ወልቂጤ ከተማ አሠልጣኝ ሾመ

አሠልጣኝ ተመስገን ዳናን በኢትዮጵያ ቡና የተነጠቁት ወልቂጤ ከተማዎች ገብረክርስቶስ ቢራራን በመንበሩ መሾማቸው ታውቋል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን የደረጃ ሰንጠረዡን አካፋይ ቦታ ይዞ ያጠናቀቀው ወልቂጤ ከተማ የቀጣይ ዓመት ስብስቡን እንደ አዲስ እያደራጀ የሚገኝ ሲሆን ከደቂቃዎች በፊትም የአራት አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ማገባደዱን ዘግበን ነበር። አሁን ከክለቡ ባገኘነው መረጃ ደግሞ ገብረክርስቶስ ቢራራን በአሠልጣኝነት መንበሩ ሾሟል።

ዲላ ከተማን በመቀላቀል የስልጠናውን ዓለም የተቀላቀሉት ገብረክርስቶስ ቢራራ በደቡብ ክልል የሚገኙ የተለያዩ የእድሜ ቡድኖችን ያሰለጠኑ ሲሆን ደቡብ ፖሊስን እንዲሁም ወላይታ ድቻን በፕሪምየር ሊጉ መርተዋል። ዘለግ ላሉ ጊዜያት ከስልጠናው ከራቁ በኋላ ዳግም በፕሪምየር ሊጉ ለማሰልጠን በክለቡ አመራሮች የተመረጡ ሲሆን በነገው ዕለትም በይፋ ፊርማቸውን እንደሚያኖሩ ተጠቁሟል።