ሪፖርት | ሙጂብ እና ሱራፌል ከ20 ሳምንታት በኋላ ዐፄዎቹ የሊጉን መሪነት እንዲረከቡ አድርገዋል

ፋሲል ከነማ በሙጂብ ቃሲም እና ሱራፌል ዳኛቸው ጎሎች ታግዞ ቅዱስ ጊዮርጊስ እስኪጫወት ድረስ የሊጉ መሪ ሆኗል።

ባሳለፍነው ሳምንት ሀዋሳ ከተማን አንድ ለምንም የረቱት ፋሲል ከነማዎች ሦስት ነጥብ ካሳኩበት ጨዋታ አምበላቸው ያሬድ ባየህን በከድር ኩሊባሊ ምትክ በቀዳሚ አሰላለፋቸው አካተዋል። በተቃራኒው በአርባምንጭ ከተማ የተሸነፉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ ወደ ደቡብ አፍሪካ ጉዞ የጀመረው አጥቂያቸው አቡበከር ናስርን ጨምሮ ገዛኸኝ ደሳለኝ እና ሮቤል ተክለማርያምን በእንዳለ ደባልቄ፣ ቴዎድሮስ በቀለ እና ታፈሰ ሰለሞን ተክተዋል።

ገና ከጅምሩ ጨዋታውን ወደ ራሳቸው ማድረግ የያዙት ፋሲል ከነማዎች መሪ ለመሆን ሲንቀሳቀሱ ነበር። ኢትዮጵያ ቡናዎች በበኩላቸው ኳሱን በተሻለ ለመቆጣጠር እና በትዕግስት በራሳቸው ሜዳ ለመቆየት ሲጥሩ ተስተውሏል። በጨዋታው የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ሙከራ የተደረገውም በፋሲል ከነማ አማካኝነት ነበር። በ8ኛው ደቂቃም በረከት ደስታ በግራ መስመር ፈጣን ሩጫ በማድረግ ወደ ሳጥን የላከውን ኳስ ሙጂብ ቃሲም ለመጠቀም ጥሮ በግብ ብረቶቹ መካከል የነበረው በረከት አማረ ራሱን ለጉዳት ዳርጎ አምክኖታል።

በርከት ባሉ ደጋፊዎች ታጅቦ ሞቅ ባለ ድባብ የቀጠለው ጨዋታው በ12ኛው ደቂቃ መሪ አግኝቷል። በዚህም ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች በድንቅ ጥምረት ቡድናቸውን ሲጠቅሙ የነበሩት ሱራፌል ዳኛቸው እና ሙጂብ ቃሲም ዳግም ተጣምረው ፋሲልን ቀዳሚ አድርገዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ሱራፌል ከተከላካዮች ጀርባ የላከውን የተመጠነ ኳስ ሙጂብ ፈጥኖ በማግኘት እርጋታ በተሞላበት ሁኔታ ከመረብ ጋር አዋህዶታል።

በራሳቸው ሜዳ ኳስን ከማንሸራሸር ባለፈ በላይኛው ሜዳ አላማ ያላቸው ቅብብሎችን በማድረግ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ያልቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች በ35ኛው ደቂቃ በአምበላቸው አማኑኤል ዮሐንስ አማካኝነት ዒላማውን የሳተም ቢሆን የመጀመሪያ ጥቃት ሰንዝረረው ተመልሰዋል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ዊሊያም ሰለሞን ፍጥነቱን ተጠቅሞ ግብ ለማስቆጠር ጥሮ ሚኬል ሳማኪ አውጥቶበታል። መሪዎቹ ፋሲል ከነማዎች በበኩላቸው ግቡን ካገኙ በኋላ የማጥቃት ኃይላቸውን ቀነስ አድርገው መጫወትን መርጠዋል። ይህ ቢሆንም ግን ከመዓዘን ምት የተነሳን ኳስ በረከት አሻምቶ ሽመክት በግንባሩ ሁለተኛ ግብ ሊያደርገው ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በስምንተኛው ደቂቃም ፋሲሎች እጅግ አስቆጪ ኳስ አምልጧቸዋል። በዚህም በራሳቸው ሜዳ ጥፋት ተሰርቶ በፍጥነት የጀመሩትን ኳስ ከተከላካይ ጀርባ በረከት ደርሶት ወደ ግብነት ለመቀየር ቢጥርም ሌላኛው በረከት ሰውነቱን አግዝፎ መልሶበታል። አሁንም ከኳስ ጋር ዘለግ ያለውን ጊዜ እያሳለፉ የሚገኙት ቡናማዎቹ ይህንን አስደንጋጭ ሙከራ ካስተናገዱ ከደቂቃ በኋላ እንዳለ ደባልቄን ዒላማ ያደረገ ተከላካይ ሰንጣቂ ልከው ወደ ጨዋታው ለመመለስ ቢጥሩም አጥቂው ከግብ ጠባቂው ጋር የሚያገናኘውን ኳስ መቆጣጠር ሳይችል ቀርቶ ዕድሉ አምልጦታል።

64ኛው ደቂቃ ላይ ግን ውጤቱን አስተማማኝ የሚያደርጉበትን ጎል ዐፄዎቹ አግኝተዋል። በዚህ ደቂቃ ሱራፌል የላከውን ተንጠልጣይ ኳስ በረከት በሞክሼው ግብ ጠባቂ አናት ላይ ለማስቆጠር ጥሮ ሲመለስበት በቅፅበቱ ላይ የነበረው ሙጂብ አግኝቶት ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ግል አድርጎታል።

ሁለተኛው ጎል ከተቆጠረ በኋላ ጨዋታው እምብዛም ሳቢ መሆን አልቻለም። እርግጥ አሠልጣኝ ካሣዬ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ለውጠው በማስገባት ከጨዋታው አንዳች ነገር ለማግኘት ቢጥሩም ውጥናቸው ሳይሰምር ቀርቷል። ሙሉ 90 ደቂቃው ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው በረከት በሳጥን ውስጥ ቴዎድሮስ ጥፋት ሰርቶበት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ሱራፌል ዳኛቸው ወደ ግብነት ቀይሮት ዐፄዎቹ ከጨዋታው ሦስት ነጥብ እና ሦስት ጎል ይዘው እንዲወጡ አድርጓል።


ውጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከነማ ከአንድ ሰዓት በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታውን እስኪያደርግ የሊጉን መሪነት በ61 ነጥቦች ሲረከብ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ በ20 ነጥቦች አንሶ የነበረበት 6ኛ ደረጃ ላይ ፀንቶ ተቀምጧል።