ቅድመ ዳሰሳ | የ29ኛ ሳምንት የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ዳሰሳ

በቀጣዩ ዓመት በሊጉ ለመክረም ትልቅ ትግል የሚደረግበትን የአዳማ እና ድሬዳዋ ጨዋታ እንዲሁም የረፋዱን የመከላከያ እና ሀዋሳ ጨዋታ እንደሚከተለው ቃኝተናል።

የዘንድሮ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ በደረጃ ሰንጠረዡ አናትም ሆነ ግርጌ አጓጊ ፉክክር እያስመለከተ እንደሚገኝ ይታወቃል። የዋንጫው መዳረሻ እስከ 30ኛ ሳምንት ድረስ እንደሚዘልቅ ዛሬ ያወቅን ሲሆን ሰበታ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋርን ተከትሎ ወደ ታችኛው የሊግ እርከን የሚወርደውን አንድ ክለብ ለመለየት ግን ከነገ ጨዋታዎች ፍንጭ የምናገኝ ይሆናል። ከተጋጣሚዎቹ አራት ክለቦች ሦስቱ ቀጥተኛ የመውረድ ስጋት ያለባቸው ሲሆኑ ሀዋሳ ከተማ ግን አራተኛ ደረጃን ለመያዝ እንዲሁም ለክብር ብቻ ሦስት ነጥብን እያሰበ ወደ ሜዳ የሚገባ ይሆናል። ቡድኑ ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ታርቆ የአሸናፊነትን መንገድ ይዞ ተከታታይ ቢያሸንፍም ባሳለፍነው ሳምንት በፋሲል ከነማ አንድ ለምንም ተረቷል። ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ደግሞ ነገ ጠንክሮ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይገመታል።

የሀዋሳ ከተማ የነገው ተጋጣሚ መከላከያ በሊጉ መትረፉ በሂሳባዊ ስሌቶች ባይረጋገጥም ከቀሪ ስድስት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ካገኘ ለከርሞ በከፍተኛው የሀገሪቱ የሊግ እርከን ይወዳደራል። በጊዜያዊ አሠልጣኙ ዮርዳኖስ አባይ እየተመራ በጥሩ የድል ጉዞ ላይ የነበረው መከላከያ ያለፉትን ጨዋታዎች ግን በአጨዋወትም ሆነ በውጤት ረገድ መንገራገጭ የገጠመው ይመስላል። እርግጥ ቡድኑ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ቢረታም አንዱንም ግን አላሸነፈም። ከሦስት ነጥብ ውጪ ደግሞ ያለፉትን 445 ደቂቃዎች ከግብ ጋር መገናኘት የተሳበው ስብስቡ ከበታቹ የሚገኙት ክለቦች አላሸንፍ አሉ እንጂ አጣብቂኝ ውስጥ ይገባ ነበር። በእንቅስቃሴ ረገድም በነፃነት ማጥቃት ላይ ትኩረት በመስጠት የተለወጠ የሚመስለው ቡድኑ ጨዋታ በጨዋታ ከዚህ አጨዋወት እየወጣ ወደ ቀደመ ቀጥተኛነቱን እና ጥንቃቄ አዘል ሀሳቡ የተመለሰ ይመስላል። በነገው ጨዋታ ደግሞ በአራቱም የሜዳ ክፍሎች በጉዳት እና በቅጣት የሚያጧቸውን ተጫዋቾች እና የሀዋሳን ፈጣን የማጥቃት አጨዋወት ታሳቢ በማድረግ የበለጠ ከኳስ ውጪ ላለ አደረጃጀት ትኩረት ሊሰጥ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የዕለቱ ወሳኝ ጨዋታ 10 ሰዓት ሲል ይደረጋል። በአንድ ደረጃ እና ሁለት ነጥቦች ተበላልጠው 13ኛ እና 14ኛ ቦታ ላይ የሚገኙት አዳማ እና ድሬዳዋ ከተማ የነገውን ፍልሚያ ማሸነፍ ምንም አማራጭ የሌላቸው ጉዳይ ነው። እርግጥ አዳማ ከተማ አንድ ነጥብ ከጨዋታው ይዞ መውጣት ለክፉ የሚዳርገው ባይሆንም 30ኛ ሳምንትን ሳይጠብቅ ለመትረፍ ሦስት ነጥብ ለማሳካት እንደሚጥር ይታሰባል። በጊዜያዊ አሠልጣኙ ይታገሱ የሚመራው አዳማ ከተማ ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች ድል ማድረግ ባይችልም በእንቅስቃሴ ደረጃ ግን ጥሩ ተፎካካሪ ሲሆን ይታያል። በዋናነት በመከላከሉ ረገድ እምብዛም እንከን የሌለበት ስብስቡ የሊጉ ዝቅተኛ ግቦችን ተጋጣሚ ላይ ያስቆጠረ መሆኑ ችግሩን ፍንትው አድርጎ የሚነግረን ይመስላል። ፈጣኖቹን አጥቂዎች ያማከለ የማጥቃት አጨዋወት ቢከተልም ጎል ፊት ያለው የስልነት ችግር አሁን የሚገኝበት ደረጃ ላይ እንዲገኝ አድርጓል። የነገው ተጋጣሚ ድሬዳዋ ከተማ ማሸነፍ የማያወላዳ አማራጩ ስለሆነ ነቅሎ ሊወጣ ስለሚችል የግብ ዕድሎችን ሊያገኝ ይችላል ፤ አጋጣሚዎቹን መጠቀም ደግሞ ትኩረት ሊሰጥበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑንን መናገር ያስፈልጋል።

