ኢትዮ ኤሌክትሪክ የተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾችን ውል አድሷል

ፕሪምየር ሊጉን ዳግም የተቀላቀለው ኢትዮ ኤሌክትሪክ አዳዲስ ተጫዋቾችን እያስፈረመ የሚገኝ ሲሆን የነባር ተጫዋቾችንም ውል እያደሰ ይገኛል።

ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ያሳደጉትን አሠልጣኝ ክፍሌ ቦልተናን ውል ለአንድ ዓመት ካራዘመ በኋላ ወደ ዝውውር ገበያው ጎራ ያለው ኢትዮ ኤሌክትሪክ አዳዲስ ተጫዋቾችን እያስፈረመ ሲሆን የነባር ተጫዋቾችንም ውል ጎን ለጎን እያደሰ ይገኛል። አሁን ባገኘነው መረጃም ቡድኑ የሁለት ተጫዋቾችን ውል አድሷል።

ውሉን ያደሰው የመጀመሪያው ተጫዋች አቤል ሀብታሙ ነው። የአጥቂ መስመር ተጫዋቹ አቤል የውድድር ዓመቱን በሌላኛው የከፍተኛ ሊግ ክለብ ጅማ አባ ቡና ጀምሮ የነበረ ቢሆንም በግማሽ ዓመት ኤሌክትሪክን ተቀላቅሎ ሲጫወት ነበር። ሌላኛው ተጫዋች ደግሞ ማታይ ሉል ነው። እንደ አቤል ሁሉ ከጅማ አባ ቡና ኤሌክትሪክን በግማሽ ዓመት የተቀላቀለው ይህ ተከላካይ ቀይ እና ነጩን መለያ ለቀጣይ ዓመት ለብሶ ለመዝለቅ ውሉን ማደሱ ታውቋል።