ሲዳማ ቡና የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር ፈፅሟል

ከሰዓታት በፊት ፍሊፕ ኦቮኖን የግሉ ያደረገው ሲዳማ ቡና አሁን ደግሞ አጥቂ እና ተከላካይ አስፈርሟል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ሲዳማ ቡና በቀጣዩም ዓመት ተጠናክሮ ለመምጣት ጊዜያዊ አሠልጣኙን ወንድማገኝ ተሾመ በዋናው መንበር ከሾመ በኋላ ትኩረቱን የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ላይ አድርጓል። ከሰዓታት በፊት ኢኳቶሪያል ጊኒያዊውን የግብ ዘብ ፍሊፕ ኦቮንኖ ማስፈረሙን ዘግበን የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን የግሉ ማድረጉን አረጋግጠናል።

ቡድኑን የተቀላቀለው የመጀመሪያው ተጫዋች አንተነህ ተስፋዬ ነው። የቀድሞው የአርባምንጭ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ተጫዋች ያለፉትን ዓመታት በሰበታ ከተማ ሲጫወት የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ ወደ ቀደመ ክለቡ ሲዳማ ቡና በአንድ ዓመት ውል መመለሱ እርግጥ ሆኗል።

ሁለተኛው ተጫዋች ደግሞ ፀጋዬ አበራ ነው። የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን በአርባምንጭ ከተማ ያሳለፈው የመሐል እና የመስመር አጥቂው ፀጋዬ ደግሞ በሲዳማ ቤት ለመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ለመቆየት መፈረሙን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል።