ከነዓን ማርክነህ በይፋ መከላከያን ተቀላቅሏል

ከመከላከያ ጋር ቅድመ ስምምነት ፈፅሞ የነበረው ከነዓን ማርክነህ በይፋ የጦሩ ተጫዋች ሆኗል።

በዝውውር ገበያው የነቃ ተሳትፎ እያደረገ የሚገኘው መከላከያ በዛሬው ዕለት አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝን በመንበሩ መሾሙን ይፋ አድርጎ ነበር። ለቀጣይ ዓመት ስብስቡን በአዲስ መልክ እያዋቀረ የሚገኘው ቡድኑ ከዚህ ቀደም ዳግም ተፈራ ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ ፣ ምንይሉ ወንድሙ እና በረከት ደስታን ያስፈረመ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ ቅድመ ስምምነት ፈፅሞ የነበረውን ከነዓን ማርክነህን በይፋ የግሉ አድርጓል።

ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ቻምፒዮን የሆነው ከነዓን ውሉ እስከ ነሐሴ 30 የሚዘልቅ መሆኑን ተከትሎ ዝውውሩ ለሁለት ቀናት ዘግይቶ የነበረ ቢሆንም የቀሪ ቀናት ቆይታውን ውል ከፈረሰኞቹ ጋር አፍርሶ ለመከላከያ የሁለት ዓመት ፊርማውን ማኖሩን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።