ጦሩ ወሳኝ ተጫዋች የግሉ አድርጓል

በቅርቡ ዋና አሠልጣኙን ይፋ ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቀው መከላከያ በፋሲል ከነማ ውሉ የተገባደደውን የመስመር ተጫዋች ማስፈረሙ ታውቋል።

ፕሪምየር ሊጉን ዳግም ከተቀላቀለ በኋላ ለከርሞም መሳተፉን ያረጋገጠው መከላከያ በቀጣዩ ዓመት ስብስቡን ለማጠናከር በዝውውር ገበያው መሳተፍ ጀምሯል። ከደቂቃዎች በፊትም ከፋሲል ከነማ ጋር ያለው ውል የተጠናቀቀውን በረከት ደስታን የግሉ ማድረጉ ተረጋግጧል።

ከአዳማ ወጣት ቡድን የተገኘው በረከት ደስታ ወደ ዋናው ቡድን ካደገ በኋላ እስከ 2012 ቆይታን አድርጎ ወደ ፋሲል ከነማ አምርቶ ነበር። በፋሲል ከነማም በግሉም ሆነ እንደ ቡድን ስኬታማ ጊዜን ያሳለፈ ሲሆን ዓምናም የሊጉን ዋንጫ ከፍ አድርጎ አንስቷል። ተጫዋቹም ከደቂቃዎች በፊት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በመገኘት ለሁለት ዓመት የሚያቆየውን ውል መፈረሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።