የትንቅንቁ ተፋላሚዎች መንገድ – ክፍል 1

የውድድር ዓመቱን ወሳኝ የጨዋታ ዕለት በማስመልከት የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከነማን የፉክክር ጉዞ የተመለከተ ፅሁፍ ያዘጋጀን ሲሆን ቀዳሚውን ክፍል በዚህ መልክ አሰናድተናል።

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2014 የውድድር ዘመን ሊጠናቀቅ ሁለት የጨዋታ ቀናት ብቻ ይቀሩታል። ከሁለቱ ቀናት ደግሞ የነገው እጅግ በጉጉት የሚጠበቅ ነው። የውድድሩ አሸናፊ የሚሆነውን ክለብ የሚለዩት ሁለት ተጠባቂ ጨዋታዎች ነገ በተመሳሳይ ሰዓት ከመከናወናቸው በፊትም የቻምፒዮንነት ክብሩን የመድፋት ዕድሉ ያላቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከነማ በዚህ ዓመት የመጡበትን መንገድ ለመቃኘት ወደናል። ቀዳሚው የዚህ ፅሁፋችን ትኩረትም ቡድኖቹ በዝግጅት እና በውድድር ጊዜ ያሳለፏቸውን ጊዜያት የሚያስቃኘን ይሆናል።

ከውድድር በፊት…

የዘንድሮው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከመጀመሩ አስቀድሞ ዋንጫውን ለማሸነፍ ግምት የተሰጣቸው ክለቦችን ብንዘረዝር ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከነማ ከመጀመሪያዎቹ ውስጥ መካተታቸው አይቀርም። ክለቦቹም ቢሆኑ እንደተሰጣቸው ግምት ሁሉ ራሳቸውን በቻምፒዮንነት ደረጃ አሻሽለው ለመቅረብ ጥረት ሲያደርጉ ነበር የ2013ን ክረምት ያሳለፉት።

ከ2009 በኋላ ከሊጉ ክብር ርቆ የሰነበተው ቅዱስ ጊዮርጊስ የተሰረዘውን የውድድር ዓመት ሳይጨምር ለአራተኛ ጊዜ የአሸናፊነት ክብርን መልሶ የመቀዳጀት ፈተናውን ለመጀመር ይጠቅሙኛል የሚላቸውን ማሻሻያዎች አድርጓል። በዋነኝነት ክለቡ የ64 ዓመቱን ሰርቢያዊ አሰልጣኝ ዝላትኮ ክራምፖቲችን በዋና አሰልጣኝነት መንበር አስቀምጧል። ባለፉት ዓመታት በቡድኑ ቀዳሚ ተሰላፊነት ዝርዝር ውስጥ የማይጠፉ ተጫዋቾችን ጨምሮ ዘጠኝ ከሚሆኑ ተጫዋቾቹ ጋር ቢለያይም በምትካቸው ሁለት የውጪ ዜጎችን ጨምሮ ስምንት ተጫዋቾችን በጊዜ አስፈርሞ ቢሾፍቱ በሚገኘው የክቡር ይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ ከትሞ በዝግጅት አሳለፈ። ቡድኑ ከስብስብ ጥልቀት እና ከድል ርሀብ አንፃር ዓመቱን ትልቅ ግምት ተሰጥቶት ቢጀምርም የአዲሱ አሰልጣኝ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር ላይ ሳይታዩ የመቅረታቸው ነገር ጥርጣሬን ፈጥሮ ነበር። ያም ቢሆን የክለቡ ኃላፊዎች ፣ አጠቃላይ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ፣ ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች ይህ የውድድር ዓመት አዲስ ነገር ይዞላቸው እንደሚመጣ በማሰብ በተስፋ የጀመሩት ነበር።

