ችለዋል። 

ከዚህ ባለፈ የቡድኑ መልሶ ማጥቃት ውጤታማ አይሁን እንጂ ወደ ውሃ ዕረፍቱ መቃረቢያ ላይ በንፅፅር በተሻለ ሁኔታ ከሜዳው ሲወጣ ይታይ ነበር።
ከውሃ ዕረፍቱ መልስ የድሬዳዋ መሻሻል ቀጥሎ የማጥቃት ጫናው ወደ ባህር ዳር ሜዳ አድልቷል። 32ኛው ደቂቃ ላይ ማማዱ ሲዲቤ ከሳጥን ውጪ የጨዋታው የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግም ችሎ ነበር። በአንፃሩ ባህር ዳሮች የማጥቃት ፍሰታቸው እና የኳስ ቁጥጥራቸው አቅም ቀንሶ ታይተዋል። ያም ቢሆን 38ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ዓለሙ ወደ ግብ የላከውን ወደ ግራ ያደለ የቅጣት ምት ኳስ ፍሬው ጌታሁን ሲመልስ አደም በድጋሚ ወደ ሳጥን የላከበት አጋጣሚ የድሬዳዋ የመከላከል ችግር ያገረሸበትን ቅፅበት ፈጥሯል። ኳሱን አህመድ ረሺድ ተቆጣጥሮ ሲያሳልፍለት የድሬ የጨዋታ ውጪ መረብ በአቤል አሰበ አቋቋም ሲከሽፍ ትክክለኛ ቦታ ላይ የተገኘው መናፍ ዐወል ተቀብሎ ጎል አድርጎታል።

ከዕረፍት መልስ በነበሩ የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች ጨዋታው የሙከራ ናዳ አስተናግዷል። 50ኛው ደቂቃ ላይ ሣለአምላክ ተገኘ ወደ ሳጥን የላከውን ኳስ የድሬዳዋ ተጫዋቾች ጥፋት ተሰርቷል ብለው በተዘናጉበት ቅፅበት ዓሊ ሱለይማን ነፃ ዕድል አግኝቶ ከቅርብ ርቀት ቢሞክርም ፍሬው አድኖበታል። ዓሊ ከአንድ ደቂቃ በኋላም ከተከላካይ ጀርባ ሌላ የመጨረሻ ዕድል ቢያገኝም ፍሬው ከሳጥን ውጪ ሄዶ አቋርጦበታል። ዓሊ ለሦስተኛ ጊዜ 58ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ዓለሙ በግራ ሰብሮ ገብቶ ያደረሰውንም ኳስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በሌላኛው የጎል ፅንፍ ደግሞ 58ኛው ደቂቃ ላይ አብዱለጢፍ መሐመድ ከግራ በረጅሙ ያሻማውን ኳስ መናፍ ሳይገጨው ቀርቶ አቤል ከበደ ከሳጥን ውስጥ ወደ ግብ ሲልከው አቤል አሰበ በግንባሩ መጭረፍ ተሳነው እንጂ ድሬዳዋ ለግብ ቀርቦ ነበር። ከደቂቃ በኋላ ማማዱ ሲዲቤ ከማዕዘን ምት በግንባሩ የገጨው ኳስ ደግሞ ከግብ ጠባቂው አልፎ አህመድ ረሺድ ከግብ አፋፍ ላይ አውጥቶታል። በመቀጠል ባህር ዳሮች እንደገና ለግብ ሲቃረቡ 65ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም እና ማዉሊ በአንድ ሁለት ቅብብል የሰነዘሩት መልሶ ማጥቃት ለፍፁም የመጨረሻ ዕድል ቢያስገኝም ፍሬው በድጋሚ ደሬዳዋን ከሌላ ግብ ታድጓል።

ቀጣዮቹ ደቂቃዎች የጨዋታው እንቅስቃሴ ጋብ ብሎ ባልተሳኩ የማጥቃት ሂደቶች እና በተጨዋቾች ጉዳት እና ቂያሪዎች ተተክቷል። 78ኛው ደቂቃ ላይ ግን የፍሬው ጌታሁን አስደናቂ የግብ አጠባበቅ የኦሴይ ማዉሊ እና ተቀይሮ የገባው ግርማ ዲሳሳን ተከታታይ ሙከራዎች ግብ ከመሆን ሲያድን ተመልክተናል።

በቀሪ ደቂቃዎች የባህር ዳር የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶች እየከሰሙ የድሬዳዋ ከተማ ግብ የማግኘት ፍላጎትን የተከተለ ጥቃት እየጎላ ማጥቷል። በእርግጥ ቡድኑ ከዚህ ጫና ያሰበውን ያህል ዕድል ባይፈጥርም መጨረሻ ደቂቃ ላይ አንድ ነጥብ የሚያስገኝለትን ግብ አግኝቶ ነበር። ጭማሪ ደቂቃ ላይ ማማዱ ሲዲቤ ከማዕዘን ምት የደረሰ እና አቡበከር ኑራ የጨረፈውን ኳስ በግንባር ወደ ሁለተኛው ቋሚ ልኮት ሱራፌል ጌታቸው በግንባር ቢያስቆጥርም የዕለቱ አርቢትር ተፈሪ አለባቸው ጥፋት ተሰርቷል በሚል ሳያፀድቁት ቀርተው ጨዋታው በባህር ዳር ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በዚህም የጣና ሞገዶቹ ነጥባቸውን 33 አድርሰው ከአደጋው ሸሸት ሲሉ በከፍተኛ ሀዘን እና እምባ ታጅበው ሜዳውን ለቀው የወጡት ድሬዳዋ ከተማዎች በ29 ነጥቦች በወራጅ ቀጠናው ውስጥ ለመቆየት ተገደዋል።