አፄዎቹ የመስመር አጥቂ አስፈርመዋል

በሲዳማ ቡና መለያ የሚታወቀው አጥቂ ቀጣይ ማረፊያው ፋሲል ከነማ ሆኗል፡፡

ከሰሞኑ ውል ማራዘም እና መለያየት ላይ ቆይቶ የነበረው ፋሲል ከነማ ወደ ዝውውሩ በዛሬው ዕለት በመግባት አዲስ ቅጥሮችን እየፈፀመ የሚገኝ ሲሆን አሁን ደግሞ የመስመር አጥቂው ሀብታሙ ገዛኸኝን የግሉ አድርጓል፡፡

ሀብታሙ በደቡብ ፖሊስ እግርኳስን መጫወት የጀመረ ሲሆን ያለፉትን አምስት ዓመታት በሲዳማ ቡና ቤት ዕድገቱን ማስቀጠል ችሎ በዛሬው ዕለት ደግሞ ሦስተኛ ክለቡ ወደሆነው ፋሲል ከነማ በሁለት ዓመት ውል አምርቷል፡፡

ክለቡ በዛሬው ዕለት ካስፈረማቸው አዳዲስ ተጫዋቾች በተጨማሪ የይድነቃቸው ኪዳኔ እና ዓለምብርሀን ይግዛውን ውል ማደሱ ይታወሳል፡፡