ፈረሰኞቹ የወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን ውል ሊያድሱ ነው

በትናትናው ዕለት በይፋ ወደ ዝውውር ገበያው የገቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የአራት ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን ውል ለማደስ በጠረቤዛ ዙሪያ ተቀምጠዋል።

የ2014 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ባለቤቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ረመዳን የሱፍን ከወልቂጤ ከተማ በማስፈረም በዝውውር መስኮቱ መሳተፍ እንደጀመረ በትናንትናው ዕለት መዘገባችን ይታወሳል። አሁን ከቅርብ ምንጮቻችን ባገኘነው መረጃ መሠረት ደግሞ ክለቡ የ4 ወሳኝ ተጫዋቾቹን ውል ለማደስ በአሁኑ ሰዓት ድርድር እያደረገ መሆኑን አውቀናል።

ይህንን ዘገባ በምንሰራበት ሰዓት ውላቸውን ለማደስ ንግግር ላይ የሚገኙት አቤል ያለው ፣ ከነዓን ማርክነህ ፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ሔኖክ አዱኛ ናቸው። አቤል እና ሔኖክ 2011 ላይ ፈረሰኞቹን ተቀላቅለው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ከነዓን እና አማኑኤል ደግሞ ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ ለክለቡ ግልጋሎት ሲሰጡ ቆይተዋል። ተጫዋቾቹ አሁን ላይ ውላቸው ማለቁን ተከትሎ ለማራዘም በንግግር ላይ እንደሚገኙ ሶከር ኢትዮጵያ ያረጋገጠች ሲሆን ከክለቡ ጋር ለመቀጠል የመስማማታቸው ጉዳይ ከጫፍ መድረሱን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።