ባለፉት አምስት ጨዋታዎች “ከድጡ ወደ ማጡ” የሆነበት ድሬዳዋ ከተማ ከአምስቱም የመውረድ ስጋት ካለባቸው ክለቦች የባሰ አጣብቂኝ ውስጥ ያለ ክለብ ነው። በውድድር ዓመቱ ሦስት አሠልጣኞችን አፈራርቆ የተጠቀመው ድሬዳዋ አጣብቂኝ ውስጥ ነው ብንልም የራሱን ዕድል የመወሰን አቅም ግን አሁንም አለው። ነገርግን ነገ ቀጥተኛ ያለመውረድ ተፎካካሪውን በ30ኛ ሳምንት ደግሞ የዋንጫ ተወዳዳሪው ፋሲልን መግጠሙ ፈተናውን ያበዛበታል። ይህ ቢሆንም ግን ከባዱን ፈተና መፋለም ከላይ እንደገለፅነው አማራጭ የሌለው ጉዳይ ስለሆነ ማጥቃት ላይ የተመረኮዘ አጨዋወት ሊከተሉ ይችላሉ። ይህንን ተከትሎ ከወትሮ በተለየ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን በመጠቀም ጠጣሩን የአዳማ የመከላከል አደረጃጀት ለመፈተን ይጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ማጥቃቱ ላይ ቅድሚያ ቢሰጥም መከላከሉ ግን መዘንጋት የለበትም። በተለይ ያለፉትን ጨዋታዎች የታየው የግለሰባዊ እና መዋቅራዊ የመከላከል ክፍተት ተሻሽሎ ሚዛናዊ አጨዋወት ያስፈልጋል። ያለበለዚያ በፈጣኖቹ የአዳማ አጥቂዎች ሊቀጣ ይችላል።

በማስቀጠል ሁለቱን ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው ሰብስበናል።

መከላከያ ከ ሀዋሳ ከተማ


የቡድን ዜናዎች

ሀዋሳ ከተማ ከወንድማገኝ ማዕረግ እና ፀጋሰው ድማሙ ውጪ የሚያጣው ተጫዋች የሌለ ሲሆን መከላከያ ደግሞ ቢኒያም በላይ፣ ዳዊት ማሞ፣ ደሳለኝ ደባሽ እና ብሩክ ሰሙን በጉዳት እንዲሁም ክሌመንት ቦዬን በቅጣት ከነገው ጨዋታ ውጪ አድርጓል።

የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ ተከተል ተሾመ ፣ ረዳቶች አማን ሞላ እና ኤልያስ አበበ ፣ አራተኛ ዳኛ እያሱ ፈንቴ

ተጨማሪ ዳኞች – ደረጀ አመራ እና ተስፋዬ ንጉሴ

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች 29 ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ ከተማ 13 በማሸነፍ ቅድሚያውን ሲይዝ መከላከያ 7 ጨዋታ አሸንፏል። ቀሪዎቹ 9 ጨዋታዎች አቻ የተለያዩባቸው ግንኙነቶች ናቸው።

– በርካታ በጎሎች የታጀበ ታሪክ ያለው ይህ ግንኙነት 65 ጎሎች የተቆጠሩበት ሲሆን ሀዋሳ 37 ፣ መከላከያ 28 ጎሎችን አስቆጥረዋል። በመጨረሻ 4 ግንኙነታቸው ብቻም 17 ጎሎች ተቆጥሯል።

ግምታዊ አሰላለፍ


መከላከያ (4-2-3-1)

ሙሴ ገብረኪዳን

ገናናው ረጋሳ – አሌክስ ተሰማ – አሚን ነስሩ – ግሩም ሀጎስ

ኢማኑኤል ላርዬ – ምንተስኖት አዳነ

ተሾመ በላቸው – አዲሱ አቱላ – ሰመረ ሀፍታይ

እስራኤል እሸቱ

ሀዋሳ ከተማ (3-5-2)

መሀመድ ሙንታሪ

ካሎንጂ ሞንዲያ – አዲስዓለም ተስፋዬ – ላውረንስ ላርቴ

ዳንኤል ደርቤ – አብዱልባስጥ ከማል – ወንድምአገኝ ኃይሉ – በቃሉ ገነነ – መድሃኔ ብርሃኔ

ኤፍሬም አሻሞ – ብሩክ በየነ


አዳማ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ


የቡድን ዜናዎች

አዳማ ከተማ በዲሲፕሊን ምክንያት ከስብስቡ ውጪ ካደረጋቸው ቶማስ ስምረቱ እና ዮናስ ገረመው በተጨማሪ የአማኑኤል ጎበናን ግልጋሎት በጉዳት ምክንያት አያገኝም። አጥቂው ዳዋ ሁቴሳ ግን የቅጣት ጊዜውን ጨርሶ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሆኗል። በድሬዳዋ በኩል ያለውን የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባይሳካም ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን ግን በ5 ቢጫ ምክንያት አለመኖሩን ከሊጉ የበላይ አካል ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ ፣ ረዳቶች ትግል ግዛው እና ይበቃል ደሳለኝ ፣ አራተኛ ዳኛ ዮናስ ካሳሁን

ተጨማሪ ዳኞች – ሲራጅ ኑርበገን እና ማዕደር ማረኝ

የእርስ በእርስ ግንኙነት 

– ቡድኖቹ 19 ጊዜ ተገናኝተው አዳማ 9 ጨዋታ በድል ሲያጠናቅቅ ድሬዳዋ 6 አሸንፏል። ቀሪዎቹ 4 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው። አዳማ 20 ፣ ድሬዳዋ 16 ጎሎችንም በግንኙነታቸው አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ


አዳማ ከተማ (4-3-3)

ሴኩምባ ካማራ

ጀሚል ያዕቆብ – ሚሊዮን ሰለሞን – አዲስ ተስፋዬ – ደስታ ዮሐንስ

ፀጋአብ ዮሴፍ – ዮሴፍ ዮሐንስ – ታደለ መንገሻ

አቡበከር ወንድሙ – ዳዋ ሁቴሳ – አሜ መሐመድ

ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)

ደረጄ ዓለሙ

እንየው ካሣሁን – አውዱ ናፊዩ – መሳይ ጳውሎስ – አብዱለጢፍ መሐመድ

ዳንኤል ደምሴ – ብሩክ ቃልቦሬ

አብዱርሀማን ሙባረክ – ሙኸዲን ሙሳ – ጋዲሳ መብራቴ

ሄኖክ አየለ