የተከላካይ አማካዩ መከላከያን ተቀላቅሏል

ቡድኑን በአዲስ መልክ እያዋቀረ የሚገኘው መከላከያ ከሀዲያ ጋር ውሉን አራዝሟል ተብሎ በክለቡ በኩል የተገለፀውን ተጫዋች የግሉ አድርጓል።

በአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ እየተመራ ቀጣዩን የውድድር ዓመት የሚቀርበው መከላከያ እስካሁን የበረከት ደስታ፣ ከነዓን ማርክነህ፣ ዳግም ተፈራ፣ ዳሙኤል ሳሊሶ እና ፍፁም ዓለሙን ዝውውር ያገባደደ ሲሆን ከደቂቃዎች በፊት ደግሞ ግዙፉን የተከላካይ አማካይ ተስፋዬ አለባቸውን ወደ ስብስባቸው መቀላቀላቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ከቀናት በፊት የሀዲያ ስራ-አስኪያጅ አቶ አባተ ተስፋዬን ዋቢ አድርገን ተስፋዬ ከከቤራዎቹ ጋር ይቆያል ብለን ዜና ሰርተን የነበረ ቢሆንም ጉዳዩ ሀሰት እንደሆነ አረጋግጠናል። የቀድሞው የሰበታ ከተማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወልድያ ከተማ የተከላካይ አማካይ ስፍራ ተጫዋች የሆነው ተስፋዬ ከ2013 ጀምሮ በሀድያ ሆሳዕና መለያ ሲጫወት ማሳለፉ የሚታወቅ ሲሆን አሁን ደግሞ ከቀድሞ አሠልጣኙ ፋሲል ተካልኝ ጋር አብሮ ለመስረት በሁለት ዓመት ውል ጦሩን ተቀላቅሏል።