2009 ላይ ወደ ሀገሪቱ የከፍተኛ የሊግ እርከን ብቅ ያለው ፋሲል ከነማ በጥቂት ዓመታት ራሱን በተጠባቂ ክለቦች ደረጃ ከማሰለፍ አልፎ 2013 ላይ የሊጉን ክብር መቀዳጀት ችሏል። የጀመረውን የታላቅነት ጉዞ ለማስቀጠል የቻምፒዮንነት ክብርን ደጋግሞ ማጣጣም መቻል ግድ መሆኑ ለፋሲላዊያኑ አልጠፋቸውም። ይህንን ለማድረግም ባለፉት ዓመታት ስልታዊ በሆነ መንገድ የገነቡት ቡድናቸው ላይ በወጡት ሦስት ተጫዋቾች ቦታ ሦስት አዳዲስ ፈራሚዎችን በማምጣት በአሰልጣኝ ቡድን አባላቶቻቸውም ላይ ለውጥ ሳያደርጉ የቻምፒዮንነት ማግስት ፈተናውን ለመጀመር ወሰኑ። ፋሲል ከነማ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪው ሙጂብ ቃሲምን ክፍተት በተዋጣለት መልኩ የመሸፈን ብቃቱ ከማጠራጠሩ ባለፈ በአፍሪካ መድረክ በሱዳኑ አል ሂላል በደረሰበት ሽንፈት በጊዜ የመሰናበቱ ጉዳይ በተወሰነ መልኩ ጥርጣሬን ጭሯል። ነገር ግን የተረጋጋ የቡድን ግንባታው ዘንድሮም በጥቂት ለውጦች ብቻ ወደ ውድድር መግባቱ አፍርሶ መገንባት የየዓመቱ ዋና ሥራ በሆነበት ሊግ ውስጥ ዳግም የበላይ እንዲሆን ያስችለዋል የሚለው ዕምነት በክለቡ ማህበረስብ ዘንድ ፅኑ ሆነ።

ሁለቱ ክለቦች በዚህ መልኩ የሰነቁትን ተስፋ ይዘው በየራሳቸው መንገድ የገነቡትን ቡድናቸውን እየመሩ ጓዛቸውን ሸክፈው የውድድሩን የመጀመሪያ ዘጠኝ ሳምንታት ወደምታስተናግደው ሀዋሳ ከተማ አቀኑ።

የውድድር ጉዞ በአራት አዘጋጅ ከተሞች…

ውድድሩ ሀዋሳ ላይ ሲጀምር ፋሲል ከነማ የተጣለበትን ግምት ልክ መሆን ያመላከተ አጀማመር አደረገ። ሦስት ተከታታይ ድሎችን ሲያስመዘግብ ስምንት ግቦችን አስቆጥሮ አንድ ጊዜ ብቻ መረቡ ተደፈረ። ይህ አጀማመር ሁለተኛ ተከታታይ የሊግ አሸናፊነትን ለሚያልም ክለብ ድንቅ የሚባል ነበር። በአንፃሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ ጊዜ ከአምስት ነጥቦች በላይ ማለፍ ሳይችል መቅረቱ ሽንፈት አያግኘው እንጂ አስደሳች የሚባል አልነበረም። በደቡባዊቷ ከተማ የተስተናገዱት ዘጠኝ ሳምንታት ሲጠናቀቁ ግን በሁለቱ መካከል የነበረው ልዩነት እንደአጀማመሩ የሰፋ ሰይሆን ቀረ። ፋሲል በአንደኝነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በሁለተኝነት በጨረሱት የሀዋሳ ቆይታቸው በመካከላቸው የነበረው የአንድ ነጥብ ልዩነት ሲሆን ፋሲል በአምስት የግብ ልዩነት ርቀት መምራት ቻለ።

በቀጣይ ውድድሩ ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ አቀና። ሞቃታማዋ ከተማ ግን ባስተናገደቻቸው ስድስት የጨዋታ ሳምንታት መሪ ሆነው ለመጡት ፋሲል ከነማዎች ከባድ ፈተና ሆነች። ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ድሬዳዋ ላይ ከሀዋሳ ቆይታው በእጅጉ ተሻሽሎ ታየ። ፈረሰኞቹ ድሬ ላይ ከሀዋሳ አንፃር ሲታይ የሰበስቡት ነጥብ በመቶኛ ሲሰላ ከ63℅ ወደ 77% ከፍ ያለ ነበር። ፋሲል ሀዋሳ ላይ እንዳደረገው ሁሉ ሦስት ተከታታይ ድሎችን አድርገው በጀመሩት የምስራቅ ቆይታቸው የአንደኝነት ደረጃውን ከመረከባቸው ባለፈ በአምስት የግብ ልዩነት ይበልጣቸው የነበረው ፋሲልን ቦታ ቀይረው የአምስት የግብ ልዩነቱ በእነሱ መሪነት እንዲሆን አደርጉ። የአፄዎቹ የድሬ ቆይታ በጊዮርጊስ የአስር የግብ ልዩነት ብልጫን ብቻ ያስወሰደባቸው ብቻ ሳይሆን የመጀመሪያውን ዙር 4ኛ ደረጃ ላይ ሆነው እንዲጨርሱ ያስገደደ ነበር። ፋሲል ከነማ ሀዋሳ ላይ የነበረው ነጥቦችን የማሳካት ስኬትም ባልተጠበቀ መልኩ በ23% አሽቆለቆለ።

