ሲዳማ ቡና ወንድማገኝ ተሾመን በዋና አሰልጣኝነት ሾሟል

በጊዜያዊ አሰልጣኝነት ሲዳማ ቡናን ሲመራ የነበረው ወንድማገኝ ተሾመ በዋና አሰልጣኝነት ክለቡን ተረክቧል፡፡

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ስንብት በኋላ የመጨረሻ የጨዋታ ሳምንታትን ከረዳት ወደ ጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት በመምጣት ክለቡ እየመራ በደረጃ ሰንጠረዡ ሦስተኛ ላይ ተቀምጦ እንዲያጠናቅቅ ያስቻለው አሰልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት የሲዳማ ቡና ዋና አሰልጣኝ በመሆን መሾሙን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ በላከው መረጃ ጠቁሟል፡፡

የቀድሞው የሲዳማ ቡና ፣ ሀዋሳ ከተማ እና ሀድያ ሆሳዕና የግራ መስመር ተከላካይ የነበረው ወንድማገኝ ያለፉት ሁለት ዓመታት ከእግር ኳስ ከተገለለ በኋላ የሲዳማ ቡና የተስፋ ቡድንን በማሰልጠን ወደ ስልጠናው የገባ ሲሆን ከዘንድሮው የውድድር ዓመት ጅማሮ አንስቶ የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ረዳት በስተመጨረሻም ጊዜያዊ አሰልጣኝ በመሆን ጥሩ ጊዜን ማሳለፍ በመቻሉ ዋና አሰልጣኝ ሆኖ እንደተሾመ ክለቡ አሳውቋል፡፡