ባህር ዳር ከተማ አማካይ ወደ ስብስቡ ለመቀላቀል ተስማማ

በትናንትናው ዕለት ያሬድ ባየህን የመጀመሪያው ፈራሚው ያደረገው ባህር ዳር ከተማ ናይጄሪያዊውን አማካይ የግሉ ለማድረግ በቃል ደረጃ ስምምነት ላይ ደርሷል።

በአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ የሚመራው ባህር ዳር ከተማ ከቀናት በፊት በተከፈተው የዝውውር መስኮት በንቃት ለመሳተፍ የተለያዩ ተጫዋቾችን እያነጋገረ የሚገኝ ሲሆን ምሽት ላይም በፋሲል ከነማ ጥሩ ጊዜን ያሳለፈው ያሬድ ባየህን የግሉ ማድረጉን ይፋ አድርጓል። አሁን ባገኘነው መረጃ ደግሞ ክለቡ በአዲስ አበባ ከተማ የውድድር ዓመቱን ያገባደደው ቻርለስ ሪባኑን ለማስፈረም በቃል ደረጃ ስምምነት ላይ ደርሷል።

በሀገሩ ናይጄሪያ ዲያፋ አካዳሚ ውስጥ ሲጫወት ቆይቶ በ2013 በከፍተኛ ሊግ የሚወዳደረውን ሀምበሪቾ ዱራሜን ተቀላቅሎ የነበረው የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ቻርለስ ሪባኑ ዘንድሮ በአዲስ አበባ ከተማ በግሉ ስኬታማ ቆይታን አድርጎ ነበር። በአሁኑ ሰዓት ሀገሩ ናይጄሪያ የሚገኘው ተጫዋቹም ሌላኛውን የክልሉ ክለብ ፋሲል ከነማ ጨምሮ ሌሎች ክለቦች ፍላጎት እያሳዩበት ቢሆንም በቃል ደረጃ ውሃ ሰማያዊውን መለያ ለመልበስ መስማማቱ ታውቋል።