ሊጉ ወደ በሁለተኛው ዙር ሲመለስ የማስተናገድ ተራውን አዳማ ከተማ እንደ ድሬ ሁሉ ለስድስት ሳምንታት ወሰደች። ፈረሰኞቹ በጂዮግራፊ ወደ መቀመጫ ከተማቸው ሲቀርቡ መሻሻላቸውም ይበልጥ ከፍ አለ። እንደ ድሬ ሁሉ በሦስት ተከታታይ ድሎች ውድድሩን ሲጀምሩ የነጥብ አሰባሰብ ስኬታቸውም በአስር ጨምሮ 88℅ ወይንም ከ18 ነጥቦች 16 ፣ በጨዋታ ስንመለከተው ደግሞ ከስድስት ጨዋታዎች አምስት ድል እና አንድ አቻ የተመዘገበበት ሆነ። በአንፃሩ ፋሲል ከነማም የሀዋሳ ቆይታውን መድገም ባይችልም ከድሬዳዋው ደካማ አፈፃፀም አንፃር ተሻሽሎ ታየ። በዚህም ቡድኑ 61℅ የሚሆነውን ነጥብ በስኬት መሰብሰብ ቻለ። ነገር ግን ይህ የፋሲል ከነማ መሻሻል ደረጃውን ወደ 2ኛነት ቢያሳድግለትም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የነበረውን ልዩነት ያሰፋው እንጂ ያጠበበው አልነበረም። የአዳማው ውድድር የመጨረሻ የነበረው 21ኛ ሳምንት ላይ ፋሲል ከነማ ከድሬዳዋው ፍፃሜ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የነበረው የነጥብ ልዩነት በእጥፍ አድጎ አስር ሲደርስ የግብ ልዩነታቸው ደግሞ የ15 ልዩነት የተፈጠረበት ነበር።

እንደመጀመሪያዋ አዘጋጅ ሀዋሳ ሁሉ የዘጠኝ ጨዋታዎች የአዘጋጅነት ድርሻ የተሰጣት ባህር ዳር ለሁለቱም በተስፋ የምትጠበቅ ነበረች። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተከታዮቹ ያለው ርቀት መስፋቱ ወደ ዋንጫው የሚያደርገው ጉዞ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ በልበ ሙሉነት እንዲደረደር የሚያደርገው መሆኑ ነበር የተስፋው ምክንያት። ፋሲል ከነማ ደግሞ በአዳማ የመጨረሻ አራት ጨዋታዎቹ 10 ነጥቦችን ማሳካቱ እንደ ተፎካካሪው ሁሉ በጂኦግራፊ ወደ መቀመጫ ከተማው ሲቀርብ መሻሻሉን አጠናክሮ የመቀጠል ተስፋን በእጁ እንዲያኖር ያደረገ ሆነ። ዛሬ በሊጉ የፍፃሜ ቀን ዋዜማ ላይ ስንገኝ ሁለቱ ቡድኖቹ ከዘጠኙ ጨዋታዎች ስምንቱን አድርገው እንደመሆኑ የውድድሩ አሸናፊ አለመለየቱ የፋሲል ከነማ ተስፋ ወደ እውነታነት ስለመቀየሩ ይነግረናል።

አፄዎቹ ሲዋዥቅ የነበረ አቋማቸውን በባህር ዳር ላይ ባልተጠበቀ ሁኔታ አሻሽለው ነጥብ የመሰብሰብ ስኬታቸውን ሁሉንም ጨዋታዎች በድል በመወጣት 100% ላይ አድርሰዋል። በዚህም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የነበራቸውን የግብ ልዩነት ወደ ከ15 ወደ 8 ሲቀንሱ የነጥብ ልዩነቱን ደግሞ አንድ ብቻ መድረግ ቻሉ። ነገር ግን ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ቻምፒዮንነት በሚያደርገው ጉዞ ከባድ ፈተናን ባስተናገደባት ባህር ዳር እንደሀዋሳ ቆይታው ሁሉ ዝቅተኛውን የነጥብ መስብሰብ ስኬት (63%) ያስመዝግብ እንጂ ዋንጫ የማንሳት ዕድሉን በራሱ የመወሰን የበላይነቱን አሁንም በእጁ እንዳደረገ ወደ መጨረሻው የጨዋታ ሳምንት ማቅናት ችሏል።

የሁለቱ ቡድኖች ውጣ ውረድ ከከተማ ከተማ የተለያየ መልክን ይዞ ወደ መጨረሻዋ ቀን መድረሱ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተከታታዮችን ልብ አንጠልጥሎ ይገኛል። ምስጋና ለቡድኖቹ እስከ ፍፃሜ የዘለቀ ፉክክር ይግባ እና የነገው የፍፃሜ ዕለት በጉጉት እየተጠበቀ የገኛል።

ክፍል ሁለት ይቀጥላል…