ኢትዮ ኤሌክትሪክ የግብ ጠባቂውን ውል አራዝሟል

ወደ ዝውውሩ በመግባት እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የግብ ጠባቂውን ውል ማራዘሙ ታውቋል።

በአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና እየተመራ በቀጣይ ዓመት በሊጉ ተሳታፊ የሚሆነው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ግብ ጠባቂው ሰለሞን ደምሴን የመጀመርያ ፈራሚ ማድረጉን በትናንትናው ዕለት ዘግበን ነበር። በዛሬው ዕለት ደግሞ የወሳኙን ግብ ጠባቂ ዘሪሁን ታደለን ውል ለአንድ ተጨማሪ ዓመት ማራዘሙን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ዘሪሁን ከዚህ ቀደም ለዘጠኝ ዓመታት ከተጫወተበት ቅዱስ ጊዮርጊስ በመልቀቅ ወደ ጅማ አባ ጅፋር በማምራት ቆይታ ያደረገ ሲሆን ለኢትዮ ኤሌክትሪክን ያለፉት ሁለት ዓመታት ግልጋሎት ሲሰጥ ነበር። በተለይ ቡድኑ ከአራት ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ ሊጉ እንዲመለስ ትልቁን ድርሻ የተወጣ ግብ ጠባቂ እንደነበረም አይዘነጋም።